በአማራ ክልል የተከሰተው ግጭት አርሶ
አደሩን ጎድቶታል። የተፈጠረው ግጭት
በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች መሠረታዊ
አገልግሎቶችን አስተጓጉሏል:: በተለይም
በግብርናው ዘርፍ ከዘር ወቅት ጀምሮ ሰብል
እስከሚሰበሰብበት ድረስ የቀጠለ በመሆኑ አርሶ
አደሮችን ለጉዳት ዳርጓል::
ይህ ደግሞ በአርሶ አደሩ ብቻ የሚቆም
ሳይሆን ሁሉንም ዜጎች ለከፋ ጉዳት መዳረጉ
አይቀርም። እየከፋ ለሚሄደው የኑሮ ውድነትም
መሠረታዊ ምክንያት ነው።
ክልሉ ከፍተኛ ምርት ከሚመረትባቸው
የሀገሪቱ ክፍሎች አንዱ ሲሆን እንደ ሀገርም
ከ40 በመቶ በላይ አጠቃላይ ድርሻን ይሸፍናል።
በክልሉ የተከሰተው ቀውስ ግን በግብርና
ሥራው ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል:: እንደ
ሀገርም ሊደርስ የሚችለው ጉዳት ከባድ ነው።
የተከሰተው አለመረጋጋት ከዘር ወቅት ጀምሮ
የአፈር ማዳበሪያ በሚቀርብበት ጊዜ ስለነበር
ችግሩ የጐላ መሆኑን በኲር ያነጋገራቸው አርሶ
አደሮች ተናግረዋል:: በክልሉ ትርፍ አምራች
ከሆኑ አካባቢዎች መካከል ምዕራብ ጐጃም ዞን
አንዱ ነው:: በፍኖተ ሰላም ዙሪያ ገራይ ቀበሌ
ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር በቀለ አይሸሽም በቆሎ፣
ጤፍ፣ በርበሬ፣ ስንዴ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም እና
ሸንኮራ አገዳ በማልማት ከራሳቸው አልፈው
ለገበያ ያቀርቡ እንደነበር አጫውተውናል::
በስልክ ያደረሱን መረጃ እንደሚያመለክተው
የደረሱ ሰብሎችን ሰብስበው የበጋ ሰብሎችን
ለማምረትም የግብአት አቅርቦት ፈተና
ሆኖባቸዋል።