የተፈጥሮ ሀብት ልማት በረከቶች ሲገለጡ

0
427
የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ለግብርናው ዘርፍ የጀርባ አጥንት ነው። ሀገራት ወደ ተሻለ የኢኮኖሚ እድገት መሸጋገር የቻሉት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራን አጠናክረው በማልማት እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። ደቡብ ኮሪያ ደግሞ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በአብነት ተጠቃሽ ናት።
የተፈጥሮ ሀብትን በመጠበቅና በማልማት፣ የአፈር ለምነትን በማሳደግ የምርት መጠን እንዲሻሻል በማድረግ የምግብ ዋስትናን ያረጋግጣል።
የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ በ19ኛው ክፍለ ዘመን እንደተጀመረ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በአማራ ክልል ከ1970 ዎቹ ጀምሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ መከናወን መጀመሩን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶ/ር አልማዝ ጊዜው ይናገራሉ።
በክልል ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሠራ በማሕበረሰቡ የነቃ ተሳትፎ እየተሠራ በመሆኑ ተጨባጭ ውጤት እየመጣ መሆኑን ለአሚኮ ተናግረዋል። ለአብነትም በ2015 ዓ.ም 310 ሺህ ሄክታር መሬት የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ታቅዶ 357 ሺህ ሄክታር መሬት ማከናወን መቻሉን አንስተዋል።
ምክትል ኃላፊዋ እንዳስታወቁት በ2016 ዓ.ም ከ376 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የአፈር እና ውኃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን በእቅድ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን ያብራራሉ። በአማራ ክልል ከ19 ሺህ በላይ ተፋሰሶች ሲኖሩ በዘጠኝ ሺህ 60 ተፋሰሶች ላይ ለመስራት ሰፊ ዝግጅት ተደርጓል። የታቀደው እቅድ እንዲሳካም ከወዲሁ በተለያዩ አደረጃጀቶች ቅድመ ዝግድት ተደርጓልም ብለዋል። በተቀናጀ መንገድ ካልተሰራ የሚፈለገው ለውጥ ሊመጣ ስለማይችል የማሕበረሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆንኑ አስገንዝበዋል።
በ2015 ዓ.ም አርሶ አደሩ ከባለሙያው ጋር ባደረገው የጋራ ርብርብና የነቃ ተሳትፎ አራት ቢሊዮን ብር የሚገመት ጉልበቱን በነፃ እንዳበረከተ ተናግረዋል።
ደቡብ ኮሪያ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ተጠቃሽ ናት ያሉት ዶ/ር አልማዝ፣ ለውጤታማነቱ ደግሞ የማሕበረሰቡ የነቃ ተሳትፎ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አንስተዋል። በመሆኑም የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ (የተፋሰስ ሥራ) የአርሶ አደሩን የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ መረባረብ አስፈላጊ እንደሆነ አመላክተዋል።
የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ ግብርናው መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ፣ የውኃ ምንጮች እንዲጎለብቱ፣ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር፣ አረንጓዴ ልማት እንዲያድግ፣ የአፈር ለምነት እንዲጨምር፣ የባዮ ጋዝ (አማቂ ጋዝ) መጠንን እና የባዮ ማስ መጠንን (የስነ ሕይወት ስብስብን) ከፍ በማድረግ የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለው ያብራራሉ።
የአማራ ክልል እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት በመሆኑ ልንጠብቀውና ልናለማው ይገባልም ብለዋል። ትልልቅና መካከለኛ ሐይቆች፣ ትልልቅ ፓርኮች፣ ብርቅየ የዱር እንስሳት፣ ጥብቅ ደኖች፣ ተራሮች፣ ግድቦችና ሌሎች ሀብቶች ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆኑ ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው ዶ/ር አልማዝ አሳስበዋል። በተለይም የመሬት መሸርሸር እንዳይከሰት በትኩረት በመሥራት ኢኮኖሚያዊ ፍይዳቸውን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።
ዶ/ር አልማዝ እንዳሉት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የአመራሩን ዕውቀት፣ ክህሎትና ቁርጠኝነት እንዲሁም የማሕበረሰቡን ትጋት በስፋት ይጠይቃል። ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅትና ተናቦ መሥራትንም ይሻል። እየተሠራ ባለው ሥራም አበረታች ውጤት እየታየ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ጥራትን ጠብቆ አለመሥራት፣ ከሰው ቁጥር ጋር የተመጣጠነ የልማት መሣሪያ አለመኖር እንዲሁም የጉልበት መባከን ውስንነቶች መሆናቸውን በማንሳት፣ ሊስተካከሉ እንደሚገባቸው አመላክተዋል።
ዶ/ር ኃይሉ ክንዴ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ከፍተኛ ተመራማሪው ናቸው። እርሻቸው እንደሚሉት ከ2003 እስከ 2014 ዓ.ም በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ በተደረገው ጥናት የአፈር ለምነት መሻሻሎች መኖራቸውን ጥናቶች ያመለክታሉ። ይህም የአፈር ለምነቱን ለመጠበቅ ይወጣ የነበረውን የአፈር ማዳበሪያ ወጭ ዝቅ እንዲል አስችሏል ባይ ናቸው።
በ92 ተፋሰሶች ላይ በተካሄዱ ጥናቶች በጥንቃቄ የተያዙ፣ ሕግና ደንብ ያላቸው፣ የተፋሰስ ኮሚቴ ያላቸው፣ ማሕበረሰቡ በስፋት የተሳተፈባቸውን በመለየት በተሠራ ጥናት የአፈር ለምነቱ በ21 በመቶ ከፍ እንዲል አግዟል ብለዋል ተመራማሪው። ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች ያላሟሉት ደግሞ የአፈር ለምነት እንደቀነሰባቸው ጥናቶች ያሳያሉ ብለዋል።
ጥናቶችን ዋቢ አድርገው እንዳብራሩት፣ በዓለም በከባድ ዝናብና በጎርፍ ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ የአፈር መሸርሸር እየተከሰተ ከስምንት ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ይታጣል። ይህም 34 በመቶ የሰብል ምርት ወይም 34 ሚሊዮን ኩንታል ይታጣል እንደማለት ነው። ይህ ደግሞ ሦስት ነጥብ ሰባት በመቶ የዋጋ ጭማሪ (የኑሮ ውድነት) እንዲኖር ምክንያት ነው ይላሉ።
አርሶ አደሩ እርከንን በመሥራት፣ ችግኝን በመትከል፣ ከእንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግና ሕግና ደንቦችን ተከትሎ በመሥራት የምርት ጭማሪ መገኘቱን ይናገራሉ። አርሶ አደሮቹ ከራሳቸው ማሳ ጀምሮ የተፋሰስ ሥራ በመሥራታቸው የተሻለ ውጤት እየተገኘ ነውም ብለዋል።
የመሬት ለምነቱ እንዲጨምር በመሠራቱ ምርትና ምርታማነት ማደጉንም አንስተዋል። በአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ እንዲሁም በደን ልማት ሥራ አርሶ አደሩ የተሻለ ለውጥ እያሳዬ መምጣቱን አድንቀዋል። ተፋሰሶችን ጥቅም በሚሰጡ እፅዋቶች በመሸፈን አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
በተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በቅንጅት አርሶ አደሩን በተጠናከረ መልኩ ማገዝ ተገቢ እንደሆነ አመላክተዋል። ማሕበረሰቡን ለማገልገልና ግብርናውን ለማሻገር በጋራ ተናቦ መሥራት ይጠይቃልም ብለዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here