ብዙ ኃያላን ተነስተው ወድቀዋል፤ ብዙዎች ታይተው ጠፍተዋል። ነገር ግን ኢትዮጵያ የዘመናት ተግዳሮቶቿን እየተቋቋመች የግዛት አንድነቷን ጠብቃ እስከዛሬ የዘለቀች ብርቱ ሀገር ናት።
ለማንም ለምንም ሸብረክ ሳትል፣ የተዳፈሯትን ሁሉ በአልበገሬ ጀግኖች ልጆቿ ፈርጣማ የአንድነት ክንድ እየደቆሰች ለዘመናት ተፈርታ እና ተከብራ የኖረች የብርቱ ጥቁር አናብስት ምድር ናት – ኢትዮጵያ።
ጊዜ እና ሁኔታ እየጠበቁ ሁልጊዜ በእጃቸው ሊያደርጓት የዶለቱ፣ ጦር የሰበቁባት ጠላቶቿ ብዙ ነበሩ። በተፈጥሮ ፀጋዋ፣ መልከዓ ምድራዊ ጠቀሜታዋ፣ በተስማሚ አየሯ የቋመጡ ብዙዎች በሀይል ሊያስገብሯት የተዳፈሯትን ሁሉ በማያዳግም ቅጣት አደብ እያስገዛች ነፃነቷን አስከብራ የኖረች የጀግኖች መፍለቂያ ምድር ናት።
ኢትዮጵያ ሲነኳት እንጂ በእብሪት ተነሳስታ የማንንም ወሰን አልፋ አትደፍርም። ከነኳት ደግሞ ጠላቶቿን አያድርገን፣ ወዳጅነቷን እንጂ ጠላትነቷ ከባድ ነው። በሀገር ከመጡባቸው ግንባራቸውን ለጥይት ደረታቸውን ለጦር የሚሰጡ ቆራጥ ልጆች ከመውለድ የማይቦዝን ማህፀነ ለምለም ናት።
ዓለም ሁሉ የገበረላቸው በኦቶማን ቱርኮች እድሜ ልካቸውን ጠረፍ ለጠረፍ ከመንከራተት ባለፈ እግራቸው የጀግኖቹን ሀገር ስንዝር መሬት እንዲረግጥ አልፈቀደላቸውም። የኢትዮጵያን ግዛት ደጋግመው የተዳፈሩት የግብፅ ተስፋፊዎች ትንኮሳዎች ዳግም እንዳይሞክሩት ያደረጉ ደርዘን የሽንፈት ፅዋቸውን ተጎንጭተው አርፈው የተቀመጡበትን ታሪክ የፃፈችው ኢትዮጵያ ናት። ጉራ እና ጉንደት ይመስክሩ።
ባለተራዋ ጣሊያን ምንኛ ተታለለች?! አፍሪካን ለመቀራመት የአውሮፓ የቅኝ ግዛት ተስፋፊ ሀያላን በጀርመኗ መዲና በርሊን ውስጥ በዶለቱበት ወቅት አቅሙ እና ልምዱ የነበራቸው እንግሊዝ እና ፈረንሳይ እንኳ ያልደፈሩትን እድለ ቢሷ ጣሊያን ኢትዮጵያን ለመያዝ ተጋጋጠች።
በኢትዮጵያ ነፃነት ላይ የውጭ ጥቃት መታየት የጀመረው ቆየት ያለ ታሪክ ቢኖረውም ጫፍ የነካው ግን በተለይ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛው አጋማሽ ላይ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል። የወረራ ትንኮሳዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች የተቃጡ ሲሆን በግብፅ፣ በማህዲስት ሱዳን፣ እና በፋሽስት ጣሊያን በኩል የተፈፀሙ ናቸው። ሁሉንም ኢትዮጵያን በመውረር ብሔራዊ ፍላጎታቸውን ማስፈፀም ነበር፣ ሆኖም ሁሉም በኢትዮጵያ ጀግኖች መክነዋል። ለአሁኑ ትኩረታችን በጣሊያን ወረራ፣ የአድዋ ድል እና ውጤቱ ላይ ይሆናል፣ እንኳን ለ128ኛው የአድዋ ድል አደረሳችሁ ማለቴን አልረሳሁም።
