በአራቱም የዓለም ማዕዘን የሚገኙ የእግር ኳስ ተጫዋቾች የብቃታቸው ጫፍ ሲደርሱ ወደ አውሮፓ ታላላቅ ሊጎች አቅንተው መጫወት ህልማቸው እንደሆነ የማይካድ ሀቅ ነው። ህልማቸውን እውን ለማድረግም በትልቅ ተነሳሽነት እና ወኔ ጠንክረው በመሥራት ለውጤት ሲበቁ ተመልክተናል።
ከአህጉራችን አፍሪካም ስፖርቱ የተሻለ ባደገባቸው በተለይ የሰሜኑ፣ የምዕራቡ፣ የደቡቡ የአፍሪካ ክፍል ሀገራት፣ እግር ኳስ ተጫዋቾች ህልማችን ነው ወደሚሉት የአውሮፓ ምድር አቅንተው ታላላቅ ሊጎችን ሲቀላቀሉ መመልከት እንግዳ አይደለም።
ኢትዮጵያውያን እና ብዙዎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ግን ብዙ ጊዜ ለዚህ የታደሉ አይደሉም። በሀገራችን ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሻግሮ በሌሎች የአፍሪካ እና የአረብ ሊጎች የሚጫወቱ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ከታዩ አሁን ድረስ እንደብርቅ ይታያሉ። ብርቅም ቢሆን ከቅርብ ዓመታት በተሻለ በርካታ ቁጥር ያላቸው የእግር ኳስ ተጫዋቾች በቀደሙት ጊዜያት ተጫውተው አሳልፈዋል። ተሳክቶላቸው ወደ አውሮፓ ተጉዘው የተጫወቱ ጥቂቶች ቢሆኑም በአረብ እና በአፍሪካ ሀገራት የተጫወቱ ግን ብዙዎች ናቸው።
አሁን ከአቡበከር ናስር ውጪ ከሀገር ወጥቶ በሌሎቹ ሊጎች የሚጫወት ተጨማሪ ተጫዋች ኢትዮጵያ የላትም። የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተጫዋች ቢኒያም በላይ ለሙከራ ወደ ስዊድን መጓዙን ሳንዘነጋ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ወደ አውሮፓ አቅንቶ በአውሮፓ ሊግ የተጫወተ የመጨረሻው ተጫዋች ጋቶች ፓኖም ነው።
የወቅቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የብሄራዊ ቡድኑ አማካኝ በሩሲያ የመጀመሪያ ዲቪዚዮን በሚጫወተው ክለብ አንዚ ማካቻካላ ተጫውቶ አሳልፏል። ፍቅሩ ተፈራ፣ተስፋዬ ታፈሰ ፣ ኡመድ ኡክሪን የመሳሰሉት ደግሞ በአረብ ሊጎች ተጫውተው ካሳለፉ ተጫዋቾች መካከል ይገኙበታል። ይድነቃቸው ተሰማ፣ ሽመልስ በቀለ፤ደጉ ደበበ፣ ፉአድ ኢብራሂም፣ ሳላህዲን ሰኢድ ፣እንዲሁም ጌታነህ ከበደን የመሳሰሉትም በአፍሪካ ሊግ ከተጫወቱት ኢትዮጵያውያን መካከል ይጠቀሳሉ።
የአፍሪካ የእግር ኳስ አባት የሚባሉት ስመጥሩ ይድነቃቸው ተሰማ ከሀገር ወጥቶ በሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት ሊጎች በመጫወት ቀዳሚ ኢትዮጵያዊ ናቸው። አሁን ላይ የመጨረሻው ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውጪ እየተጫወተ የሚገኘው ደግሞ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡናው ተጫዋች አቡበከር ናስር ብቻ ነው።
አጥቂው አቡበከር ናስር በደቡብ ፍሪካው ክለብ ማሚሎዲ ሰንዳውንስ እየተጫወተ ይገኛል። በዜግነት ኢትዮጵያውያን ያልሆኑ ነገር ግን የዘር ሐረጋቸው ከኢትዮጵያ የሚመዘዝ በአውሮፓም፣ በአሜሪካም የሚጫወቱ እና በአንድ ወቅት ለብሄራዊ ቡድኑ ጥሪ የተደረገላቸውን ጨምሮ በርካታ ተጫዋቾች እንዳሉ ግን መዘንጋት የለበትም። በእግር ኳሱ ዝነኛ እንደሆኑት የአፍሪካ ሀገሮችም ባይሆን ልክ እንደ ሌሎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ፣ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ከሀገራቸው ፕሪሚየር ሊግ መሻገር ለምን ተሳናቸው ? የበርካቶቹ ጥያቄ ነው።
