ሞገዱን ምን ነካው?

0
269

ይህ ክለብ ከተመሰረተ 43 ዓመታትን ተሻግሯል። ለረጅም ዓመታት በታችኛው የሊግ እርከን ቆይቷል። ወደ ላይኛው የሊግ እርከን (ፕሪሚየር ሊጉ) ካደገ ስድስት ዓመታትን ብቻ ነው ያስቆጠረው። ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በደጋፊዎቹ ብዛት እና ድምቀት ከሚታወቁ ክለቦች ውስጥ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይሰለፋል። በዘንድሮው የውድድር ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ መድረክ በመሳተፍ ጥሩ ተስፋን ያሳየ ክለብ ነው- ባሕር ዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ።
ባሕር ዳር ከተማ ስፖርት ክለብ ከሚያስተዳድራቸው ክለቦች መካከል ባሕር ዳር ከነማ አንዱ ነው። የጣናው ሞገድ በጊዜ ሒደት እየተሻሻለ እና ለውጥ እያሳየ የሚገኝ ቡድን ነው። በ2010 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው (ማንጎ) እየተመራ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ አድጓል፣ የአማራ ክልል ሁለተኛው የፕሪሚየር ሊጉ ክለብ መሆንም ችሏል። ባለፉት ስድስት ዓመታትም በፕሪሚየር ሊጉ እየተፎካከር ይገኛል። ክለቡ በተለይ ባሳለፍነው የ2015 ዓ.ም እስከመጨረሻው ድረስ ከአንጋፋው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በመፎካከር ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል።
ውጤቱም በአፍሪካ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲሳተፍ አስችሎታል። ባሳለፍነው የውድድር ዓመት በፕሪሚየር ሊጉ ያሳየው ድንቅ አቋምም በደጋፊዎች ፣በተጫዋቾች እና በክለቡ አመራሮች ዘንድ ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል። ይህም በ2016 ዓ.ም የውድድር ዘመን ብዙዎቹ ተስፋ እንዲሰንቁ እና በክለቡ እምነትን እንዲያሳድሩ ማድረጉ አይዘነጋም። የዘንድሮው የውድድር ዓመት ከመጀመሩ በፊት አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ቸርነት ጉግሳን፣ ፍሬዘር ካሳን፣ ፍሬው ሰለሞንን እና ሌሎችንም አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም እና የነባሮቹን ውል በማደስ ስብስቡ እንዲጠናከር ሰፊ ሥራ መስራቱም ይታወሳል። ይህ ዕቅድ እና ፕሮጀክትም ውድድሩ ሲጀመር ክለቡ ተፎካካሪ እና ጠንካራ ሆኖ በመቅረቡ በደጋፊዎቹ ዘንድ እምነት ተጥሎበት ነበር። እንዲያውም በውድድሩ መጨረሻ ከዋንጫ ጋር ሊያጠናቅቁ ይችላሉ ተብለው ግምት ከተሰጣቸው ክለቦች ውስጥ የጣናው ሞገድ አንዱ እንደነበረም አይዘነጋም። ይሁን እንጂ ሳምንታት ተቆጥረው ወራት ሲነጉዱ ግምቶችን ፉርሽ አድርጎ ደካማ አቋም እያሳየ ይገኛል።
አሁን ላይም አስቸጋሪ የውድድር ጊዜ እያሳለፉ ነው። ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት የ14ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ድረስ አቅም አንሶት ጉልበቱ ዝሏል። ከመሪው መቻል በ11 ነጥብ ርቆ በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ ተቀምጧል።
የጣናው ሞገድ በተለይ በቅርቡ ካደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች አንድም ጨዋታ ማሸነፍ አልቻለም። በአራቱ ሲሸነፍ በሁለቱ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ከሜዳ ወጥቷል። ማግኘት ከነበረባቸው 18 ነጥቦች ሁለት ነጥቦችን ብቻ አግኝቷል። ይህ ቁጥራዊ መረጃም ክለቡ እያሳየ ያለውን ደካማ አቋም ፍንትው አድርጎ በግልጽ ያሳያል።
በአጠቃላይ እስካሁን ካደረጋቸው 14 የፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብሮች አምስት ጨዋታዎችን ብቻ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ በአምስት ጨዋታዎች ተሸንፏል። በቀሪው አራት ጨዋታ ደግሞ ነጥብ ተጋርቶ ከሜዳ ወጥቷል።
