አለመረጋጋት ሕብረቱን ፈትኗል

0
155

የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ በሚል የተቋቋመው ኢኮዋስ ምሥረታው እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር 1975 ነበር:: 15 ሀገራትን በአባልነት የያዘው ማኅበሩ በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመሥራት ነበር ዓላማ አድርጎ የተመሠረተው:: ዲሞክራሲን እና ጥሩ አመራርን ከተጠያቂነት እና ግልጸኝነት ጋር ማስፈን ደግሞ ዋና ዓላማው አድርጓል:: ይሁንና የዚህ ማሕበር አባል ሀገራት በአሁኑ ወቅት በተለይ በፖለቲካዊ ጉዳዮች እየታመሱ ይገኛል::
ቢቢሲ እንደዘገበው በውጭ እና በውስጥ ተጽዕኖዎች ሳቢያ በኢኮዋስ አባል ሀገሮች ውስጥ መከፋፈል እየተፈጠረ ነው:: ከ15ቱ የኢኮዋስ አባል ሀገሮች ውስጥ በቅርቡ በቡርኪናፋሶ እና በማሊ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደ ሲሆን፣ በኒጀር የተደረገው ደግሞ ሦስቱ ሀገሮች እርስ በርስ እንዲተጋገዙ ዕድል ፈጥሯል:: ይሁን እንጂ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ኒጀር የተደረገው መፈንቅለ መንግሥት ለቀጣናው የበለጠ ሥጋትን ደቅኗል::
እንደ ዘገባው ከሆነ የፈረንሣይ ቅኝ ግዛት የነበሩት የምዕራብ አፍሪካ ሀገሮች፣ ለፈረንሣይ የነበራቸው አመለካከት ማሽቆልቆልም ለኢኮዋስ ሌላው ፈተና ነው:: በተለይ እ.አ.አ. በ1994 በሩዋንዳ የተፈጸመውን የእርስ በርስ ጦርነት፣ ፈረንሣይ ማስቀልበስ የምትችልበት ዕድል ቢኖርም ይህንን ባለማድረጓ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አልቀዋል፣ የሚለው ግንዛቤ በማኅበረሰቡ ውስጥ መስረፁ ኢኮዋስ አንድነቱን ጠብቆ እንዳይቀጥል እያደረገ ነው::
ይህን ተከትሎም “ፈረንሣይ አትድረስብን” የሚሉ የምዕራብ አፍሪካ ሀገሮች ብቅ ማለት ጀምረዋል:: ከእነዚህም ውስጥ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባቸው ቡርኪናፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር ይገኙበታል::
ፍራንስ 24 (France 24) እንደዘገበው፣ ኢኮዋስ መፈንቅለ መንግሥት በተከናወነ ቁጥር በአባል ሀገራቱ ላይ ሰላም እንዲሰፍን በመደራደር እና ማዕቀብ በመጣል ሚና ሲጫወት ቆይቷል፣ አሁን ላይ ግን መፈንቅለ መንግሥት የሚከናወንባቸው ሀገሮች እየፈረጠሙ መጥተዋል:: በቅርቡ በኒጀር የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ፣ ኢኮዋስ የሀገሪቱ ወታደራዊ የሽግግር መንግሥት ተፈናቃዩን ፕሬዚዳንት መሐመድ ባዞምን ወደ ሥልጣን እንዲመልስ ካልሆነም ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቆ ነበር::
ይህን ለማድረግ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ የጊዜ ገደብ የሰጠው ኢኮዋስ ታዲያ፣ ወታደራዊ እርምጃ ሳይወሰድ ቀርቷል:: ለዚህ ደግሞ ወታደራዊ እርምጃው እንደሚኖር በማንሳት ለዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ቅድሚያ መስጠቱን በማንሳት ፍራንስ 24 ዘግቧል::
ኢኮዋስ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ያቀስቀመጠው ቀነ ገደብ ሲያልፍ ደግሞ፣ ኒጀር የአየር ክልሏን ዘግታለች:: ወታደራዊ መንግሥቱም የአየር ክልሉን የዘጋው ከጎረቤት ሀገሮች ሊሰነዘር የሚችል ጥቃትን ለመመከት እንደሆነ አስታውቋል::
በናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ቦላ ቲኑቡ የሚመራው ኢኮዋስ፣ በኒጀር ወታደራዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን ተከትሎ ኮትዲቯርና ሴኔጋል ሐሳቡን ደግፈዋል:: ሆኖም ከአባል ሀገሮቹ የነበረው የፖለቲካ ድጋፍ ተመሳሳይ አልነበረም:: ቤኒን ወታደር እንደማትልክ ስታስታውቅ፣ መፈንቅለ መንግሥት ያስተናገዱት ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር የኢኮዋስን ዕቅድ አጣጥለውታል::
በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዙትና ከኢኮዋስ አባልነት የታገዱት ወታደራዊ መንግሥታትም፣ ኢኮዋስ በኒጀር ላይ እርምጃ ከወሰደ “ጦርነት አውጇል” እንደ ማለት መሆኑን በመግለጽ ድጋፋቸው ለኒጂር እንደሚሆን አሳውቀዋል::
በኒጀር የተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ኢኮዋስን ብቻ ሳይሆን ፈረንሣይንም ፈትኗል:: የቀድሞ የፈረንሣይ ቅኝ ግዛት በነበረችው ኒጀር መፈንቅለ መንግሥት መካሄዱ፣ ፈረንሣይ በምዕራብ እና በመካከለኛው አፍሪካ ያላትን ቦታ የሚያሽመደምድ ሆኗል::
ክስተቱም ለፈረንሣይ ብቻ ሳይሆን አሜሪካ በአካባቢው ላላት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሥጋትን ያጫረ ነው:: ለፈረንሣይ ታማኝ አገልጋይ የነበሩት የቀድሞው የኒጀር ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ባዞም፣ መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደባቸው በኋላ ተቃዋሚዎች በፈረንሣይ ኤምባሲ በመገኘት ኤምባሲውን መዝጋታቸውን ኒውዮርክ ታይምስ አስፍሯል:: መፈንቅለ መንግሥቱን ያከናወነው የሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ኒጀር ከፈረንሣይ ጋር ያላት ትብብር ማብቃቱን አሳውቋል::
ይህ በኒጀር የተከሰተው ፈረንሣይን የማግለል አካሄድ ከዚህ ቀደም በቡርኪና ፋሶና በማሊ የታዬ ነበር:: ሦስቱም ሀገሮች የፈረንሣይ ቅኝ ግዛት የነበሩ ሲሆን፣ ፈረንሣይ በየሀገሮቹ ያላትን ተቀባይነት አሳጥተዋታል::
ይህን ተከትሎ ፈረንሣይ በቀጣናው ድህነትን ለመዋጋት፣ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና አይኤስ የተባለውን የሽብር ቡድንን ለመዋጋት በሚል የነበራት ሚና ተዳክሟል ብሏል የኒውዮርክ ታይምስ ዘገባ:: በእስያ ግሩፕ የአውሮፓ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሙጃታባ ራህማን እንደሚሉት፣ ፈረንሣይ የኒጀር መፈንቅለ መንግሥት ይመጣል ብላ አልጠበቀችም:: በማሊ እና በቡርኪና ፋሶ ከገጠማት ተቃውሞም አልተማረችም::
ዘገባው አክሎ እንዳብራራው፣ ፈረንሣይ ለዐሥርት ዓመታት ከበርካታ የቀድሞ ቅኝ ግዛት ሀገሮቿ ጋር የተወሳሰበ ግንኙነት ነበራት:: በሀገሮቹ ወታደሮችን በማሰማራት፣ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖን በማሳደር፣ በቀጥታ ከየሀገሮቹ ፕሬዚዳንቶች ጋር በመገናኘት ፍላጎቷን ስታስጠብቅ ቆይታለች::
በቁጥጥር ሥር የሚገኙት የኒጀር የቀድሞ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ባዞምም የፈረንሣይን በአጠቃላይም የምዕራባውያን ቀኝ እጅ ነበሩ:: በዚህ ተግባራቸው ደግሞ ከሌሎች በተለዬ የውጭ ዕርዳታ ይጎርፍላቸው ነበር::
በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት እንደ አውሮፓዊያን ዘመን ቀመር በ2023 የመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት ብቻ 1,800 የሽብር ጥቃቶች ተፈጽመዋል:: በዚህም 4,600 ሰዎች ሲሞቱ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል::
