የጩኽት ውድድር በውቅያኖስ ዳር

0
39

በአሜሪካ ሳንፍራሲስኮ የውቅያኖስ ዳርቻ ከመቶ በላይ በሚሆኑ ተሳታፊዎች መካከል የጩኽት ውድድር መካሄዱን ያሁ ድረ ገጽ ከሳምንት በፊት ለንባብ አብቅቶታል፡፡

መስከረም 12/2026 እ.አ.አ በባሕር ዳርቻ የተካሄደውን የከፍተኛ የድምፅ ጩኽት ውድድር ዳንኤላ ኤጋን በተሰኘች ሴት አነሳሽነት እና አዘጋጅነት መከወኑን ድረ ገፆች አስነብበዋል፡፡

በውድድሩ ላይ ከመቶ በላይ የሚሆኑ ተሳታፊዎች ተካፍለዋል፡፡ “ስክሪም ቱዎርድስ ዘ ሲ” በሚል በተዘጋጀው በዚሁ ሁነትም ከመቶ በላይ ተሣታፊዎች ተገኝተዋል፡፡ ተሣታፊዎቹ በተናጠል ባካሄዱት የጩኽት ውድድር  አንደኛ የወጣችው አሸናፊ ኦሊቪያ ጉግሊ ኤልሞቶ ያስመዘገበችው የጩኽት መጠንም 121 ነጥብ ዘጠኝ ዴሲቤል (የድምፅ መጠን መለኪያ) ነው፡፡ በእለቱ የተመዘገበው የጩኽት መጠንም በዓለም  አቀፍ ክብወረሰን ሆኖ ለተመዘገበው 129 ዴሲቢል የቀረበ መሆኑም ነው የተሰመረበት፡፡

በጩኽት ውድድሩ ሁለተኛ ደረጃን ያገኘችው ኪያና ቫን ሃውተን ስድስት ነጥብ 78 ሰከንዶች የዘለቀ 114 ነጥብ ሦስት ዴሲቤል የተለካ ጩኽት አሰምታለች፡፡ በውድድሩ አንደኛ ደረጃን ያገኘችው ኦሊቪያ በታዳጊነት ዘመኗ በአቅራቢያዋ በነበረ “ኤሪ” የተሰኘ ኃይቅ ዳር ስትጮኽ እንዳደገች ተናግራለች – ዛሬ ላይ ላስመዘገበችው ውጤቷም አበርክቶው ላቅ ያለ መሆኑን ነው ያሰመረችበት፡፡

ከተናጠል ውድድሩ በኋላ ተሣታፊዎቹ በጋራ ወደ ውቅያኖስ ፊታቸውን አዙረው ለ60 ሰከንዶች መጮሀቸውን ድረ ገፆች አስነብበዋል- ለዚህ አብዛኛዎቹ ለዓመታት በውስጣቸው አምቀው ከያዟቸው  የተለያዩ ስሜቶች መንፃታቸው  ነው በማደማደሚያነት በድረ ገጹ የሰፈረው፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመስከረም  18 ቀን 2019  ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here