ጣራ ገዳም

0
28

“ጣራ ገዳም” ከባሕር ዳር ወደ ጎንደር በሚወስደው የአስፓልት መንገድ ዳር ከአዲስ ዘመን ከተማ በቅርብ ርቀት ከጣና ሐይቅ ሰሜን ምሥራቅ ይገኛል፡፡ ጥቅጥቅ ባለው እና ረዥም ዘመናትን ባስቆጠረው የተፈጥሮ ደን ውስጥ የሚገኘው ጣራ ገዳም የሰው ልጅ ከመንፈሳዊ ሕይወቱ ባሻገር ተፈጥሮን እንዴት ተንከባክቦ ማቆየት እንደሚችል የሚያሳይና ታላቅ ተሞክሮ የሚቀሰምበት የታሪክ እንዲሁም የብዝኃ ሕይወት መገኛ መሆኑን ከ”ቪዚት ኢትዮጵያ ዶት ኢቲ” እንዲሁም “ቱርኢትዮጵያ ዶት ኢቲ” ድረ ገጾች ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ጣራ ገዳም የክርስትና ሃይማኖት በዐፄ ኢዛና ዘመነ መንግሥት (ከ330 እስከ 356 ዓ.ም.) በይፋ ወደ ኢትዮጵያ  ከመግባቱ በፊት የኦሪት ሥርዓት ይፈጸምበት የነበረ ጥንታዊ ስፍራ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ አካባቢ በዐፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት አቡነ እንድሪያስ የተባሉ መንፈሳዊ አባት ቶማስ ከተባሉ አባት እና ከሌሎች ተከታዮቻቸው ጋር ወደ ስፍራው በማቅናት ዋሻውን የክርስትና ሃይማኖት ማስተማሪያ እና የብሕትውና ስፍራ አድርገውታል፡፡

በሌላ በኩል በዚሁ የደን ክልል ውስጥ የሚገኘው የአቡነ ኤዎስጣቴዎስ ገዳም እና የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ለገዳማዊ ሕይወት መስፋፋት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ ገዳሙ ከመንፈሳዊ ዕሴቱ ባሻገር በርካታ የማይተኩ ጥንታዊ ቅርሶች የሚገኙበት  የመስህብ ስፍራ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በነገሥታት እና በሃይማኖት መሪዎች ከፍተኛ ክብር እና ትኩረት ተሰጥቶት ኖሯል፡፡

በ17ኛው ክፍለ ዘመን እንደተመሠረተ በሚነገርለት በዚህ ገዳም ውስጥ ከብራና የተዘጋጁ ጥንታዊ መጻሕፍት፣ በወርቅ እና በብር የተለበጡ መስቀሎች፣ የነገሥታት አልባሳት እንዲሁም ንዋያተ ቅድሳት  ይገኙበታል፡፡

በደኑ ውስጥ የሚገኘውና ከሀያ ኪሎ ሜትር በላይ ይረዝማል ተብሎ የሚገመተው ተፈጥሯዊ ዋሻም የታሪክ ተመራማሪዎችን እና ጎብኝዎችን በእጅጉ የሚስብ  ቅርስ ነው፡፡ የዋሻ እንድሪያስ እና የወይን ዋሻ ተክለ  ሃይማኖት አብያተ ክርስቲያናት የተገነቡበት የድንጋይ ቋጥኝ እንዲሁም የዋሻው መዋቅር የጥንታውያን ኢትዮጵያውያንን የሕንጻ ጥበብ እና ተፈጥሮን የመግራት ክህሎት የሚያሳይ ነው፡፡ በገዳሙ የሚገኙት የቅዱሳን አባቶች አጽም እና ጥንታዊ ይዞታዎች የቦታውን የመስህብ ቦታነት ይበልጥ ያገዝፉታል፡፡

“የደን ብዝኃ ሕይወት የቱሪዝሙን ዘርፍ ለማሳደግ ያለው ሚና” በሚል ርዕስ በ2017 እ.አ.አ በተካሄደ ጥናት ላይ እንደተጠቆመው በጣራ ገዳም ዙሪያ የሚገኘው ጥቅጥቅ የተፈጥሮ ደን እንዲሁም ብዝኃ ሕይወት ዋነኛ የመስህብነት መገለጫ  ነው፡፡ በጥናቱ በተጨማሪ እንደተጠቆመው የጣራ ገዳም ደን በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሥፍራዎች ላይ ከሚገኙ ጥቂት የተፈጥሮ ደኖች መካከል አንዱ ነው፡፡ ደኑ የሚገኝበት ከፍታ ከባሕር ጠለል ከ2 ሺህ እስከ 2 ሺህ 800 ሜትር ይደርሳል፡፡