የጣሊያን መንግሥት እንደ ሌሎች የአውሮፓ ሃያላን በአፍሪካ ምድር ቅኝ ግዛት የመመስረት ፍላጎት ነበረው። የምስራቅ አፍሪካን ጠረፋማ ክልልን በመያዝ ይህን ፍላጎቱንም ለማሳካት እንቅስቃሴ ጀመረ። ሰኔ 19 ቀን 1874 ዓ.ም የኢጣሊያ መንግስት አስቀድሞ አሰብን ከአካባቢው የጎሳ አለቆች በግዥ ይዞት ከነበረ ሩባቲኖ ከሚባል አንድ የኢጣሊያ የመርከብ ኩባንያ በመግዛት አሰብ የኢጣሊያ ግዛት መሆኗን አሳወቀ። በመቀጠልም በእንግሊዝ አማካይነት የጣሊያን ጦር በምፅዋ ሰፈረ። ምፅዋ በ1877 ዓ.ም በጣሊያኖች እጅ ወደቀች።
እናም በምፅዋ ሳትወሰን ወደ መሀል የኢትዮጵያ ግዛት ዘልቆ የመግባት ወረራ ሞከረች። የመጀመሪያው የጣሊያን የወረራ ትንኮሳ መሆኑ ነው። ይህ ድርጊታቸውም ከራስ አሉላ ጋር አላተማቸው። እናም ሰኔ 26 ቀን 1887 ዓ.ም በተካሄደው የዶጋሌ ጦርነት የጣሊያን ወራሪ ሀይል በራስ አሉላ ጦርነት ክፉኛ ተመታ። ከ500 በላይ የጣሊያን ወታደሮች የተገደሉበት ዘግናኝ እልቂት ነበር። ይህን አሳፋሪ ሽንፈት ለመበቀልም የጣሊያን መንግስት ከፍተኛ በጀት መድቦ ለጥቃት ተዘጋጀ። ነገር ግን
በወቅቱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መለዋወጥ በማሳየቱ ኢጣሊያኖች ወደ ኤርትራ የመስፋፋት ምቹ ሁኔታ ፈጠረላቸውን። በዚህ መካከል ነበር ከዐፄ ዮሐንስ ሞት በኋላ የተተኩት ዳግማዊ ምኒልክ ምንም እንኳ የጣሊያኖች ወዳጅ ቢሆኑም የመስፋፋት እንቅስቃሴያቸው ግን አላማራቸውም። ኢጣሊያኖች ምኒልክን ለማገዝ በሚል ሽፋን ከኤርትራ አልፈው ወደ ትግራይ የሚያደርጓቸው ዘመቻዎች የንጉሡን እምነት እየሸረሸረው መምጣቱ ፔድሮ አንቶኒሊን አሳስቦታል። ዋነኛው የውጫሌው ስምምነት ሲሆን ሚያዚያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም ውጫሌ ውስጥ በማካሄድ ሁለቱ መንግሥታት ግንኙነታቸውን ለማጠንከር በሚመስል መልኩ ተፈረመ።
በሀገራቸው ጉዳይ ቁጣቸው የሚያስደነግጡትን እነዚህን ኢትዮጵያውያን ከፍቅር ውጭ የሚያንበረክካቸው ሌላ ምንም ሀይል አለመኖሩን ፈጥኖ የተረዳው ኮንት አንቶኔሊ የንጉሡ ወዳጅ መስሎ መቅረብን መረጠ። ውስጥ ውስጡን ግን ስውር የስለላ ስራውን ይሰራ ነበር። አንቶኔሊ የኢትዮጵያውያንን ሀቀኝነት እንዲሁም ጨዋነት እንደ ሞኝነት፤ እንደ መሃይምነት ቆጥሮ በማጭበርበር አላማውን ለማሳካት ያልሞከረው የለም። አንቶኔሊ ሌላ የዘነጋው ኢትዮጵያውያን አስተዋይ እና አርቀው አሳቢ መሆናቸውን ነበር። በልቡ የተሰወረውን አላማ ይዞ የዐፄ ምኒልክ እና የእቴጌ ጣይቱ ወዳጅ በመሆን ሴራ ጉንጎናውን ይሰራ ጀመር።
