አካል ጉዳት ያልበገራቸዉ

0
207

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ማግስት የጀርመኑ ናዚ ሂትለር በአይሁዶች ላይ አሰቃቂ የዘር ፍጅት ማድረሱን የታሪክ ስንክሳር ያስረዳል። በተአምር ከዚህ ሞት ያመለጡ እና አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን ለመንከባከብ እና ቀሪ ዘመናቸውን በፍስሐ እንዲያሳልፉ ለማድረግ በ1948 እ.አ.አ እነዚህ አካል ጉዳተኞች በስፖርቱ እንዲሳተፉ ተደርጓል። ከአስራ ሁለት ዓመታት በኋላ በተደረገው የሮም ኦሎምፒክ ደግሞ ጎን ለጎን የፓራለምፒክ ውድድር ተጀምሯል። እነሆ እስካሁንም አስራ ስድስት ምዕራፎች ተደርገዋል። እ.አ.አ ከ1960ው የሮም ኦሎምፒክ ጀምሮ አህጉራችን አፍሪካም እየተሳተፈች ትገኛለች። አፍሪካ በ1994 እ.አ.አ በጃፓን ቶኪዮ በተደረገው ፓራለምፒክ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ በውኃ ዋና ፣በሩጫ ፣በክብደት ማንሳት እና በዊልቸር ቴኒስ መሳተፏን ታሪክ ያወሳል። ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ባስቆጠረው መድረክ የአህጉራችንን ስም ያስጠሩ በርካታ አትሌቶች በመድረኩ ደምቀዋል። በፓሪሱ የፓራለምፒክ ውድድርም አፍሪካውያኖቹ እንደሚጠበቁ መረጃው ያመለክታል። ባለፉት አስራ ስድስት የፓራለምፒክ መድረኮች ግንባር ቀደም አካል ጉዳተኛ ስፖርተኞችን በዛሬው የስፖርት አምዳችን እንዳስሳለን።
ደቡብ አፍሪካዊው አካል ጉዳተኛ ዋናተኛ ኪቪን ፓውል በፓራለምፒክ ታሪክ ስማቸው ከፍ ብሎ ከሚነሱ አፍሪካውያን አትሌቶች መካከል ይጠቀሳል። የሃያ ዘጠኝ ዓመቱ የውኃ ዋናተኛ በመድረኩ በተወዳደረበት መቶ ሜትር ደረት ቀዘፋ የወርቅ ሜዳሊያን ማስገኘቱ አይዘነጋም። ፓውል በወቅቱ ተወዳዳሪዎቹን ለማሸነፍ የተጠቀመበትን የደረት ቀዘፋ ዘዴ የስፖርት ቤተሰቡ አይዘነጋውም። ደቡብ አፍሪካዊው ዋናተኛ በተወዳደረባቸው መድረኮች ሁሉ በበላይነት በማጠናቀቅ የሚታወቅ ሲሆን በስፖርት ህይወቱ ሁለት ጊዜ ብቻ ነው ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው። ይህ ብርቱ ስፖርተኛ አካል ጉዳተኛ ካልሆኑት ጋርም ተወዳድሮ ማሸነፍ እንደሚችል በተደጋጋሚ ሲናገር ተደምጧል።
አልጀሪያዊው አብደላጢፍ ባቃ ከአፍሪካውያን ስመ ጥር አካል ጉዳተኛ አትሌቶች መካከል ስሙ ይነሳል። አትሌት አብደላጢፍ ዓይነ ስውር ሲሆን በስምንት መቶ እና አንድ ሺህ አምስት መቶ ሜትር ጭላንጭል በተለያዩ መድረኮች ተሳትፏል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በተወዳደረበት እ.አ.አ የ2012ቱ የለንደን ፓራለምፒክ ውድድር በሁለቱ ርቀቶች የወርቅ ሜዳሊያን በመውሰድ ታሪክ ሠርቷል። እ.አ.አ በ2016ቱ የሪዮ ፓራለምፒክም ሁለት ወርቅ ለአልጀሪያ ማበርከቱ ይታወሳል።
