ፀረ በሽታ አምጪ ተህዋስያን መድሃኒት (አንቲባዮቲክስ) እየወሰዱ እና ከወሰዱ በኋላ ስኳርን በተለያዩ ይዘቶች ውስጥ አብዝቶ መመገብ ጐጂ ተህዋስያኑ ጐልብተው መድሃኒት እንዲላመዱ እንዲሁም ለምግብ መፈጨት እና በሽታ ለመቋቋም የሚያስችሉ ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋስያንን ሊያጠፋ እንደሚችል ሳይንስ ዴይሊ ድረ ገጽ ሰሞኑን አስነብቧል፡፡
ኤን ዋይ ዩ ግሮስማን የህክምና ትምህርት ቤት በመረጃ ምንጭነት እንዳስነበበው ፀረ በሽታ አምጪ ተህዋስያን መድሃኒት እየወሰዱ ስኳርን አብዝቶ መጠቀም ጐጂ ተህዋስያኑን መድሃኒት እንዲላመዱ ከማድረግ ባሻገር ጠቃሚ ረቂቅ ተህዋስያንን ተግባራት ያስተጓጉላል፡፡ በዚህም ጐጂዎቹ በሽታ አምጪ ተህዋስያን እንዲበራከቱ እና መድሃኒት እንዲላመዱ ማስቻሉን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
የተጠቀሰው ውጤት ላይ ለመድረስ ከከፍተኛ የጤና ተቋማት የተወጣጡ ተመራማሪዎች በ173 ሆስፒታሎች የሚገኙ ህሙማን የተመገቡትን ተከታትለው የረቂቅ ህዋሳት መገኛ በሆነው አንጀት ላይ የተከሰቱ ለውጦችንም ገምግመዋል፡፡ በግምገማቸውም ከህክምና በፊት ባሉት 48 ሰዓታት ውስጥ የተመገቡት የስኳር መጠን በጨመረ ቁጥር የጠቃሚ ረቂቅ ተህዋስያን ብዛት መቀነሱን መገንዘብ ችለዋል፡፡
በመጨረሻም ምርምሩን ባካሄደው ኤን ዋይ ዩ ላንጐን ተቋም “የማይክሮ ባዮሎጂ” የትምህርት ክፍል ረዳት ኘሮፌሰር ጆናስ ሹልተር ፀረ ተህዋስያን (አንቲባዮቲክስ) መድሃኒት ከመውሰድ በፊት እና በኋላ ባሉት 48 ሰዓታት የስኳር ይዘት ያለው ምግብን መቀነስ ግድ መሆኑን ነው ያሰመሩበት፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የጥቅምት 9 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም


