የአረጋውያን  እንክብካቤ እና የሀገራት ተሞክሮ

0
105

“የማምሻ ዕድሜ እና የትውልዱ ኃላፊነት” በሚል ርዕስ ባለፈው ዕትም አረጋዊያን የትኛውን የዕድሜ ክልል እንደሚያጠቃልል፣ ስለአበርክቷቸው፣ በአረጋዊነት ዘመናቸው ስለሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች እና ሊያገኙዋቸው ስለሚገቡ እንክብካቤዎች…ለንባብ አብቅተናል፡፡  ሀገራት ለአረጋውያን የተሻለ ዓለም የፈጠሩበት ስኬታማ ተሞክሯቸውን ደግሞ በቀጣይ ዕትም ለማዘጋጀት ቃል ገብተን ነበር፡፡ ቃላችን አክብረንም እንደሚከተለው አዘጋጅተነዋል፤ መልካም ንባብ!

ለአረጋውያን ልዩ ክብር መስጠት፣ መንከባከብ፣ ያላቸውን ዕውቀትና ልምድ ማክበር በብዙ የዓለም ሀገራት ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳንድ ሀገራት ይህንን ክብር በባህላቸው ብቻ ሳይሆን በሕግ፣ በኢኮኖሚ ድጋፍ፣ በጤና ሽፋን እና በማሕበራዊ አገልግሎቶች ደረጃ የተቀናጀ ስርዓት በመዘርጋት ለአረጋውያን ልዩ ትኩረት በመስጠት ይታወቃሉ፡፡

እንደ ሄልፕ ኤጅ ኢንተርናሽናል መረጃ ለአረጋውያን ልዩ ክብር እና እንክብካቤ ከሚሰጡ ሀገራት መካከልም የሚከተሉት ይገኙበታል፦

  1. ጃፓን:- ለአረጋውያን በሚሰጠው ክብርና በሚቀርበው ዘመናዊ የእንክብካቤ ስርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ በአርአያነት የምትጠቀስ ሀገር ናት፡፡ በጃፓን በየዓመቱ መስከረም ላይ የአረጋውያን ቀን (Keirō no Hi) በብሔራዊ ደረጃ ይከበራል፡፡ በዚሁ ቀን አረጋውያን ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና ይቸራቸዋል፡፡

ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎችም ሙሉ የቤት ውስጥ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል፡፡ ለአረጋውያን አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላት ወጭም በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ይሸፈናል፡፡ እንዲሁም አረጋውያንን የሚያግዙ የሮቦት ቴክኖሎጂዎች እና ብቸኝነትን የሚያስቀሩ የማሕበረሰብ ማዕከላት በስፋት ይገኛሉ፡፡

  1. ስካንዲቪያን ሀገራት (ኖርዌይ፣ ስዊድን እና ዴንማርክ):-

እነዚህ የሰሜን አውሮፓ ሀገራት አረጋውያንን በበቂ ሁኔታ በመንከባከብ ጤናማ  ሕይወት እንዲመሩ በማድረግ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ በእነዚህ ሀገራት አረጋውያን የኢኮኖሚ ችግር  እንዳይኖርባቸው ከፍተኛ የጡረታ ክፍያ እና ነፃ የሕክምና አገልግሎት ያገኛሉ፡፡

አረጋውያን ከለመዱት አካባቢና ከቤታቸው ሳይወጡ የሕክምና ባለሙያዎች እና ረዳቶች ወደ እነሱ በመሄድ ሙሉ እንክብካቤ ያደርጉላቸዋል፡፡ የሕዝብ መጓጓዣ፣ መንገድ እና ሕንፃዎች ለአረጋውያን እንቅስቃሴ ምቹ እንዲሆኑ ተደርገው የተገነቡ ናቸው፡፡

  1. ደቡብ ኮሪያ :-

በኮንፊሺየስ (Confucianism) ፍልስፍና መሠረት ዜጎች ወላጆቻቸውን ጨምሮ    ለማነኛውም አረጋውያን ታዛዥ መሆን እና ክብር መስጠት ዋና የሥነ ምግባር መለኪያ ነው፡፡ በቤተሰብ ውስጥ አረጋውያን ቃላቸው ትልቅ ቦታ አለው፡፡ የ60ኛ (Hwangab) እና 70ኛ (Gohi)ዓመት የልደት ቀናቸው በታላቅ ድምቀት ይከበራሉ፡፡ በተለይ ልጆች ወላጆቻቸውን የመንከባከብ   ኃላፊነት አለባቸው፡፡

በደቡብ ኮሪያ አረጋውያንን የሚያስተናግዱ ማሕበራዊ ማዕከላት (Gyeongnodang) በየአካባቢው የሚገኙ ሲሆን መሠረታዊ የጡረታ አበልና ነፃ የመጓጓዣ አገልግሎት ይሰጣቸዋል፡፡

