ጥበበኛው አፋር

0
62

በምድራችን እጅግ አስቸጋሪና ሞቃታማ ከሚባሉት ስፍራዎች አንዱ በሆነው የዳናኪል በረሃ ውስጥ የሰው ልጅ የስልጣኔ ታሪክ ካያቸው እጅግ አስገራሚ የመግባቢያ መንገዶች አንዱ በጥቅም ላይ ይውላል።

ይኸውም የአፋር ሕዝብ ለዘመናት የገነባው ጥንታዊና ሕያው የመረጃ መረብ የሆነው “ዳጉ” ነው።

ዳጉ ተራ ወሬ ማውራት ወይም የገጠር ጨዋታ አይደለም፤ ይልቁንም ሳተላይት፣ ኬብልና ኤሌክትሪክ በሌለበት ምድረ-በዳ ውስጥ መረጃን በፍጥነት የሚያስተላልፍ፣ የሐሰት ወሬን በሳይንሳዊ ትክክለኛነትን የሚያጣራ ተፈጥሯዊ የኮምዩኒኬሽን ኢንጂነሪንግ ነው። በአፋር ምድር መረጃ የቅንጦት ወሬ ሳይሆን በሞትና በሕይወት መካከል ያለውን ልዩነት የሚወስን የህልውና መሣሪያ ነው።

የኮምዩኒኬሽን ሳይንስ ዳጉን ሲመረምረው የሚያገኘው እውነታ ዘመናዊውን የኮምፒውተር ኔትወርክ አሰራር የሚያስደምም ነው።

በዘመናዊው የኮምፒውተር ሳይንስ ውስጥ ሁለት ሰርቨሮች መረጃ ከመለዋወጣቸው በፊት “ቲሲፒ ሀንድሼክ” የተባለ የማረጋገጫ ሂደት ያደርጋሉ። ዳጉ ልክ እንደዚሁ ነው። ሁለት አፋሮች በመንገድ ሲገናኙ በዘፈቀደ አያወሩም።

ሂደቱ የሚጀምረው በከፍተኛ ሥነ-ምግባርና አክብሮት በታጀበ ሰላምታ ነው። ቀጥሎም አንዳቸው የሌላኛውን ማንነት፣ የመጣበትን ጎሳና የጉዞውን አቅጣጫ የሚያረጋግጥ ጥብቅ የጥያቄና መልስ ሥርዓት ይከተላል።

ተመራማሪው ሞገስ እንዳለ እ.ኤ.አ. በ2013 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባቀረቡት “ዳጉ የአፋር ባህል ጠባቂው ከተግባቦት አንጻር” በተሰኘው ጥናታቸው እንዳረጋገጡት የዳጉ ሂደት በሦስት ጥብቅ ደረጃዎች የተከፈለ ሥርዓት አለው፦ የመጀመሪያው የመተዋወቅና የሰላምታ ማረጋገጫ፣ ሁለተኛው ዋናውና ተጨባጩ መረጃ የሚለዋወጡበት ፣ ሦስተኛው ደግሞ መረጃን አጠቃለው የመሰናበቻ  ሂደት ነው።

መረጃ የሚቀበለው ወገን ራሱን ዝቅ አድርጎ ያለ ምንም ጣልቃ-ገብነት ያዳምጣል፤ አያቋርጥም፣ አይከራከርም። ሰጪው ሃሳቡን ሙሉ በሙሉ ጨርሶ ሲያበቃ ብቻ ተቀባዩ የሰማውን መረጃ ደግሞ በማረጋገጥ የራሱን መረጃ ያጋራል።

ይሄ የኮምዩኒኬሽን ሊቃውንት አንድ ለአንድ የመረጃ ልውውጥ ንድፍ (P2P) ብለው የሚጠሩት ማዕከላዊ አገልጋይ የማይፈልግ፣ ራሱን በራሱ የሚያንቀሳቅስ ፍጹም የኔትወርክ አወቃቀር ነው።

ይህ የዳጉ አውታር በመረጃ ንድፈ-ሐሳብ አኳያ ሲተነተን እጅግ አስገራሚ ስልት አለው። እያንዳንዱ መንገደኛ አፋር በኔትወርክ ቋንቋ «ተንቀሳቃሽ ኖድ» (Mobile Node) ነው።