አሚኮ በኩር ጋዜጣ ዝግጅትም በዚህ ጉዳይ ላይ ከዓለም አቀፉ ዳኛ ኃይለእየሱስ ባዘዘው (ዶ.ር) ጋር ቆይታ አድርጋለች። ኃይለእየሱስ ባዘዘው(ዶ.ር) ዓለም አቀፍ ዳኛ ሲሆኑ በርካታ ዓለም እና አህጉር አቀፍ ጨዋታዎችን መርተዋል፤ አሁንም እየመሩ ነው:: በሀገራችንም በላይኛው የሊግ እርከን ጨዋታዎችን እየመሩ ሲሆን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሰፖርት ሳይንስ አካዳሚ በመምህርነትም እያገለገሉ ነው::ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተጫዋቾች ለምን ከሀገር ወጥተው መጫወት እንደተሳናቸው ዓለማቀፉ ዳኛ ኃይለእየሱስ ባዘዘው(ዶ.ር) እንደዚህ ያብራራሉ::
ኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ ተጫዋቾች ከሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት ተጫዋቾች በንፅፅር በግል ክህሎታቸው የተሻሉ ናቸው ተብሎ ይታመናል።ነገር ግን ዘርፉ የሚጠይቀውን የአካል ብቃት ጥንካሬ(physical fitness) የሚያሟሉ አይደሉም። በአካል ብቃቱ ደካማ መሆናቸው ደግሞ ከሀገር ውጪ እንዳይጫወቱ መሰናክል እንደሆነባቸው አንደኛው ምክንያት መሆኑን ዓለም አቀፉ ዳኛ ይናገራሉ።
መሰረታዊ የእግር ኳስ ክህሎት የሚባሉትን ኳስ መቀበል ፣ መግፋት እና ማቀበል ብቻ ለአንድ የእግር ኳስ ተጫዋች በቂ አለመሆኑን የጠቀሱት ዓለም አቀፉ ዳኛ ጠንካራ የአካል ብቃት ለእግር ኳስ ተጫዋቾች አስፈላጊ መሆኑንም ያስረዳሉ።
የኛ ሀገር ተጫዋቾች ከሌሎቹ ሀገራት ተጫዋቾች ጋር ሲነፃፀሩ ባላቸው የአካል ብቃት ጥንካሬ እና ፍጥነት በልጠው አለመገኝታቸው መልማዮቹ፣ ወኪሎቹ ዓይናቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንዳያዞሩ አድርጓቸዋል። የታክቲካል አረዳዳቸው ደካማ መሆኑም ሌላኛው ትልቁ እና መሰረታዊ ምክንያት እንደሆነ ዓለም አቀፉ ዳኛ ያስረዳሉ። የኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ ባህል እና ፍልስፍና ልክ እንደ ባርሴሎና ፣የስፔን ብሄራዊ ቡድን እና ማንቸስተር ሲቲ እንደ ሆነ በተደጋጋሚ ይነገራል። ተጫዋቾች የሚሰጣቸውን ሚና እና ንድፈ ሀሳብ ፣ እንዲተገበር የሚፈለገውን የጨዋታ ስልት ተገንዝቦ ተግባራዊ የማድረጋቸው አቅም ደካማ ነው::
አንድን ቡድን ሜዳ ላይ የጎደለውን ተገንዝቦ ጉድለቱን ለመሙላት በተጫዋቾች ዘንድ የፍላጎት ብቻ ሳይሆን የእውቀት ውስንነትም ይስተዋላል።
“ከአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ክለብ አሰልጣኞች እና ዳኞች ጋር ስለ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች አውርተናል።የሚነግሩኝም በግል ክህሎታቸው ጎበዞች እንደሆኑ ነገር ግን ታክቲካል አረዳዳቸው በጣም ደካማ ስለመሆናቸው ይነግሩኛል። ታክቲክ ምን እንደሆነም ግንዛቤ የላቸውም።” መቼ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተገንዝበው እግር ኳስን የመጫወት አቅማቸው ደካማ ጭምር ነው ተብሏል::
ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች የማሸነፍ ስነልቦናቸው ደካማ ነው፤ከቡድን ሥራ ይልቅ ለግል ሥራ የሚጨነቁ እና ሜዳ ላይ ኳስ ሲነጠቁ የመደንገጥ እና ተስፋ የመቁረጥ ዝንባሌም ይታይባቸዋል። በተሸናፊ ቡድን ውስጥ ጎልቶ የሚወጣ ተጫዋች አለመመልከታችን ለዚህ አንዱ ማሳያ መሆኑንም ነው ኃይለእየሱስ ባዘዘው (ዶር) የተናገሩት። ይህም ተጫዋቾቹ ከሀገራቸው ወጥተው እንዳይጫወቱ የሚያደርጋቸው ሌላኛው መንስኤ ነው ያሉት። ተጫዋቾቹ በሙያቸው ብቁ ባለመሆናቸው ከዳኞች፣ከተጋጣሚ ቡድን እና ከደጋፊዎቹ ጋር አላስፈላጊ እሰጥ አገባ ውስጥ ሲገቡ ይስተዋላል። ይህ ደግሞ በፈላጊ ክለቦቻቸው ዓይን ውስጥ እንዳይገቡ እና ተመራጭ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በቀጥታ የቴሌቪዥን መስኮት በዲኤስቲቪ (DSTV) መተላለፍ ከጀመረ ዘንድሮ አራተኛ ዓመቱን ይዟል።ጨዋታዎች በቀጥታ ስርጭት መተላለፋቸው ለተጫዋቾች ብዙ ትሩፋቶችን ይዞ ይመጣል ቢባልም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከአቡበከር ናስር ውጪ እድሉን ያገኝ ተጫዋች ግን የለም። ብዙዎቹም ምንድነው ምክንያቱ? ሲሉ ይደመጣሉ። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ደካማ መሆኑ ተጫዋቾች በሌሎቹ ዘንድ ተፈላጊ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል! ለጥያቄው ምላሽ ይሆናል።
በዓለም ላይ ያሉት የእግር ኳስ ወኪሎች፣መልማዮች ከኢትዮጵያውያን ክለቦች እና አካዳሚዎች ጋር ያላቸው ጥምረት አነስተኛ መሆኑም፣ ባለተሰጥኦ እና ተስፈኛ የሚባሉት ተጫዋቾችም ከሀገር ወጥተው እድሉን እንዳያገኙ አድርጓቸዋል።
ታዲያ መፍትሄው ምንድ ነው?
ተጫዋቾቹ ያሉበትን ወቅታዊ አቋም በመገንዘብ ራሳቸውን ለማሻሻል ጠንክረው መሥራት አለባቸው ።የታክቲክ አረዳዳቸውን የቴክኒክ ክህሎታቸውን ፣የአካል ብቃት ጥንካሬያቸውን ማጎልበትም ይጠበቅባቸዋል፤ የዓለም አቀፉ ዳኛ ኃይለእየሱስ ባዘዘው(ዶ.ር) አስተያየት ነው። በእግር ኳስ ወኪሎች፣አሰልጣኞች እና መልማዮች ዓይን የሚገቡ ተስፈኛ ተጫዋቾች እንዲኖሩ ታዳጊዎች የሚሰለጥኑበት መንገድ የተሻለ ሳይንሳዊ እና በተግባር የተደገፈ መሆን አለበትም የዓለም አቀፉ ዳኛ ምክረ ሀሳብ ነው።
ኢትዮጵያውያን እግር ኳስ ተጫዋቾች ከሀገር ወጥተው መጫወት የመጨረሻ ግባቸው ሊሆን ባይገባም ፋይዳው ግን ከፍ ያለ ነው። ታዲጊ የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ያነሳሳል፣ እድሉን ያገኝው ተጫዋችም ልምድ እንዲያገኝ ይጋብዛል።ከዚህ ባለፈም ምጣኔ ሀብታዊ ፋይዳውም ላቅ ያለ ነው። ለሀገራችን የውጪ ምንዛሬ ከማምጣት ጀምሮ ተጫዋቾች ራሳቸውን ፣ቤተሰባቸውን፣አልፎ ተርፎም ሀገራቸውን የሚጠቅሙበት እድል ይፈጠራል::
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ኅዳር 24 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም