ከአፍሪካ አህጉር ብሎም ከዓለም ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ የተጓዘ የሀገረ
መንግሥት ግንባታ ታሪክ ባለቤት ናት። ግዛታዊ አንድነቷን፣ ሉዓላዊነቷን፣ ነፃነቷን እና
ሀገራዊ ክብሯን በሕዝቧ ደም እና ላብ አስጠብቃም ቆይታለች። ይህም ኢትዮጵያ ከራሷ
አልፋ የአፍሪካውያን እና የጭቁን ሀገራት እና ሕዝቦች የነፃነት ፋናወጊ እንድትሆን መንገድ
ጠርጓል። አፍሪካዊ ተቋማት እንዲዋቀሩ፣ የዓለም መንግሥታት ማህበር እንዲመሰረት፣
በሀገራት መካከል ጦርነት ሲነሳ (በማሸማገል) ዓለምአቀፍ ሞገስን የተቀናጀች ሀገርም ናት።
ይህ ታሪካዊ ሞገስ ግን ቀስ እያለ መፈተኑ አልቀረም። የዚህ ፈተና ምንጮችም
በመሰረታዊነት ሁለት ናቸው። የመጀመሪያው የዕርስ በዕርስ ጦርነት መኖር እና ይሄን
ተከትሎም ድህነት እና ሗላቀርነት መኖሩ ነው። በ21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን ዓለም አይቶት
የማያውቅን አስከፊ ጦርነት ባለፉት ዓመታት ውስጥ ያደረገችው ኢትዮጵያ ፣ ይህ ወደ ራስ
የተተኮሰ ጥይት የራሷን ሕዝብ እና ኢኮኖሚ ከመብላቱ ባለፈ፣ በዓለም ፊትም ገፅታዋን
አጠልሽቶታል። በእርግጥ በዲፕሎማሲው ዓለም ተፅዕኖ ፈጥሮ ለመታየት ውስጣዊ
አንድነት፣ ሰላም፣ ዕድገት መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው። በሌላው ዓለም ደምቆ፣ ተከብሮ እና
ሞገስ ጨምሮ ለመታየት ውስጣዊ ሰላም ቁልፉ ጉዳይ ነው። ውስጣዊ ሰላም በሀገራችን
በነበረ ጊዜ ሁሉ ኢትዮጵያ ሀይሏን ለሰላም አስከባሪነት ታስመርጥ ነበር። አሁን ግን
ፖለቲካዊ ጉስቁልና በወለደው ጠባሳ ምክንያት የዕርስ በዕርስ ጦርነት፣ መገዳደል፣ መፈራረጅ
ወዘተ በመኖሩ ሀገራዊ ፍቅር እና ውጫዊ ሀገራዊ ገፅታ ወደ ፈተና እየገቡ ይገኛሉ። ይህም
ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ውድቀት፣ ለሰብአዊ ክብር መጣስ እና ለዙሪያ መለስ ቀውስ
እያጋለጣት ይገኛል።
የዜጎች ደህንነት፣ የሀገር ክብር እና የተሟላ ሀገራዊ ሰላም ይኖር ዘንድ የአጥፍቶ መጥፋት
አባዜ ከተጠናወተው የጠብመንጃ ፖለቲካ መውጣት የግድ ይላል። አሁን በሀገራችን ሐሳብ
መፍረዱን፣ መዳኘቱን፣ መሸምገሉን ትቶ ነፍጥ የፖለቲካ ገበያውን ይዞታል። ጥያቄ አለን
የሚሉ መታሰራቸው፣ ነፃነት ማጣታቸው እና መደመጥ አለመቻላቸው የጠብመንጃ
አብዮትን አጋግሏል። ከዚህ ለመውጣት ሁልጊዜም ደጋግመን እንደምንለው ሀቀኛ
ውይይት፣ ንግግር እና ድርድር ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው። እነዚህን የሰላም መንገዶች ተከትሎ
ደግሞ አካታች መንግሥታዊ ውቅር፣ ጠንካራ ተቋማት እና የሰለጠነ የሰው ሀይል ወደ ሥራ
መሰማራት ከተቻለ ሀገር ሞገሷ ይመለሳል። ሕዝብም ከሰቆቃ ይወጣል። በሀገሪቱ ጥበብ እና
ፈጠራ፣ ሰላም እና ዕድገትም ይመጣል።
ዲፕሎማሲያችን ግቡን ይመታ ዘንድ በሀገር ውስጥ የጠብመንጃ አፈሙዞች በፍትሐዊ
እና በሀቀኛ ንግግር ከመጮህ ሊያባሩ ይገባል። የውስጥ ሰላም እና አብሮነት ለውጭ ገፅታ
ማማር ቅመሙ ነው። ውስጥ ሰላም ሳይሆን በዓለም ፊት የተስተካከለ ገፅታ ይዞ ለመታየት
መሞከር ሆድን በጎመን ቢደልሉት ጉልበት በዳገት ይለግማል መሆኑ አይቀሬ ነው። ውስጣዊ
ሰላማችን ለሁለተናዊ ውበታችን መድመቂያ ነውና