የጣራ ገዳም ደን በርካታ ሀገር በቀል እና ብርቅዬ የዕፅዋት ዝርያዎችን የያዘ በመሆኑ “የደን ባንክ” ተብሎ ይጠራል፡፡ በደኑ ውስጥ ከሚገኙት ዋነኛ የዛፍ ዝርያዎች ዋርካ፣ ወይራ፣ ጽድ፣ ዋንዛ፣ በለስ፣ ክትክታ፣ ሰሳ  ድግጣ፣ ጉመሮ፣ አጋም፣ ኮሽም፣ ለንቋጣ፣ ሰንሰል፣  አባሎ እና ብሳና ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ይህ ጥቅጥቅ  ደን ለዕፅዋት ብቻ ሳይሆን ለበርካታ የዱር እንስሳት እና ወፎች  መጠለያም ነው፡፡ በደኑ ውስጥ ነብር፣ ዝንጀሮ፣ ጉሬዛ፣ ድኩላ፣ ሰስ፣ ጅብ፣ ቀበሮ፣  ከርከሮ፣ አነር፣ የሜዳ ፍየል፣ ጦጣ፣  እርያ (የዱር አሳማ)፣ ሽኮኮ፣ ጥንቸል፣ ሸለምጥማጥ፣ ሙጭልጭላ፣ ጃርት እና ሌሎች አጥቢ እንስሳት ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም የሀገር ውስጥ እና ስደተኛ ወፎች መናኸሪያ በመሆኑ ለወፍ ተመልካቾች ድንቅ የመስህብ ስፍራ ነው፡፡

ወደ ጣራ ገዳም የሚጓዝ ማንኛውም ሰው ሊያያቸው እና ሊያደንቃቸው የሚገቡ በርካታ ተፈጥሯዊ እንዲሁም ሰው ሠራሽ መስህቦች ይገኙበታል፡፡ የመጀመሪያው እና ዋነኛው በድንጋይ ቋጥኝ ሥር የሚገኘው የዋሻ እንድሪያስ ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ ዋሻው ውስጥ ለውስጥ እስከ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው እና እስከ ወይን ዋሻ ተክለ ሃይማኖት ገዳም እንደሚደርስ ይታመናል፡፡ በጥንት ዘመን የነበሩ አባቶች በእነዚህ ምስጢራዊ የዋሻ መንገዶች ውስጥ ለውስጥ በመጓዝ መንፈሳዊ አገልግሎት ይሰጡ ነበር፡፡ ጎብኚዎች በደኑ ውስጥ ንጹሕ አየር እያጣጣሙ፣ በወፎች ዝማሬ ዘና እያሉ እና የቅጠላ ቅጠሎችን መልካም መዓዛ እየሳቡ መጓዝ ይችላሉ፡፡

በገዳሙ ውስጥ የሚኖሩት ባሕታውያን እና መነኮሳት ሕይወት የገዳሙ ሌላው መልካም ገጽታ  ነው፡፡ በልዩ ልዩ የትምህርት ዓይነቶች ለምሳሌ በሥነ ሕይወት እና ተፈጥሮ ሳይንስ  የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ዓለማዊ ሕይወትን ትተው የመነኑ አባቶችን በገዳሙ ውስጥ ማግኘት የተለመደ ነው፡፡ እነዚህ አባቶች ተራ ልብስ ለብሰው የገዳሙን ደን ሲንከባከቡ እና እንጨት ሲያጓጉዙ ማየት ለሰው ልጅ ትሕትናን እና መንፈሳዊ ጥንካሬን የሚያስተምር ታላቅ ትዕይንት ነው፡፡

ጣራ ገዳም  በሀገር ውስጥ እና በውጭ  ጎብኚዎች ሊጎበኝ የሚገባው ታላቅ  መዳረሻ ነው፡፡ የጣራ ገዳም ደን ለምርምር እና ለትምህርት የሚውል ትልቅ የተፈጥሮ ሀብት ነው፡፡ የዕፅዋት እና የእንስሳት ተመራማሪዎች፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች እንዲሁም የታሪክ አጥኚዎች በርካታ ዕውቀትን የሚቀስሙበት ስፍራ ነው፡፡ ጣራ ገዳምን መጎብኘት ማለት መንፈስን ማደስ፣ ታሪክን ማወቅ እና ተፈጥሮን ማድነቅ ነው፡፡

 

በኢትዮጵያ የሚገኙ አምስት አስደናቂ ጥብቅ  ደኖች

  1. የሐረና ደን

የሐረና ደን በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ደቡባዊ ተዳፋት ላይ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ትላልቅ የተፈጥሮ ደኖች አንዱ ነው። በሻጋታ የተሸፈኑ ረዣዥም ዛፎች፣ ወደ ፏፏቴዎች የሚወስዱ በቀርከሃ  መሀል የሚያልፉ መንገዶች አሉት፡፡  ባለ ጥቁር ጎፈር አንበሳ፣ የባሌ ጦጣዎች እና ብርቅዬ ወፎች መገኛ ነው፡፡

  1. የመናገሻ ሱባ ደን

የመናገሻ ሱባ ደን ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በውጫጫ ተራራ አቅራቢያ ይገኛል፡፡ ከአሥራ አምስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በአዋጅ ሲጠበቅ የቆየ በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው የመንግሥት ጥብቅ ደን እንደሆነ ይታመናል። የአራት መቶ  ዓመታት ዕድሜ ያላቸው የፅድ እና የቀርከሃ ዛፎች ይገኙበታል፡፡ የመናገሻ ሱባ ደን  የሚኒሊክ ድኩላን ለመመልከት ተመራጭ ቦታ ነው። ቦታውን ተመራጭ የሚያደርገውም  ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት መገኘቱ፣ የተራራው ጫፍ ላይ ለመውጣት እና በተለይም በሳምንቱ መጨረሻ ሽርሽር ለማድረግ አመቺ መሆኑ ነው።

  1. የሸካ ደን

የሸካ ደን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሸካ ዞን ከ230 ሺህ ሄክታር  የሚልቅ ቦታ ሸፍኖ የሚገኝ የመስህብ ሀብት ነው፡፡ የሸካ ደን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና  የባሕል ድርጅት( ዩ.ኔ.ስ.ኮ.) በዓለም ቅርስነት ተመዝግቦ እንደሚገኝ ከዩኔስኮ ዶት ኦርግ ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡ የተራራ ቀርከሃዎች እንዲሁም ዝናባማ ደኖች፣ጥልቅ ሸለቆዎች፣ ንጹህ ረግረጋማ ቦታዎች እና  ፏፏቴዎች መገኛ ነው፡፡ የአካባቢው ማኅበረሰቦች የተፈጥሮ ማር እና ቅመማ ቅመሞችን ያመርቱበታል።

  1. የያዩ የጫካ ቡና

የያዩ የጫካ ቡና  በኢሉባቦር ዞን ይገኛል፡፡ የያዩ ጫካ የዱር አረቢካ ቡና ተጠብቆ የሚገኝበት ስፍራ ነው። ይህ ጥብቅ ስፍራ ከጫካ ቡናው በተጨማሪ ዋሻዎች እና ወንዞች ይገኙበታል፡፡ በተለይ ለቡና አፍቃሪዎች፣ በወንዞች ዳርቻ የደን ውስጥ ጉዞ ማድረግ ለሚያስደ ስታቸው ጎብኝዎች ምርጥ የመስህብ ስፍራ ነው፡፡

  1. የቦንጋ ደን

የቦንጋ ደን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ በሆነው ከፋ ዞን ይገኛል፡፡ የጥልቅ ሸለቆዎች እና የወንዞች፣ የረዣዥም ዛፎች መገኛ ነው፡፡ የቦንጋ ደን አስደናቂ ተራራማ መልክዓ ምድርን ይሸፍናል። የጫካው የላይኛው ክፍል ከ30 ሜትር በላይ ቁመት ባላቸው ትላልቅ ሀገር በቀል ዛፎች የተሞላ ነው። ደኑ በማኅበረሰብ መር የጥበቃ ቡድኖች በጥብቅ የሚጠበቅ በረዣዥም ዛፎች መካከል የእግር ጉዞ ለማድረግ፣ የቀርከሃ ዛፎችን ለመመርመር እና በማኅበረሰቡ በሚመሩ ጉዞዎች መሳተፍ ለሚፈልጉ ጎብኝዎች ተመራጭ የመስህብ ስፍራ ነው።

(  ቦረቦር ዘዳር አገር)

በኲር የመስከረም  18 ቀን 2019  ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here