በሱፍ ያማረዉ

0
167
የዕደ ጥበብ ባለሙያዋ አጫጭር ፀጉር ያለውን “ፒንቸር” የተሰኘ የውሻ ዝርያ ለዕውነታ በቀረበ መልኩ በሱፍ ክር መስራት መቻሏን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል::
ጃፓናዊቷ ትሩሚ ኦታ በመጀመሪያ ዕይታ ዕውነተኛ ውሻ የሚመስለውን ባለ አጫጭር ፀጉር የውሻ ቅርፅ በሱፍ ክር ሰርታ ለማጠናቀቅ 500 ሰዓታት ወይም 20 ቀናት ከ20 ሰዓታት ወስዶባታል::
የዕደ ጥበብ ባለሙያዋ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከደንበኞች በሚቀርቡላት የተለያዩ ትዕዛዞች መሠረት በርካታ የጥበብ ውጤቶችን መስራት ችላለች።
ከሁሉም በተለየ መልኩ የ“ፒንቸር” ዝርያው ውሻ ስራው አድካሚ እና በርካታ ቀናት የወሰደባት መሆኑን ተናግራለች:: ቴሩሚ ኦታ ዊዝ ኒውስ ለተሰኘ መገናኛ ብዙሃን የውሻ ዝርያው አካል አጫጭር ፀጉር የለበሰ መሆኑ አድካሚ አድርጎታል።
ለውሻው ቅርፅ በተሰራው “frame’’ መቃን ላይ የተለያየ ቀለም ያለው የሱፍ ክርን በመቀላቀል በመርፌ መትከልን ግድ ብሏታል- ቱሩሚ ኦታን:: የውሻው ቅርፅ ፀጉሮቹ ረዣዥም ቢሆኑ አካሉን በስፋት ስለሚያለብሰው ስራው ቀላል ይሆን እንደነበር ተናግራለች።
ቅርጹን በጣም አጠጋግቶ በመርፌ በመውጋት ሙሉ አካሉን ጸጉር ለማልበስ በርካታ ቀናትን ወስዶባታል:: የፀጉሩን አበረቅራቂነት ለማስጠበቅ፤ በሆድና ዕግሮቹ ጥጋ ጥግ ነጣ ያለ መልክ ለማስያዝም የተለያየ የሱፍ ክሮች መቀላቀል እንደነበረባቸውም ጠቁማለች ::
በመጨረሻም ውጤቱ ያማረ ለመሆኑ በማህበራዊ ሚዲያ ከ32 ሺህ በላይ አድናቂ ተመልካቾች ማግኘቱ አብነት መሆኑን ነው ድረ ገጹ ያመላከተው::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here