ሌላኛው ደቡብ አፍሪካዊ ብስክሌተኛ ዱ ፕሪዝ በቶኪዮ ፓራለምፒክ የብስክሌት ውድድር ውጤታማ እንደነበር አይዘነጋም። ለብስክሌት ስፖርት ልዩ ፍቅር የነበረው ዱፕሪዝ ገና በልጅነቱ በኦሎምፒክ መድረክ የመሳተፍ ህልም እንደነበረው ያስታውሳል። ነገር ግን በስድስት ዓመቱ በህመም ምክንያት የግራ ዓይኑን አጥቷል። የማይሰበረው ሰው ይህ ሳይበግረው በኦሎምፒክ የመሳተፍ ህልሙ ቢደናቀፍም ወደ ፓራለምፒክ ፊቱን በማዞር ስኬታማ መሆን ችሏል። ለመጀመሪያ ጊዜም በለንደን ፓራለምፒክ ተሳትፏል። እ.አ.አ ከ2012ቱ የለንደን ጨዋታዎች በኋላ የዚህ ደቡብ አፍሪካዊ አካል ጉዳተኛ ለስፖርቱ ያለው ፍላጎት እና ፍቅር ጨምሯል። በዓለም የፓራ ሻምፒዮናም ውጤታማ እንደነበር አይዘነጋም። የፓሪሱ መድረክ የመጨረሻው እንደሆነ የተናገረው ዱፕሪዝ የስፖርት ህይወቱን በውጤት በማጀብ ማጠናቀቅ እንደሚፈልግም ተናግሯል። በ2024ቱ የፓራለምፒክ ውድድር በፓራ ሳይክል ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል አንዱ ነው።
አካል ጉዳተኞች ካሰቡበት የትኛውም ቦታ መድረስ እንደሚችሉ ያሳዩ እና በፓራ ስፖርት ምልክት ከሆኑ ሰዎች መካከል አባስ ካሪሚ አንዱ ነው። የ24 ዓመቱ ዋናተኛ ያለ እጅ በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል ነበር የተወለደው። በወቅቱ በሀገሪቱ በነበረው አለመረጋጋትም 16 ዓመት እስኪሞላው በአራት የተለያዩ የስደተኛ መጠሊያ ጣቢያዎች ነው ያደገው። ቤተሰቦቹ ከሚያሳልፉት አሰቃቂ ህይወት በላይ የታዳጊው አባስ የወደፊት ዕጣ ፋንታ ያሳስባቸው እንደነበረ በቃለ ምልልሱ ተናግሯል። በመጨረሻ ቤተሰቦቹ በስደት ወደ አሜሪካ ካመሩ በኋላ ሁሉም ነገር ተቀይሯል።
የታዳጊው አባስ ካሪሚ ዕጣ ፋንታም ተቀይሯል። ወንድሙ ባስገነባው የመዋኛ ገንዳ የውሃ ዋና ስፖርት እንደተለማመደ የተናገረው ዋናተኛው በወቅቱ ድጋሚ የተወለደ ያህል እንደተሰማው አባስ ይናገራል። በመጨረሻም በዓለም ፓራ ሻምፒዮና እና ፓራለምፒክ ውጤታማ እስከመሆን ደርሷል። በ2024ቱ የፓሪስ ፓራለምፒክ ይደምቃሉ ተብለው ከሚጠበቁት መካከል ይጠቀሳል።
የወራት እድሜ በቀሩት የፓሪሱ ውድድር ኦሎምፒክ ዶት ኮም (Olympics.com) ይደምቃሉ ብሎ ግምት ከሰጣቸው ስፖርተኞች መካከል የውሃ ዋና ስፖርት ተወዳዳሪዋ ሊና ስሚዝ አንዷ ነች። አሜሪካዊቷ ዋናተኛ በቶኪዮ ፓራለምፒክ የብር ሜዳሊያን እና በ2022ቱ የዓለም ፓራ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷ አይዘነጋም። ሊና ስሚዝ በቅርቡ በማህበራዊ የትሥስር ገጿ ባሰፈረችው መልዕክት ለፓሪሱ ፓራለምፒክ ውድድር በደንብ እየተዘጋጀች መሆኗን አስፍራለች።
