ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ በታሪክ፣ በባህልና በሃይማኖታዊ እሴቶቿ ቀዳሚ ከሚባሉ ጥንታዊ ሀገራት አንዷ ናት። በየዓመቱ በመላው ኢትዮጵያ የሚከበሩ ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላት ከመንፈሳዊ ይዘታቸውና ከማህበራዊ ውበታቸው ባሻገር፣ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ የሚፈጥሩና ገቢ የሚያስገኙ እንዲሁም የሀገርን በጎ ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚገነቡ ዋነኛ መሣሪያዎች ናቸው። በተለይም በሀገራችን በዓለም የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰሱ ቅርሶች የተካተቱ በርካታ በዓላት ጎብኝዎችን በመሳብ የኢትዮጵያን ገጽታ በጉልህ እየቀየሩ ይገኛሉ።
በዓላት ከገቢ ምንጭነት ባሻገር ሰፊ የሥራ ዕድል ፈጣሪዎች ናቸው። በመስተንግዶው ዘርፍ ከሚፈጠሩ ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎች በተጨማሪ፤ ለባህል አልባሳት አምራቾች፣ ለሸማ ሠሪዎች፣ ለእደ-ጥበብ ባለሙያዎችና ለቅርጻ ቅርጽ ሠሪዎች ሰፊ የገበያ መድረክ ይከፍታሉ። በርካታ ሰዎችን በአንድነት የሚያሰባስቡት እነዚህ በዓላት የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ከማነቃቃታቸውም በላይ የግብርና ምርቶች ከአገልግሎት ዘርፉ ጋር ጠንካራ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ያደርጋሉ። በመጓጓዣ፣ በምግብ አቅርቦትና በንግድ ዘርፍ የሚፈጠረው የገንዘብ ዝውውር የበርካታ ዜጎችን የዕለት ተዕለት ኑሮም ይደግፋል።
በኢትዮጵያ የሚከበሩ በዓላት ጎብኝዎችን በመሳብ ከሚያስገኙት የገቢ ምንጭ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፤ ማኅበራዊ ትስስር ገጽታ የመገንባት አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እነዚህን በዓላት በሚዘግቡበት ወቅት ኢትዮጵያን የአብሮነት ተምሳሌት አድርገው ያስተዋውቃሉ። ይህ ክስተት ኢትዮጵያ ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በማጠናከር ለቀጣይ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትና ለቱሪዝም እድገት እንደ ነፃ ዓለም አቀፍ ማስታወቂያ ያገለግላል። በሀገራችን ኢትዮጵያ በተለይም በዩኔስኮ የተመዘገቡ መዳረሻዎች ለዚህ እንደማሳያ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ፣ ይህንን ግዙፍ ምጣኔ ሀብታዊ አቅም በተሟላ መልኩ ለመጠቀም የመሠረተ ልማት ክፍተቶችን መሙላት፣ ዲጂታል የክፍያና የቦታ ማስያዣ አገልግሎቶችን ማስፋፋት፣ እንዲሁም ጎብኝዎች ለበዓላት ብቻ መጥተው እንዳይመለሱ ቆይታቸውን የሚያራዝሙ የባህል ሳምንታትና ዐውደ ርዕዮች ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በቆይታቸው ድጋሚ እንዲመለሱ የሚያስችል አቀባበልና መልካም መስተንግዶ ያስፈልጋል፡፡
በዓለም ላይ በርካታ ሀገራት ምጣኔ ሀብታቸውን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፍተኛ ደረጃ በቱሪዝም ዘርፍ በሚገኝ ገቢ ላይ መስርተው ያስተዳድራሉ። በእነዚህ ሀገራት ቱሪዝም የጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ዋነኛ ምንጭ፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ እና ለሕዝባቸው ዋነኛ የሥራ እድል ፈጣሪ በመሆን እየተጠቀሙበት ይገኛል።
እነዚህ ሀገራት የተፈጥሮ ውበት፣ የባሕር ዳርቻዎች እና የቅንጦት መስተንግዶዎችን በመጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ ቱሪዝም መተዳደሪያቸውና ዋነኛ የገቢ ምንጫቸው ነው፡፡ አንዳንድ ሀገራት ታሪካዊ ቅርሶቻቸውን፣ ባህላቸውንና የተፈጥሮ ውበታቸውን በመጠቀም ከፍተኛ ገቢ ከቱሪዝም ያገኛሉ፡፡ በቱሪዝም ገቢ ላይ በእጅጉ ጥገኛ የሆኑ እና በዘርፉ ስኬታማ ከሆኑ ዋና ዋና ሀገራት መካከል በአፍሪካ ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ካላቸው ሀገራት አንዷ የሆነችው ሲሼልስ፣ ምጣኔ ሀብቷ ከ30% በላይ በቱሪዝም ላይ የተመሠረተ ነው። የአብዛኛው ሕዝብ የሥራ መስክ ከሆቴልና መስተንግዶ ጋር የተያያዘ ነው። ግብጽ በጥንታዊ ፒራሚዶቿና ቀይ ባሕር ዳርቻዎቿ፣ ሞሮኮ ደግሞ በታሪካዊ ከተሞቿና በሰሃራ በረሃ ቱሪዝም፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ በዱር እንስሳት እና በተፈጥሮ ፓርኮቻቸው የሚታወቁ ሲሆን ቱሪዝም ዋነኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጫቸው ነው። እንደ ዱባይ ዓይነት በረሃ ላይ የተገነቡ ሀገራት ደግሞ ከነዳጅ ጥገኝነት ለመውጣት በተከተሉት ስልት ዛሬ ላይ እጅግ ግዙፍ የንግድ፣ የመዝናኛ እና የመተላለፊያ /የትራንዚት/ ቱሪዝም መዳረሻ በመሆን ምጣሄ ሀብታቸውን ከቱሪዝም በሚገኝ ገቢ እየመሩ ይገኛሉ።
እነዚህ ሀገራት ስኬታማ ከሆኑባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል ቀልጣፋ የመሠረተ ልማት ዝርጋታና ደረጃቸውን የጠበቁ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎች፣ የመጓጓዣ አማራጮችና ሆቴሎች፣ ቀላል የቪዛ አሰጣጥ እንዲሁም የቀጥታ ቪዛ እና እንደ ደረሱ የሚሰጥ ቪዛ ማመቻቸት፣ ለጎብኝዎች አስተማማኝ የጸጥታ ዋስትና በመፍጠር ደኅንነትን እና ሰላምን ማረጋገጥ እንዲሁም ጥራት ያለው አገልግሎት እና በሀገራቸው የሚገኙ መስህቦችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ማስተዋወቅ ይጠቀሳሉ፡፡
እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን? ኢትዮጵያ በዩኔስኮ የተመዘገቡ በርካታ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ያሏት ቢሆንም፣ የቱሪዝም ዘርፉ ለጠቅላላ ሀገራዊ ምጣኔ ሀብቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እስካሁን ከእነዚህ ሀገራት አንጻር ዝቅተኛ ነው። መሠረተ ልማትን በማሟላት፣ ሰላምን በማስፈንና ዘርፉን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ ቱሪዝምን ዋነኛ የምጣኔ ሀብቱ ዕድገት መሪ ማድረግ ይቻላል። የበዓላቱን መንፈሳዊና ባህላዊ ይዘት ጠብቆ ከዘመናዊው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ጋር በቅንጅት ማስተሳሰር ከተቻለ፣ በዓላት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገት የሚያፋጥኑ ዘላቂ የምጣኔ ሀብት ማድረግ ይቻላል።
በኲር የመስከረም 18 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


