ከጥልቅ ውቅያኖስ እስከ ተራራ ጫፍ፣ በቸልተኝነት የሚጣል ኘላስቲክ ተፈጥሯዊ አካባቢን በክሎ በዱር እንስሳት ጤንነት ላይ አደጋ ማስከተሉን ኤንዲቲቪ ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::
በህንድ ማሃራሽትራ ግዛት ታዶባ ብሄራዊ ፓርክ ከኩሬ ውስጥ ውጋጅ ኘላስቲክ አውጥቶ በአፉ የያዘ ነብር እ.አ.አ. በ2023 ታህሣስ ወር ለዕይታ በቅቶ ነበር:: ሁነቱን የተመለከቱም መልዕክቱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ማህበራዊ ድረገፆች አስነብበዋል::
ዲኘ ካቲከር በተሰኘ ፎቶግራፍ አንሺ ባለሙያ የተቀረፀው ምስል ውጋጅ ኘላስቲክን ከኩሬ ውስጥ አውጥቶ በአፉ ይዞ በሚሄደው ነብር ግርጌ “መኖሪያ ደናችንን እናፀዳለን!” የሚል የፎቶ መግለጫ የተፃፈበት እንደነበር ነው ድረ ገጹ ያስነበበው::
የተለቀቀውን ቪዲዮ የተመለከቱ የበይነ መረብ ተገልጋዮች አስደንጋጭ እንደነበርም ነው አስተያየታቸውን ያሰፈሩት::
ባለ ግርማ ሞገሱ ነብር ከኩሬ ያወጣውን ኘላስቲክ ቢበላው የሚደርስበት የጤና ዕክል ግልፅ መሆኑን አስፍረዋል:: ተመልካቾች ከዚህም በላይ የፍጥረታት ቁንጮ በሆነው “የሰለጠነው” ሰው በሚፈፅመው ስህተት ሌሎች የሚከፍሉት ዋጋ አሳዛኝ መሆኑን ጠቁመዋል::
የህንድ የደን ሀብት አገልግሎት ባለሙያ ሱዛንታናንዳ ተቀርጾ የተለቀቀውን ቪዲዮ ተመልክተው ሰዎች የተገለገሉበትን ኘላስቲክ በዘፈቀደ እንዳይጥሉ መክረዋል:: ከዚህም ባለፈ ተገልጋዮች ወደ ዱር እንስሳት መኖሪያ ክልል የማይበሰብሱ ቁሶችን ወስደው በመጣል ለአደጋ ከማጋለጥ መጠንቀቅ እንደሚገባቸው ነው ያሳሰቡት::
ባለሙያዋ ድምፅ አልባው የነብሩ መልዕክት ለሁሉም ጐልቶ የሚሰማ መሆኑንም አስምረውበታል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