የመም እና የሜዳ ተግባራት ንግስቷ ዲያ ያንግ ካርዶክም በአጭር ርቀት ጭላንጭል የስፖርት ቤተሰቡ ማየት ከሚጓጓላቸው አትሌቶች መካከል አንዷ ነች። ካርዶክ ከስምንት ዓመታት በፊት ከፍተኛ ድባቴ ውስጥ ገብታ እንደነበረ በታሪክ ማህደሯ ሰፍሯል። በወቅቱም ራሷን ለማጥፋት ሞክራ በቤተሰቦቿ እና በጓደኞቿ እርዳታ መትረፏ ተሰምቷል። በ2016ቱ የሪዮ ፓራለምፒክ የመጀመሪያ ውድድሯን ያደረገች ሲሆን በቶኪዮ ፓራለምፒክ ደግሞ በመቶ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያን አግኝታለች። ዘንድሮም በፓሪሱ የአትሌቲክስ ድግስ ተጠባቂ ሆናለች።
አሜሪካውያኖቹ የመም እና የሜዳ ተግባር ስፖርተኛዋ ኒክ ማይሀ ፣ሌላኛው አሜሪካዊት ብስክሌተኛ ኦስካና ማስተርስ የማይበገሩ ድንቅ የፓራ ሴት ስፖርተኞቹ ሲሆኑ በፓሪሱ መድረክም የሚጠበቁ መሆናቸው ተዘግቧል።
የ2024ቱ የፓራለምፒክ ውድድር የፊታችን ነሐሴ ወር ይጀመራል።ለዚህ ግዙፍ የአትሌቲክስ መድረክ ፈረንሳይ ድግሱን አሰናድታ መጨረሷን ከወዲሁ በመገናኛ ብዙኃኗ በኩል አስታውቃለች። ዘንድሮ ከአራት ሺህ አራት መቶ አትሌቶች በላይ እንደሚሳተፉ መረጃዎች አመልክተዋል። የአትሌቲክስ ድግሱ ከዚህ በፊት ከነበረው በተሻለ ውድድሩን ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ሥራ መሠራቱን የአዘጋጇ ሀገር ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን ተናግሯል። ስፖርተኞቹ ለአስራ ሁለት ቀናት በሚኖራቸው የፓሪስ ቆይታ በምቾት እንዲያሳልፉ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዩሮ በላይ ገንዝብ በማውጣት መሰረተ ልማቶች ተገንብተዋል። በሀገሪቱ ከአስራ ሁለት ሚሊዮን በላይ አካል ጉዳተኛ መኖሩ ፓሪስ ጉዳዩን ትኩረት ሰጥታ እንድትሰራ ማድረጓን ጋዜጣው አስነብቧል።
ይህ የአትሌቲክስ መድረክ ከስፖርት ሁነት ባለፈ አካል ጉዳተኞች ራሳቸውን የሚያሳዩበት ፣የማህበረሰቡን እና የግለሰቦችን አመለካከት የሚቀየሩበት፣ በስፖርቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ እና ወደ አደባባይ እንዲይወጡ የሚያደርግ ነው።
በኛም ሀገር ምንም እንኳን አካል ጉዳተኛ የሆኑ ስፖርተኞች በትላልቅ የውድድር መድረኮች ሳይቀር ውጤታማ ቢሆኑም ለስፖርተኞቹም ሆነ ለስፖርቱ የተሰጠው ትኩረት ግን አነስተኛ ነው፡፡ሀገራት ለአካል ጉዳተኞቻቸው መልካም አጋጣሚዎችን በሚፈጥሩበት ዓለም ውስጥ እየኖርን ለአካል ጉዳተኞቻችን ትኩረት መንፈጋችን ከስህተትም የገዘፈ ስህተት ነው፡፡
ኦሎምፒክ ዶት ኮም፣ አፍሪካ ኒውስን እና ኢንሳይድ ዘጌምን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል፡፡
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር ታኀሣሥ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም – https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here