ለወትሮ ጠንካራ የነበረው የፊት መስመሩም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኳስ እና መረብን ለማገናኝት ሲቸገር ተስተውሏል። በ14 መርሐ ግብሮች 17 ግቦችን ብቻ በተጋጣሚ መረብ ላይ አስቆጥሯል። ይህ ቁጥርም ከታላላቅ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ያነሰ ሆኖ ተመዝግቧል። በአንጻሩ የኋላ ክፍሉም በቀላሉ የሚረበሽ እና ግቦች የሚቆጠርበት መሆኑን ባለፉት ወራት ተመልክተናል። በአጠቃላይም 16 ግቦች ተቆጥረውበታል።
ይህም አሁን ላይ በፕሪሚየር ሊጉ ደካማ የኋላ ክፍል ካላቸው የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ተርታ እንዲሰለፍ አስገድዶታል። ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ባጠናቀቀበት የ2015 ዓ.ም ባሕር ዳር ከነማ በአጠቃላይ አራት ጨዋታዎችን ብቻ መሸነፉ ይታወሳል። ዘንድሮ ግን ይህ ቁጥርን ገና ከወዲሁ ተሻግሮታል። ያስቆጠራቸውን እና የተቆጠረበትን ግቦች ስንመለከት ዘንድሮ ምን ያህል ደካማ አቋም እያሳየ ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል። ታዲያ ደጋፊዎቹም የቡድኑ ችግር ምን ይሆን? ሲሉ ይጠይቃሉ። የባሕር ዳር ከተማ ስፖርት ክለብ ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑል ፈቃደ የጣናው ሞገድ አሁን ለገባበት የውጤት ቀውስ ምክንያቶች ናቸው ያሏቸውን በግምገማቸው መለየታቸውን ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የኦንላይን ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። ሥራ አስኪያጁ ለክለቡ ውጤት ማጣት ዋነኛ ችግሮች ናቸው ብለው ካነሷቸው ምክንያቶች መካከል በቂ የቅድመ ውድድር ዝግጅት እና እረፍት አለማድረጋቸውን አንስተዋል::
የጣናው ሞገድ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈበት የአፍሪካ መድረክ በመጀመሪያው ዙር የታንዛኒያውን አዛምን በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ሲልፍ በሁለተኛው ዙር ግን በቱኒዚያው ክለብ አፍሪካ ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ መሆኑ የሚታወስ ነው። እንደ አቶ ልዑል ማብራሪያ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ጨዋታዎች ምክንያት ክለቡ በቂ የቅድመ ውድድር ዝግጅት እና እረፍት ሳያደርግ ፕሪሚየር ሊጉ መጀመሩ አሁን ላስመዘገበው ደካማ ውጤት አንደኛው ምክንያት ነው።
ተጫዋቾቹ በቂ እረፍት አለማድረጋቸውም ለጉዳት እና ለድካም እንዳጋለጣቸው ነው የስፖርት ክለቡ ሥራ አስኪያጁ የተናገሩት። ተጫዋቾቻቸው ያልተገባ ካርዶችን መመልከታቸውም ለቡድኑ ውጤት ቀውስ ሌላኛው መንስኤ ተደርጎ ተነስቷል። ይህም በሁሉም የሜዳ ክፍል ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል። አደም አባስ በጉዳት ምክንያት ወደ ሜዳ አለመግባቱ፣ የዱሬሳ ሹቢሳ ክለቡን መልቀቅ የፊት መስመሩ ላይ መሳሳት ፈጥሯል። እንዲሁም አንዳንድ የክለቡ ተጫዋቾች ከሜዳ ውጪ የሚያሳዩት የስነ ምግባር ጉድለትም ክለቡን ሜዳ ውስጥ ዋጋ እያስከፈለው ስለመሆኑ አቶ ልዑል ያስረዳሉ። ይሁን እንጂ በመልበሻ ቤት ግን ምንም ዓይነት ክፍፍል አለመኖሩን የስፖርት ክለቡ ሥራ አስኪያጅ ጠቁመዋል።
ምንም እንኳ እነዚህ ሁሉ ችግሮች ቢኖሩም ባሕር ዳር ከነማ በዚህ ደረጃ የውጤት ቀውስ ውስጥ ሊገባ እንደማይገባ አቶ ልዑል በአጽንኦት ተናግረዋል። ታዲያ ክለቡን ቶሎ ወደ ቀድሞ አቋሙ ለመመለስም የዝውውር ጊዜውን ተጠቅመው በሁሉም የሜዳ ክፍል ተጫዋቾችን በማስፈረም ክፍተታቸውን እንደሚሞሉ አቶ ልዑል ተናግረዋል።
በተጨማሪም ሜዳ ውስጥም ከሜዳ ውጪም ያሉባቸውን ችግሮች ፈትተው በሁለተኛው ዙር የተሻለውን እና ተፎካካሪውን ባሕር ዳር ከነማ ይዘው እንደሚመጡም ነው የተናግሩት፤ አቶ ልዑል።

(ስለሺ ተሾመ)
በኲር የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here