አንድ ሰው ከሰሜን ወደ ደቡብ ሲጓዝ ያገኘውን መረጃ ሁሉ ይዞ ይጓዛል፤ በየመንገዱ ከሚያገኛቸው ሌሎች ተጓዦች ጋር መረጃ ይለዋወጣል።

በዚህ ቅብብሎሽ አማካኝነት አንድ ወሳኝ ክስተት በበረሃው ውስጥ ሲፈጠር መረጃው በሰዓታት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ያቋርጣል።

ይህ ሂደት በዘመናዊው የኮምፒውተር ሳይንስ “ዲሌይ ቶለራንት ኔትወርኪንግ) ወይም መረብ በሌለበት አካባቢ መረጃን በመንገደኞች አማካኝነት የማስተላለፍ ስልት ተብሎ የሚታወቀውን ሳይንስ በሺህ ዓመታት የቀደመ ነው።

የአፋር ማኅበረሰብ መረጃን ሲያስተላልፍ የመረጃውን ምንጭ፣ የቀኑን፣ ሰዓት እና ያየውን ሰው ማንነት በጥብቅ መዝግቦ የሚያስተላልፍ በመሆኑ የሐሰት ወሬ ወደ መረቡ ውስጥ ገብቶ የመዛመት ዕድሉ ፍጹም ዜሮ ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በዓለም አቀፍ አንትሮፖሎጂስቶች የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያስረዱት ዳጉ ለአፋር ማኅበረሰብ የቅድመ ማስጠንቀቂያና የሰላም ጥበቃ ዋነኛ ምሰሶ ነው።

በዚያ አስከፊና ተለዋዋጭ በረሃ ውስጥ የዝናብ መዝነብ፣ የውኃ ጉድጓድ መገኘት፣ የበሽታ መከሰት ወይም የጠላት እንቅስቃሴ በደቂቃዎች ውስጥ በመቶዎች ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ለሚገኙ ወገኖች መዳረስ አለበት።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዳጉ የሚተላለፍ መረጃ ከ98 በመቶ በላይ እውነተኛ ነው። ይሄ እንዴት ሊሆን ቻለ? ዳጉ የሐሰት መረጃን የሚከላከል ኃይለኛ ማኅበራዊ መሠረት እና የሞራል  አጥር አለው።

አንድ አፋር በዳጉ ውስጥ ሆን ብሎ የሐሰት መረጃ ቢያስተላለፍ ከማኅበረሰቡ ይገለላል፤ ክብሩ ይገፈፋል፤ ለዘላለም ታማኝነቱን ያጣል። ይህ ጥብቅ ማኅበራዊ ተጠያቂነት የሐሰት ዜናን የማጣራት ወጪን ወደ ዜሮ ያወርደዋል።

ጉዳዩን ከነርቭ ሳይንስ አንፃር ስንመረምረው ደግሞ ይበልጥ አስደናቂ ሚስጥር ይገለጣል። በዘመናዊው ዓለም የስልክ ስክሪን እያየን የምናደርገው ንግግር የአንጎላችንን ትኩረት ሲበትነው ዳጉ ግን ጥልቅ የሆነ “የአንጎል ቅንጅት” ይጠይቃል።

የነርቭ ሳይንስ ተመራማሪዎች እንደሚሉት በዳጉ ወቅት የአፋር ተራኪና አድማጭ እርስ በእርስ የሚተያዩበት የዓይን ግንኙነት፣ የድምፅ ቅላጼ እና የሰውነት እንቅስቃሴ በአንጎላቸው ውስጥ ያሉትን  መልእክት አስተላላፊዎች (ሚረር ኒውሮኖች) በከፍተኛ ሁኔታ ያነቃቃቸዋል።

ይህ ሂደት መረጃው በአድማጩ አእምሮ ውስጥ በስሜት፣ በምስል እና በቦታ ትውስታ  ታትሞ እንዲቀመጥ ያደርጋል። በተጨማሪም በበረሃው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መረጃን በደቂቃዎች ውስጥ በትክክል የመያዝ ፍላጎት፣ የአንጎልን የትኩረት ሆርሞን (ኖሬፊንፍሬን) በማመንጨት የመረጃ ማስታወስ አቅምን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያጎለብተው የስነ-ልቦና ጥናቶች ያረጋግጣሉ።

