ቱሪዝም – ከፈተና ወደ አዲስ የመነቃቃት ምዕራፍ

0
43

አዲስ አድማስን የማየት ጉጉት፣ አዳዲስ ባሕሎችን የመጋራት ጥማት እና ከዕለት ተዕለት ጭንቀት የመላቀቅ ፍላጎት የሰው ልጅ ከጥንት ጀምሮ ያደገ ፍላጎት ነው። ዛሬ ላይ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከቀን ወደ ቀን እየተቀየረ፣ የብዙኃንን ትኩረት ስቧል። ይሁን እንጂ ቱሪዝም ማለት ከጉዞና ከዕረፍት ባለፈ ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ማበብ፣ ለባሕል ልውውጥ እና ለቀጣናዊ ዕድገት ያለው ሚና የላቀ ነው።

ኢትዮጵያ ደግሞ በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ጸጋዎቿ የታደለች ሀገር ናት፤ የአማራ ክልልም በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ በሰማይ ጠቀስ የተፈጥሮ ግርማ ሞገሳቸው በሚደነቁት የስሜን ተራሮች አናት፣ ከዓለት የተፈለፈሉት የላሊበላ ድንቅ ጥበባት፣ እንዲሁም በጥንታውያን ገዳማት ባሸበረቀው የጣና ሐይቅ ውቅያኖሳዊ ማዕበል ውስጥ የአማራ ምድር የዘመናት ታሪክ፣ ባሕልና ተፈጥሮ በስምምነት የፈሰሱበት ሕያው ሙዚየም ነው።

ይሁን እንጂ ቱሪዝም እንደ እንቁላል ስስ፣ እንደ ንጋት ጤዛ ረቂቅ ነው። ይህ ዘርፍ የሚተነፍሰው የተረጋጋ ሰላም ሲኖር ነው። ተጓዥ ከቀየው ተነስቶ ወደማያውቀው ምድር የሚተመው ደህንነቱ አስተማማኝ መሆኑን በልበ-ሙሉነት ሲያረጋግጥ ብቻ ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሰሜኑን ጦርነት ተከትሎ በመጣው አለመረጋጋት ሳቢያ የቱሪዝም ዘርፉ ክፉኛ ተጎድቷል።

ሆኖም ታሪክ እንደሚያስተምረን፣ ፈተናዎች አዳዲስ የህልውና መንገዶችንም ይወልዳሉ። ዛሬ ላይ የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ዘርፉን ከገጠመው ፈተና ለማንሳት፣ የተጎዱ አካባቢዎችን ለማካካስና የቱሪዝም ምህዳሩን ወደ አዲስ የዕድገት ምዕራፍ ለማሸጋገር ዘርፈ-ብዙ ስልቶችን ነድፎ እየሠራ ይገኛል።

ከበኩር ጋር ቆይታ ያደረጉት የቢሮው የቱሪዝም ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መልካሙ አዳም የሚያነሷቸው ነጥቦችም ይህንኑ ነው የሚያጠናክሩት።

ቱሪዝም እንደ ሌሎች ዘርፎች ተነጥሎ የሚቆም ሳይሆን፣ እልፍ ዜጎችን በሥራ ዕድል የሚሸከም ግዙፍ የኢኮኖሚ ምሰሶ ነው። በክልሉ የተከሰተው አለመረጋጋት ቀጥተኛ ተጎጂዎች ያደረገውም ይኸንኑ የሰው ኃይል ክፍል እንደሆነ አቶ መልካሙ ለበኩር በሰጡት መረጃ ተናግረዋል። “እንደ ላሊበላ እና ደባርቅ (የስሜን ተራሮች መግቢያ) ያሉ ከተሞች ኑሯቸው ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ በቱሪዝም ፍሰት ላይ የተንጠለጠለ ነው” ያሉት አቶ መልካሙ  እነዚህ አካባቢዎች ከፍተኛ የግብርና ትርፍ አምራች ባለመሆናቸው፣ “የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር መቀነስ በቀጥታ የዜጎችን የዕለት ጉርስ ፈትኖታል” ።

ዳይሬክተሩ አክለውም አስጎብኚዎች፣ የሆቴል ባለሙያዎች፣ የመኪና አከራዮች እና የእደ-ጥበብ ቅርሶችን ሸጠው የሚያድሩ ዜጎች ሥራ እስከመቀየርና ለከፋ ማሕበራዊ ቀውስ እስከመዳረግ ደርሰዋል።