  1. ቻይና፡-

በቻይና ለአረጋውያን የሚሰጠው ክብር ጥልቅ ባህላዊ መሠረት ያለው ሲሆን በሕግ ደረጃም የተደገፈ ነው፡፡ በቻይና ሕግ  ራሳቸውን የቻሉ ልጆች በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን በየጊዜው የመጎብኘት እና የመጠየቅ ሕጋዊ ግዴታ አለባቸው፡፡

  1. ሲንጋፖር (Singapore)

ሲንጋፖር የቤተሰብ ትስስርን ከመንግሥት ድጋፍ ጋር በማቀናጀት ለአረጋውያን ምቹ ሁኔታን ፈጥራለች፡፡ ወላጆች የራሳቸውን ሕይወት መምራት በማይችሉበት ጊዜ ልጆቻቸው የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው በሕግ የሚጠይቁበት አሠራር አለ፡፡

አረጋውያን ወላጆቻቸው በሚኖሩበት አቅራቢያ ወይም አብረው የሚኖሩ ልጆች የመኖሪያ ቤት ሲገዙ የመንሥስት ድጋፍ እና የግብር ቅናሽ ይደረግላቸዋል፡፡

  1. የሜዲትራኒያን እና የላቲን አሜሪካ ሀገራት

ለምሳሌ ጣሊያን፣ ግሪክ እና  ሜክሲኮ አረጋውያንን ወደ እንክብካቤ ማዕከላት ከመላክ ይልቅ በቤተሰብ ውስጥ አብሮ ማኖርን ይመርጣሉ፡፡ አያቶች፣ ወላጆች እና ልጆች በአንድ ቤት ወይም በአቅራቢያ የሚኖሩ ሲሆን አረጋውያን የቤተሰቡ አማካሪ እና አስተዳዳሪ ተደርገው ይታያሉ፡፡

አረጋውያን በየቀኑ በየአካባቢው ባሉ አደባባዮች ከጎረቤቶቻቸው ጋር የሚያወሩበት እና የሚጫወቱበት ንቁ ማሕበራዊ ሕይወት አላቸው፡፡

  1. የአፍሪካ ሀገራት እና ባህላዊ እሴቶች:- ኢትዮጵያን ጨምሮ በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት አረጋውያን የዕውቀት፣ የባህል እና የታሪክ ማዕከል ተደርገው ይወሰዳሉ፡፡

በአፍሪካ  አረጋውያን በሕብረተሰቡ ውስጥ አለመግባባቶች ሲፈጠሩ በሽማግሌዎች ምክር እና ዕርቅ ሰላም ያወርዳል፡፡

የታሪክ፣ የባህል እና የሥነ-ምግባር እሴቶችን ለቀጣዩ ትውልድ በማስተላለፍ ረገድም ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በኢትዮጵያ በእድር፣ በማሕበር እና በቤተሰብ መዋቅር ውስጥ አረጋውያን ቅድሚያ የሚሰጣቸው እና የሚከበሩ ናቸው፡፡

በአፍሪካ ደረጃ አረጋውያንን ለመደገፍ የተዘረጉ በርካታ ባህላዊ፣ ማኅበራዊ እና መንግሥታዊ የፖሊሲ ስልቶች አሉ፡፡ እነዚህ ተሞክሮዎች በተለይም የመንግሥት የፋይናንስ ዐቅም ውስን በሆነባቸው  ታዳጊ ሀገራት ውስጥ አረጋውያንን እንዴት በክብርና በደኅንነት መንከባከብ እንደሚቻል ለሌሎች ዓለም ሀገራት ጠቃሚ ትምህርት የሚሰጡ ናቸው፡፡

በብዙ የደቡብ እና ምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት  “እኔ ያለሁት እኛ ስላለን ነው!” የሚለውን የደቡብ አፍሪካውያን ጥንታዊ  የኡቡንቱ ፍልስፍና ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ አረጋውያንን መንከባከብ የቤተሰብ ብቻ ሳይሆን የጠቅላላው ማሕበረሰብ ኃላፊነት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

በበርካታ የምዕራባውያን ሀገራት አረጋውያንን ወደ አረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከላት (Nursing Homes) የመላክ ልማድ ሰፊ ቢሆንም በአፍሪካ ግን አረጋውያን ከቤተሰቦቻቸው ጋር አብረው እንዲኖሩ ይደረጋል፡፡ ይህም ብቸኝነት እና ድብርት እንዳይሰማቸው በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው፡፡

በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ አረጋውያን በወጣትነታቸው በመደበኛው የመንግሥትም ሆነ የግል ዘርፍ ውስጥ ባይሠሩ እንኳ በዕድሜያቸው መግፋት ብቻ ከመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ያገኛሉ፡፡ ለአብነትም በሞሪሸስ ከ60 ዓመት በላይ ለሆኑ ዜጎች በሙሉ ቀደም ሲል የጡረታ ክፍያ ባይከፍሉም እንኳ ሁለንተናዊ የጡረታ ክፍያ ትሰጣለች፡፡ ይህም አረጋውያንን ከድህነት በመታደግ ረገድ ለሌሎች ሀገራት ትልቅ ማሳያ መሆኗን ኢንተርናሽናል ሌበር ኦርጋናይዜሽን እና ሄልፕ ኤጅ ኢንተርናሽናል ላይ በ2022የወጡ ሪፖርቶች የመላክታሉ፡፡

እንደ ቦትስዋና፣ ናሚቢያ እና ሌሶቶ ያሉ የአፍሪካ ሀገራትም በተመሳሳይ መልኩ ዕድሜያቸው ለገፉ ዜጎቻቸው በሙሉ ወርሃዊ የገንዘብ ድጋፍ ያቀርባሉ፡፡ ይህም አረጋውያን በኢኮኖሚ በልጆቻቸው ላይ ብቻ ጥገኛ እንዳይሆኑ አስችሏቸዋል፡፡

የአፍሪካ ሕብረትም የአረጋውያንን መብት፣ ክብር እና እንክብካቤ ሕጋዊ መሠረት ለመስጠት ልዩ ፕሮቶኮል ያጸደቀ የመጀመሪያው አህጉራዊ ተቋም ነው፡፡ የአፍሪካ ሕዝብ ሰብአዊ መብቶች ቻርተር ፕሮቶኮል  ሀገራት አረጋውያንን ከጥቃት እንዲጠብቁ፣ የጤና እና የኢኮኖሚ ዋስትና እንዲሰጧቸው እና በውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ላይ እንዲሳተፉ የሚያስገድድ ዓለም አቀፍ ፕሮቶኮል ነው፡፡

በጥቅሉ ሲታይ ለአረጋውያን የሚደረግ እንክብካቤ የሰብአዊነት እና የማሕበረሰብ ጥንካሬ መለኪያ ነው፡፡ በጃፓን እና በስካንዲኔቪያን ሀገራት የሚታዩትን ዘመናዊ የሕግ፣ የቴክኖሎጂ እና የጤና ሽፋን ተሞክሮዎች ከአፍሪካ የኡቡንቱ እና የአብሮነት ባህላዊ እሴቶች ጋር ማቀናጀት ከተቻለ ለአረጋውያን የተሻለ፣ በክብር እና በደስታ የተሞላ ሕይወትን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ የታዳጊ ሀገራት መንግሥታትም በባህላዊ መንገድ ከሚያደርጉት ድጋፍ ጎን ለጎን የተጠናከረ የማሕበራዊ ዋስትና ፖሊሲ ሊዘረጉ ይገባል፡፡

መረጃ

በዓለም ላይ ከፍተኛ የአረጋውያን ቁጥር ያሏቸው ቀዳሚ ሀገራት ፦

  1. ጃፓን

ከጠቅላላ ሕዝቧ ውስጥ ከ29 በመቶ በላይ የሚሆኑት ዕድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ የሆኑ ናቸው፡፡

  1. ጣሊያን

በአውሮፓዊያኑ 2024/2025 መረጃዎች መሠረት ጣሊያን በአውሮፓ ውስጥ ከፍተኛ የአረጋውያን ቁጥር ያላት ሀገር ስትሆን ከጠቅላላ ሕዝቧ ውስጥ 24 በመቶ ገደማ የሚሆነውን ይይዛሉ፡፡

  1. ፊንላንድ

ከጠቅላላ ሕዝቧ ከ23 በመቶ በላይ አረጋውያን ናቸው፡፡ይህም ከሰሜን አውሮፓ ሀገራት በአረጋዊያን ቁጥር ቀዳሚ አድርጓታል፡፡

  1. ፖርቹጋል እና ግሪክ

ሁለቱም የደቡብ አውሮፓ ሀገራት ከ 22 በመቶ እስከ 23በመቶ የሚደርስ የአረጋውያን ምጣኔ አላቸው፡፡

  1. ጀርመን

የአውሮፓ ትልቁ የኢኮኖሚ ባለቤት የሆነችው ጀርመን ከ22በመቶ በላይ አረጋዊ ሕዝብ አላት፡፡

  1. ክሮኤሺያ እና ቡልጋሪያ

የምሥራቅ/ደቡብ-ምሥራቅ አውሮፓ ሀገራት የአረጋውያን ቁጥር ከ21በመቶ እስከ 22በመቶ ይደርሳል፡፡

ምንጭ፦ UN World Population Prospects & Eurostat Data)

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር የጥቅምት 16 ቀን 2019 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here