የኢኮዋስ ኮሚሽን ሊቀመንበር ኦማር ቶሬይ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እንዳስታወቁት፣ በምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ አባል ሀገሮች ውስጥ ያለው ሁኔታ ካልተስተካከለ የቀጣናው ደኅንነት የከፋ አደጋ ውስጥ ይወድቃል::
ከዚህ ቀደም መፈንቅለ መንግሥት በተካሄደባቸው ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ እና ጊኒ በታጠቁ ኃይሎች የሚሰነዘር ጥቃትም እንደቀጠለ ነው:: ፀረ ፈረንሳይ አመለካከት እያደገ መምጣቱም ወታደሮች ሀገሮችን እንዲቆጣጠሩ ዕድል እየፈጠረ ነው::
በአባል ሀገሮቹ ውስጥ ያሉ አለመረጋጋቶች ከመፈንቅለ መንግሥት ጋር ተደምረው ኢኮዋስን እየፈተኑት ይገኛሉ:: ይህ በእንዲህ እንዳለ አባል ሀገሮቹ በኒጀር የተደረገውን መፈንቅለ መንግሥት የሚይዙበት አኳኋን ተቀባይነት ያለው መሆን እንዳለበት የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፤ ሀገሮቹ ኃይላቸውን ማጠናከር ላይ ካልሠሩም በቀጣናው የሚታየው የመፈንቅለ መንግሥት ልማድ ለቀጣናው ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ሥጋት ይሆናል::
እ.ኤ.አ. ከ1990 ወዲህ በአፍሪካ 43 መፈንቅለ መንግሥቶች ተደርገዋል:: 41 የመፈንቅለ መንግሥት ጥረቶች ደግሞ ከሽፈዋል:: ከከሸፉት ውስጥ ዐሥራ ሦስቱ ከ2000 እስከ 2009 ድረስ ባሉት ጊዜያት የተሞከሩ ናቸው፤ 36 ሙከራዎች የተከናወኑት ደግሞ ከ2010 እስከ 2019 ባለው ጊዜ ውስጥ ነው:: ከ2020 እስካሁን (2024) ደግሞ አፍሪካ ዘጠኝ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎችን አስተናግዳለች::
በኢኮዋስ አባል ሀገራት የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ ኒጀር፣ ማሊ እና ቡርኪናፋሶ ከኢኮዋስ አባልነት መውጣታቸውን አስታወቀዋል። ሦስቱ በወታደራዊ መንግሥት የሚመሩ ሀገራት ባወጡት መግለጫ በ1975 ከመሠረቱት የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ወይም ኢኮዋስ በይፋ መውጣታቸውን ጠቁመዋል።
ሀገራቱ ባወጡት የጋራ መግለጫ ኢኮዋስ “በውጭ ኃይሎች ተጠምዝዞ ከቀደሙት የቡድኑ መሥራቾች የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ተንሸራቷል” ብለዋል። “ኢኮዋስ የተመሠረተበትን መርህ በመካድ ለአባል ሀገራቱ እና ሕዝቦቻቸው ስጋት ሆኗል”ም ነው ያሉት።
በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የተነሳው አለመረጋጋት ሴኔጋልንም እየፈተነ ይገኛል፤ በሴኔጋል የተራዘመውን ምርጫ ተከትሎ በተቃዋሚ እና በመንግሥት ደጋፊዎች መካከል ግጭት ተፈጥሯል:: በዚህም ፖሊስ በተቃዋሚዎቹ ላይ በወሰደው እርምጃ ሦስት ሰዎች መሞታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ የምሥራቅ አፍሪከ ሀገራትን አንድነት እና ትብብር ለማጠናከር አልሞ የተቋቋመው ኢጋድ ተመሳሳይ ዕጣ ፋንታ እንደተጋረጠበት ይታወቃል:: ለአብነትም ሱዳን ከአባልነት ራሷን እንደምታገል ማስታወቋ የድርጅቱን ዕጣ ፋንታ አጣብቂኝ ውስጥ አስገብቶታል። ከዚህ በተጨማሪም ቀጣናው የግጭት ማዕከል መሆኑ የድርጅቱን ፈተና ከድጡ ወደ ማጡ አድርጎታል።

(ቢኒያም መስምን)
በኲር የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም – https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here