ይህም እውነተኛ የሰው ልጅ የተፈጥሮ ተዓምር ነው። ጥንታዊው አፋራዊ ያለ ወረቀት እና ያለ ድምፅ መቅረጫ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ስም፣ የከብቶችን ብዛት፣ የአየር ሁኔታን እና የተጓዘበትን መንገድ በሙሉ በቃሉ የሚይዘው በዚህ አስደናቂ የአንጎል የትኩረት ምህንድስና አማካኝነት ነው።

የሚዲያ ሥነ-ምህዳር ጥናቶች ዳጉን “የሕዝብ ጋዜጠኝነት” ፍጹም ጥግ አድርገው ይወስዱታል። ዘመናዊው ሚዲያ መረጃን ለገበያ፣ ለፖለቲካ ትርፍ ወይም የሰዎችን ቀልብ ለመስረቅ ሲያውለው፣ በአፋር ምድር ግን መረጃ የጋራ ሰብዓዊ ሀብት ነው።

በኡፕሳላ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ በሆኑት ክብረአብ ወልደሚካኤል እ.ኤ.አ. በ2016 የተጠናው “ሀገር በቀል የተግባቦት ስርዐት ለዘላቂ ልማት_ጥናት በዳጉ ላይ” የተሰኘው ጥናት ዳጉ መረጃን እንደ የጋራ ማኅበረሰባዊ ሀብት በማሰራጨት ረገድ ያለውን ሚና ያብራራል።

መንገድ ላይ የተገናኘህን አላፊ አግዳሚ ዳጉ (መረጃ) መከልከል በባህሉ እንደ ከባድ ነውርና ግፍ ይቆጠራል። መረጃን መደበቅ ሕይወትን እንደ መከልከል ይቆጠራል። በመሆኑም መረጃ ያለ ምንም ሳንሱር፣ ያለ ምንም የገንዘብ ክፍያ እና ያለ አድልዎ በነፃነት ይፈሳል። እያንዳንዱ መንገደኛ ተዘዋዋሪ ጋዜጠኛ፣ እያንዳንዱ አድማጭ ደግሞ አርታዒ ነው።

የአፋር ዳጉ ያስመሰከረው ትልቁ ጥበብ ቴክኖሎጂ ሳይሆን የሰው ልጅ የሞራል ስነ-ምግባር እውነተኛውን የኮምዩኒኬሽን መረብ እንደሚፈጥር ነው።

እኛ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የምንገኝ የቴክኖሎጂ ባሪያዎች በፋይበር ኦፕቲክስ፣ በሳተላይትና በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ተከበን ሳለን በየቀኑ በሐሰት ዜና እና በስም ማጥፋት ውቅያኖስ ውስጥ እንሰጥማለን።

የሰው ልጅ በቢሊዮን ዶላሮች ኢንተርኔትን ገንብቶ እውነቱን ከውሸት መለየት አቅቶት በዲጂታል ትርምስ ውስጥ ሲሰምጥ አፋሮች ግን ሌላ ዘዴ አላቸው።

በጠራራ ፀሐይ በሚነደው በረሃ ውስጥ ያለ አንዲትም ሽቦ እውነት ብቻ የሚናገር፣ በማኅበረሰብ ፍቅር የተሳሰረና በዓለም ላይ ማንም ሊጠልፈው ወይም ሊያጠፋው የማይችል ድንቅ “ሕያው የሰው ልዕለ-ኮምፒውተር” ከሺህ ዓመታት በፊት አንብበው ገንብተዋል!

 

ማረፊያ

የአፋሮች አበባባል

ላንተ ማን ነገረህ? ላንተ የነገረህን ሰው ማን ነገረው?

እውነት (ወሬ) ሦስት ጊዜ ይሰማል / ይረጋገጣል፡፡

ዳጉን (ወሬውን) መናገር ለመንገደኛው ነው፤ መቀበል ደግሞ እዚያው ለቆየው/ለነዋሪው ነው፡፡

ፈጣሪ ከሁላችንም ይበልጣል፤ አንተ ደግሞ ከእኔ ትሻላለህ፡፡

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር የጥቅምት 9 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here