በዚህ መካከል ታዲያ ኮንት አንቶኔሊ በኤርትሪያ ካሉ ጣሊያናውያን ወገኖቹ ጋር በመሆን አንድ የስምምነት ሰነድ አዘጋጅቶ ለመፈራረም ወደ ምኒልክ ይዞት መጣ። ከንጉሡ ጋር በጉዳዩ ላይ በደንብ ተወያዩ። በወቅቱ ያልተረጋጋውን ዙፋናቸውን ለማረጋጋት ወሎ ወርደው ነበር። እናም አንቶኔሊ ምኒልክ እንደምንም ሰብኮ እና አግባብቶ ውጫሌ ከተማ ውስጥ በንጉሡ ድንኳን ውሉ ተፈረመ። የውጫሌው ስምምነት ተብሎ ተሰየመ። ዉሉ 20 አንቀፆችን የያዘ ሆኖ በአማርኛ እና በጣሊያንኛ ቅጅዎች ሰነዱ እንዲዘጋጅ ተደርጓል። አስራ ሰባተኛው አንቀፅ ግን በአማርኛ እና በጣሊያንኛ ሆን ተብሎ የተለያየ ትርጉም እንዲይዝ ተደርጎ ነበር። የአማርኛው ቅጅ …ኢትዮጵያ ከውጭ መንግሥታት ጋር የምታደርጋቸውን ግንኙነቶች ከፈለገች በጣሊያን በኩል ማድረግ እንደምትችል የሚገልፅ እንድምታ ያለው ሲሆን ይህም ትክክለኛው የስምምነቱ ሀሳብ ነበር። ነገር ግን በጣሊያነኛው ቅጅ …ኢትዮጵያ ከውጭ መንግሥታት ጋር የምታደርጋቸውን ግንኙነቶች በጣሊያን በኩል ብቻ እንደሚሆን የሚገልጽ ሀሳብ የያዘ ነበር። የጣሊያነኛው ትርጓሜ ኢጣሊያንን የኢትዮጵያ ሞግዚት በማድረግ በተጭበረበረ መልኩ ለሁሉም የዓለም መንግሥታት ተሰራጨ። ስለሆነም መንግስታት ኢትዮጵያ በጣሊያን መንግሥት ስር ያለች ግዛት አድርገው አወቁ።
ዐፄ ምኒልክ ሰነዱ በዚህ መልኩ መጭበርበሩን አያውቁም ነበር። ስምምነቱ ችግር እንዳለበት የታወቀው ከሶስት ዓመታት በኋላ ነበር። ይኸውም ዐፄ ምኒልክ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መሆናቸውን ለማሳወቅ የፃፉላቸውን ደብዳቤ የጀርመኑ ንጉሠ ነገሥት በቀጥታ መቀበላቸውን ተከትሎ የጣሊያን ጋዜጦች በጀርመኑ ንጉሥ ላይ ተቃውሞ በመፃፋቸው ነበር። ኢትዮጵያ የጣሊያን ጥገኛ መሆኗን በውጫሌ ስምምነት ላይ መፈረሟ እየታወቀ የጀርመኑ ንጉሥ በቀጥታ ከምኒልክ መቀበሉ ከተለያዩ ሀገራት ውል እንዳፈረሱ ተደርጎ ተፃፈባቸው።
ልዑል ራስ መኮንን በወቅቱ በጣሊያን ሀገር በጉብኝት ላይ ነበሩ እና ጋዜጦቹ ስላስነበቡት ጉዳይ ተረዱ። ወደ ኢትዮጵያ በተመለሱ ጊዜም የውሉን መበላሸት ለዐፄ ምኒልክ አሳወቁ። ብዙም ሳይቆይ የጣሊያን ጋዜጦች ያዋከቧቸው የጀርመኑ ንጉሠ ነገሥት ለዳግማዊ ምኒልክ የፃፉላቸው ደብዳቤ ደረሳቸው። ለማንኛውም ጉዳይ መነጋገር የሚቻለው በውጫሌው ስምምነት መሰረት በኢጣሊያ መንግሥት አማካይነት መሆኑን የሚገልፅ ደብዳቤ ደረሳቸው። ይህም ደብዳቤ የመጣላቸው በጣሊያን በኩል ነበር።
ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ምኒልክም በዚህ የአንቶኔሊ ቅጥፈት ተቆጥተው እና አዝነው ስምምነቱን እንዲያስተካክል አለበለዚያ እንደሚሰርዙት በጨዋ ደንብ ጠየቁት። እርሱ ግን በእብሪት ተሞልቶ በጀ ሊል አልቻለም። ስለሆነም ዐፄ ምኒልክ እውነታውን የሚገልፅ ደብዳቤ በማዘጋጀት ለሁሉም የዓለም መሪዎች ስምምነቱን መሰረዛቸውን እወቁልኝ በማለት አሰራጩ። ነገር ግን ከአውሮፓ መሪዎች ለጣሊያን የወገኑ ምላሾች ደርሷቸው። እንዲያውም ኢትዮጵያ የጣሊያንን ሞግዚትነት ተቀብላ ከመቀጠል የተሻለ አማራጭ አለመኖሩን ለዐፄ ምኒልክ ምክር አዘል መልእክት ላኩላቸው። ሁሉም ምዕራባውያን ኢትዮጵያን ከዷት። በአውሮፓውያኑ የተበሳጩት ዐፄ ምኒልክ ግን፣ “እኔ ግን እንኳን ለአንድ እና ለሁለት እልፍ ሰው የኢጣሊያ ሀገር ሰው ሁሉ ቢመጣ፣ የኢጣሊያን ጥገኝነት ይቀበላሉ ብለህ አትጠርጥር ።” በማለት ሙሴ ኢልግ ለሚባል በአውሮፓ ላለው የቀድሞ የቅርብ ወዳጃቸው በግል ፅፈውለት እንደነበር ጳውሎስ ኞኞ ፅፎት ይገኛል።
ዐፄ ምኒልክ ምንም እንኳን የጣሊያን ክህደት፣ የአውሮፓ መንግሥታት አድመኛነት ቢያስቆጣቸውም ነገሩን በሰላም ለመፍታት ብዙ ጥረት አደረጉ። ነገር ግን የጣሊያኑ ተወካይ ተደራዳሪ ጭራሽ የሚያበሳጭ ንቀት የተሞላበት ምላሽ ሰጠ። ስምምነቱ እንደማይስተካከል አለበለዚያ የጣሊያን መንግሥት መብቱን በሀይል ለማስከበር እንደሚገደድ በድፍረት ሲናገር የሰሙት እቴጌ ጣይቱ ከምኒልክ በላይ ተቆጡ እና “የዛሬ ሳምንት አድርገው። በዚህ የሚደነግጥልህ የለም። ሂድ የፎከርክበትን አድርግ። እኛም የመጣውን እናነሳዋለን። እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር ሰጥቶ ሀገሩን የሚያድን ሰው በዚህ የሌለ እንዳይመስልህ። የገዛ ደሙን ገብሮ ለገዛ ሀገሩ መሞት ጌጥ ነው፣ እንጂ ሞት አይደለም። አሁንም ሂድ አይምሽብህ። የፎከርክበትን በፈቀድከው ጊዜ አድርገው። እኛም እዚህ እንቆይሃለን” በማለት ጮሁበት።
የእቴጌ ጣይቱ ቁጣ ያስደነገጠው አንቶኔሊ ወጥቶ ሄደ። የምኒልክ ቁጣ ከፊታቸው ይንቀለቀል ነበር። ጦርነት አይቀሬ መሆኑ የገባቸው ንጉሡ ወዲያው ወታደራዊ ዝግጅት እንዲደረግ አዘዙ። ይህ በእንዲህ እያለ ወራሪው የጣሊያን መንግሥት የተለያዩ የትግራይ ከተሞችን እየወረረ ብዙ ከተሞችን ያዘ። የዐፄ ምኒልክ ትእግስት ከዚህ በላይ ሊቀጥል አልቻለም፣ ወዲያው የክተት ነጋሪት አስመቱ። በጥቅምት እኩሌታ ወረኢሉ እንገናኝ የሚል ቀጠሮ ለሀገራቸው ህዝብ አደረሱ። ያኔ የኢትዮጵያውያን ቁጣ ከሁሉም አቅጣጫ ነደደ፣ እናም የንጉሡን ጥሪ ተቀብሎ አዋቂ፣ ህፃን፣ ወንድ፣ ሴት ሳይለይ ወደ አድዋ ተመመ።