የጉዳቱ መጠን እስካሁን በቁጥር ተጠንቶ ይፋ ባይደረግም በተለይም የውጭ ምንዛሪ ምንጭ የሆኑት የዓለም አቀፍ ጎብኚዎች መቀነስ በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሱን አንስተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በስጋት ወደ ኋላ ባፈገፈጉበት ወቅት፣ ክልሉ ዘርፉን በእግሩ ለማቆም የተለያዩ ስልቶችን ተጠቅሟል፤ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም እና የአደባባይ ክብረ በዓላት ቱሪዝሙን ለማነቃቃት ከተጠቀምንባቸው ስልቶች ዋነኞቹ ናቸው።

ላሊበላ ዓመቱን ሙሉ እንግዳ የሚጎርፍበት ድንቅ ቦታ ነው፤ በችግሩ ወቅትም የገና (ልደት) በዓል ለነዋሪዎች ትልቅ የኢኮኖሚ እስትንፋስ ሆኖ አገልግሏል። “ቢሮው ይህንን ተሞክሮ በማስፋት እንደ መስቀል፣ ጥምቀት እና ባሕላዊ የክረምት ሁነቶችን በድምቀት በማክበር፣ ሕብረተሰቡ ያለ ስጋት እንዲንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል” ብለዋል።

ይህ አካሄድ መንፈሳዊና ባሕላዊ እሴትን በቀጥታ ወደ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የመቀየር ስልታዊ እርምጃ ነው፤ በዓላቱ በሚከበሩባቸው ወቅቶች የሚፈጠረው የንግድ እንቅስቃሴ የአካባቢውን ማሕበረሰብ ከገባበት የኢኮኖሚ ፈተና በከፊልም ቢሆን የታደገ የሕልውና አድን ድልድይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህንን ለማጠናከር እና ለማሳደግ የአማራ ክልል የቱሪስት መስመር ለበርካታ ዐሥርት ዓመታት ከአዲስ አበባ ተነስቶ በደጀን፣ ባሕር ዳር እና ጎንደር አድርጎ ወደ ስሜን ተራሮች የሚያመራ የነበረው መስመር  በአሁኑ ወቅት ወደ ምሥራቅ አማራ ኮሪደር በማተኮር  ከአዲስ አበባ ተነስቶ በደብረ ብርሃን፣ ደሴ፣ ሐይቅ፣ ላሊበላ እና ዋግኸምራ አድርጎ ወደ አጎራባች ክልሎች የሚዘልቅ ሰፊ ዕድልን እንዲይዝ እየተሰራ ነው።

በዚህ መስመር ላይ የሚገኙትና እስካሁን በሚገባ ያልተዋወቁት የሾንኬ መንደር፣ የደቡብ ወሎው የተፈጥሮ ገጸ-በረከት ሐይቅ ከተማና ገዳማቱ፣ እንዲሁም በጋሸና አካባቢ የሚገኘው አስደናቂው ዳግማዊ ላሊበላ እና የደብረ ታቦሩ ውቅሮ መድኃኔዓለም የድንጋይ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለጎብኚዎች ምቹ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሠራበት መሆኑን አብራርተዋል።

በተጨማሪም ከስሜን ተራሮች ባሻገር፣ ከፍተኛ የተራራ ላይ የእግር ጉዞ የሚካሄድባቸው የጮቄ፣ የጉና እና የአቡነ ዮሴፍ ተራራ ሰንሰለቶች ያልተነኩ የተፈጥሮ ጸጋዎች ናቸው፤ አካባቢዎቹን የጉብኝት ማዕከል (መዳረሻ) ማድረግ ደግሞ አንዱ የቢሮው ትኩረት ነው።

“የመረጃ ክፍተትን ለመድፈን የተዘረጋው የዲጂታል ስትራቴጂ ሌላኛው ተስፋ ሰጪ ርምጃ ነው” ያሉት አቶ መልካሙ ባለፉት ዐሥር ዓመታት ሲያገለግል የቆየው የቪዚት አማራ የማሕበራዊ ሚዲያ ድረ ገጽ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አሁን ላይ “የተቀናጀ የቱሪዝም አስተዳደር ሥርዓት”  የተሰኘ ዘመናዊ ድረ ገጽ (ፖርታል) ተገንብቶ ወደ ሥራ ገብቷል።

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ይህ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ፖርታል፣ አንድ ጎብኚ የት መሄድ እንዳለበት መረጃ ከማግኘት ጀምሮ፣ ሆቴል የመያዝ፣ የመኪና ኪራይ አገልግሎቶችን የማወዳደር እና ብቁ አስጎብኚዎችን በአንድ ዲጂታል ቋት የማግኘት ዕድልን ይፈጥርለታል። ከዚህ ጎን ለጎን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸውን የቲክቶክ እና የቪዲዮግራፊ ባለሙያዎችን  በማስተባበር የክልሉን ገጽታ በፈጠራ ይዘቶች በስፋት ለማስተዋወቅ እና ለመሥራትም ዕድሉን እንደሚያሰፋ ነው የተናገሩ።

በበጀት ዓመቱም ክልሉ ከ19 ሚሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ እና ከ58 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን አስተናግዷል፤ ከሀገር ውስጥ ቱሪዝም ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ደግሞ ከ374 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህም ዘርፉ እያገገመ ስለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።

ይሁን እንጂ ይህንን ተስፋ ወደ ዘላቂ ስኬት ለመቀየር የመሠረተ ልማት እጥረቶች አሁንም ፈተናዎች ናቸው፤ ሆኖም ችግሩን መፍታት እና የግሉን ዘርፍ ኢንቨስትመንት ማነቃቃት ደግሞ ፈተናውን ለመሻገር አስቻይ ሁኔታዎች ስለመሆናቸው ነው አቶ መልካሙ የተናገሩት። ለዚህ ማሳያ ደግሞ በደብረ ብርሃን የተገነባውን የኃይሌ ሪዞርትን እና በሐይቅ እና በጎርጎራ የተከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶችን ነው ያነሱት።

በመሆኑም በሁሉም አዳዲስ መስመሮች ደረጃቸውን የጠበቁ ማረፊያዎችና መንገዶች እንዲሟሉ ባለሀብቱ በስፋት እንዲሰማራ  አቶ መልካሙ ጥሪ አቅርበዋል።

በአጠቃላይ፣ የአማራ ክልል የቱሪዝም ዘርፍን ከገባበት ፈተና ለማውጣት እና አሁን ያለውን መነቃቃት ይበልጥ ለማጠናከር የመንግሥት የመሠረተ ልማትና የፖሊሲ ድጋፍ፣ የሚዲያው (በተለይም እንደ አሚኮ ያሉ ግዙፍ የሕዝብ ተቋማት) የማስተዋወቅ ጥረት፣ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እና ከምንም በላይ ደግሞ የሕብረተሰቡ ሰላምን በጋራ የማስጠበቅ ቁርጠኝነት ቅንጅት ወሳኝ ናቸው፤ በመጨረሻም “ሰላም ሲጸና ጥበብ ይደምቃል፤ ጥበብ ሲደምቅ ደግሞ የአማራ ምድር በዓለም የጉዞ ካርታ ላይ ድምቀቱ ዳግም ፈክቶ ይታያል” ሲሉ ነው አቶ መልካሙ የቱሪዝምን እና የሰላምን ቁርኝት አጽንኦት በመስጠት ጥሪ ያቀረቡት።

ከዓለም ምን እንማር?

ሀብት መታደል ብቻውን ዋጋ የለውም፤ ትልቁ ጥበብ የታደሉትን ጸጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ አቅም መቀየር መቻል ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአፍሪካዊቷ ጎረቤታችን የኬንያ እና የእሲያዊቷ ግዙፍ ሀገር የቻይና ተሞክሮዎች ማሳያዎች ናቸው፤ የሀገራቱ ተሞክሮ ደግሞ ለኢትዮጵያ በብዙው ያስተምራሉ፡፡

ትኩረቱን ቱሪዝም ላይ አድርጎ መረጃዎችን የሚያጋራው ኬንያ ኤክስፔሪያንስ (www.kenya-experience.com)   የተባለው ድረ ገጽ እንዳስነበበው ጎረቤታችን ኬንያ ከኮቪድ -19 ወረርሽኝ እና ከፀጥታ ስጋቶች ማግስት ባስመዘገበችው አስደናቂ የማገገም ፍጥነት በ2023 እ.ኤ.አ ብቻ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን በመሳብ ከሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ ዓመታዊ ገቢ ሰብስባለች፡፡

ለዚህ ስኬት የበቃችው ደግሞ  የኬኒያን ብራንድ በማስተዋወቅ፣ የቱሪዝም ምርቶቿን በማብዛት፣ መሠረተ ልማቶችን በማሻሻል፣ ዲጂታል ቴክኖሎጅን በመጠቀም እና ከአካባቢው ማሕበረሰብ ጋር ተቀናጅታ በመሥራት መሆኑን የመረጃ ምንጩ አስነብቧል፡፡

በሌላ በኩል ቻይና ከወረርሽኙ ማግስት በጥቂት ወራት ውስጥ በዘረጋችው ጠንካራ የዲጅታል ቴክኖሎጅ እና የመሠረተ ልማት ትስስር በ2023 እ.ኤ.አ ብቻ ከአራት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን በላይ የሀገር ውስጥ የጉዞ እንቅስቃሴዎችን በማስተናገድ ከ700 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዓመታዊ ገቢ ማግኘቷን ያስነበበው ወርልድ ዳታ (www.worlddata.info) የተሰኘው የመረጃ ምንጭ ነው፡፡

(ሰናይት በየነ)

በኲር የመስከረም  18 ቀን 2019  ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here