ያዩ የጫካና ቡና መጠበቂያ

0
37

ያዩ የጫካ ውስጥ ቡና መጠበቂያ በኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ ደቡብ ምእራብ አቅጣጫ 64 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በኢሉ አባቦራ ዞን ነው የሚገኘው፡፡ ጠቅላላ ስፋቱም 167,021 ሄክታር ተለክቷል፡፡ ቀጣናው በዓለም ተመራጭ የሆነው “ኮፊ አረቢካ” የተሰኘው የቡና ዝርያ ከሚገኝባቸው ጥቂት ቦታዎች አንዱ ነው፡፡በ2010 እ.አ.አ በ“ዩኔስኮ” የ“ባዮስፌር ሪዘርቭ” ተብሎ እውቅና አግኝቷል፡፡

በዞኑ ስድስት ወረዳዎች የተካለለው “ኮፊ አረቢካ” የቡና ዝርያው ከ27,733 ሄክታሩ ዋና ጥብቅ ቀጣና፣ 21552  ሄክታሩ መጠባበቂያ፣ ቀሪ 117736  ሄክታሩ የሽግግር ቀጣና ተብሎ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ በሽግግር ቀጣናው ኗሪዎች ቡና እና ሌሎች አዝርእትን እንዲያመርቱ ይፈቀድላቸዋል፡፡ በዋና ጥብቅ ቀጣናው ድንበር (በፈር ዞን) ግን አዝርእትን ማምረት የተከለከለ መሆኑን ድረገፆች አስነብበዋል፡፡

በያዩ የጫካ ቡና መጠበቂያ ቀጣና 450 የእፅዋት ዝርያ፣ 50 አጥቢ እንስሳት፣ 20“ ኦምፊቢያንስ” 200 የዓእዋፍ ዝርያዎች መገኘታቸው ተረጋግጧል በጫካው ውስጥ ከሚገኙ እፅዋት እና እንስሳቱ 100 ያህሉ ብርቅዬ እና የመጥፋት አደጋ ያንዥበበባቸው ናቸው፡፡

በመልካ ምድሩ ደን፣ ረግረጋማ ቀጣና፣ የሳር ምድር፣ የእርሻ መሬት፣ ዋሻ እና ፏፏቴዎች መገኘታቸውም ተረጋግጧል፡፡ በቀጣናው የሚደረገው ጥበቃ እና ቁጥጥር በመጠናከሩም  ለዘላቂነቱ ስጋት የነበረው የደን መጨፍጨፍ ምጣኔ ከዜሮ ነጥብ ሰባት በመቶ ወደ ዜሮ ነጥብ አራት በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡

የደን ውስጡን “አረቢካ” የቡና ዝርያ ለመጠበቅ ግብር ሃይል የተቋቋመ ሲሆን አዳዲስ የቡና ችግኝ በመትከል ቀጣናውን ለማስከበር እየሰራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ለዘገባችን በመረጃ ምንጭነት ያዩ ባዮስፌር ድረገጽ፣ ሀርነስቲፍቲንግ ድረ ገጽ እና ዩኔስኮ ዶት ኦርግ ድረገፆችን ተጠቅመናል፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር የመስከረም  18 ቀን 2019  ዓ.ም ዕትም

 

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here