ከአራቱም አቅጣጫዎች ወታደሮቻቸውን ይዘው የገሰገሱት የጦር መሪዎች ወረኢሉ በቀጠሮው መሰረት ደረሱ። ወረኢሉ ከንጉሡ ጋር አብረው ለጥቂት ጊዜ መከሩ። ማድረግ ያለባቸውን የጦር ስልት ነድፈው አጠቃላይ ዝግጅታቸውን እንደጨረሱ ወደ ትግራይ ዘመቻው ቀጠለ።
የአማባላጌው ጦርነት የመጀመሪያው ጦርነት ነበር። በፊታውራሪ ገበየሁ የሚመራው የኢትዮጵያ ሰራዊት የጣሊያንን ጦርነት አርበደበደው። የጣሊያን መድፍና መትረየሱ ሳይበግራቸው ለነፍሳቸው የማይሳሱት ጀግኖች ኢትዮጵያውያን እያሳደዱ ወቀጡት። የጣሊያን ሰራዊት አፈግፍጎ መቀሌ በመግባት ጠንካራ ምሽግ ሰርቶ ተቀመጠ።
የመቀሌውም ምሽግ ተሰብሮ ለመግባት ብዙ ዋጋ ስላስፈለገ ጀግናዋ እቴጌ ጣይቱ የውጊያ ስልት ዘየዱ። ወደ ጣሊያን ጦር ምሽግ ድረስ ይፈስ የነበረውን ወንዝ አቅጣጫ በማስቀየር በማስጨነቅ ለማፍረክረክ የወጠኑት ስልት ውጤታማ ነበር። የመቀሌው ምሽግ ተሰበረ።
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ከሌሊቱ 11 ሰዓት የአድዋው ጦርነት ተጀምሮ ከፍተኛ ውጊያ ሲደረግ ዋለ። ቆፍጣኖቹ የኢትዮጵያ ጀግኖች እንደመብረቅ እየተወረወሩ በጠላት ላይ ወደቁበት። እሳት ይተፉ በነበሩት መድፎች፣ ያለማቋረጥ በሚንጣጣው መትረየስ መሀል ጀግንነትን የናቁት ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ክብር ለነፃነት እየፎከሩ እና እየሸለሉ በደስታ ተፋለሙ፤ ተሰዉ።
ያ ምስራቅ አፍሪካን ሊያስገብር እጅግ የዘመነው የኢጣሊያ ሰራዊት በኢትዮጵያዊያን ጀግንነት ተደቆሰ። በአንድ ጀምበር ጀነራል አልቤርቶኒ እና ወታደሮቹ ተማረኩ፣ ጀነራል ባሪያቴሪ ነፍሱን ለማዳን ወደ አስመራ ሸሸ። በርካታ ወታደሮቹ ተሰውተው በርካቶች ተማርከው፣ የአድዋ ጦርነት በአንድ ቀን በድል ተደመደመ።
አድዋ ለመላው አውሮፓ ሀፍረት ለጥቁር ሕዝብ ትልቅ ኩራት ሆኖ ተመዘገበ። የአለም የፖለቲካ ታሪክ ተቀየረ፣ የቅኝ አገዛዝ ህልም ተሰበረ። አድዋ፣ የነፃነት ምልክት ሆኖ፣ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያን ድል ሆኖ ለዘላለም ይታወሳል። ዘላለማዊ ክብር ለጀግኖቻችን።
(መሠረት ቸኮል)
በኲር የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur