በ2016 በጀት ዓመት ለአንድ ሚሊዮን ሁለት መቶ ሠላሳ ሁለት ሺህ በላይ ሥራ ፈላጊ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።
እስካሁን በተደረገዉ ጥረት ከሁለት መቶ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ነው የአማራ ክልል ሥራና ስልጠና ቢሮ ያስታወቀው።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አወቀ ዘመነ ለበኩር እንደገለፁት በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ገደቦች ምክንያት በሥራ ዕድል ፈጠራው ላይ ጫና አሳድሯል። የሥራ ዕድል የሚፈጠረው ሀብት ማመንጨት እና ኢኮኖሚው ማደግ ሲችል እንደሆነም ያብራራሉ።
የሥራ ዕድል ፈጠራ በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ እየተከናወነ ቢሆንም የኢንተርኔት መዘጋት የተለያዩ ተግባራትን ለመከወን ፈታኝ አድርጎታል ብለዋል።
በተፈጠረው የሰላም እጦትና አለመረጋጋት ምክንያት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር አፈፃፅሙ ከግማሽ በላይ መቀነሱን አስታውቀዋል። በክልሉ አንፃራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አቶ አወቀ አስረድተዋል።
ሆኖም ግን በምዕራብ ጎጃም፣ በሰሜን ጎጃምና በምሥራቅ ጎጃም ዞኖች የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማከናወን የሰላም እጦቱ ፈታኝ አድርጎታል ነው ያሉት። በክልሉ አንዳንድ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳድሮች ሥራውን ለማከናወን ቢሮው መቸገሩን ገልፀዋል።
በኑሮውና በሀገሩ ተስፋ ያለው ወጣት ለመገንባትና ወደ ሥራ ለማስገባት ሁሉም የድርሻውን ሚና ሊወጣ ይገባል። ይህ ደግሞ የጋራ ርብርብን ይጠይቃል ብለዋል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ በየደራጃው ያለው የሥራ ዕድል ምክር ቤት በተደራጀ አግባብ ወደ ሥራ በመግባት የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም