የቀደሙ የድል ባለቤቶች አካሄድ ለነገዋ ኢትዮጵያ

0
218

የኢትዮጵያውያን የጋራ መግባቢያ መድረክ፣ የመተባበር እና የአንድነት ውጤት ማስመስከሪያ – ዓድዋ:: የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊ ማንነት ዘመናትን ጸንቶ እንዲኖር አድርጓል:: የኩሩ ታሪክ ማስመስከሪያ ሆኖም ይነሳል:: ለጥቁር ሕዝብ ነፃነት እና እኩልነት መሰረትን ጥሎ ያለፈ ታላቅ ድል ነው::
“የኢትዮጵያ መንግሥት ከውጭ ሀገራት መንግሥታት ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግሥት አማካኝነት ማድረግ ይኖርበታል” የሚለው የውጫሌ ስምምነነት አንቀጽ 17 የጣሊያንኛ ትርጓሜ ኢትዮጵያን በእጅ አዙር ለቅኝ ግዛት የሚዳርግ በመሆኑ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነትን አላገኘም:: ጣሊያንም በእብሪት አሻፈረኝ ብሎ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ እንደገባ፣ ዐፄ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱም የገባውን የጣሊያን ወራሪ በገባበት ለመቅበር የክተት አዋጅ እንዳወጁ ታሪክ ያስረዳል::
ወትሮውንም “የውጭ ጠላት መጣ” በተባለ ጊዜ በአንድነቱ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ እግሩን ለጠጠር፣ ደረቱን ለጦር ሰጥቶ ሀገሩን ለማጽናት ከአራቱም የሀገሪቱ ክፍል ተነስቶ ወደ ዓድዋ ተመመ:: ኢትዮጵያም የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም እብሪተኛውን የጣሊያን ወታደር በአንድ ቀን በዓድዋ ሰንሰላታማ ተራሮች በመቅበር አኩሪ ገድልን ፈጸመች::
በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር መምህር መሰረት ወርቁ ሚያዚያ 2 ቀን 2015 ዓ.ም በዚሁ ጉዳይ ከበኲር ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያ በታሪኳ የገጠሟትን ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎች አልፋ ዛሬን እንድትደርስ፣ ነገንም እንድትሻገር ያደረጉ ምስጢራት የማይዳሰሱ ኀያል ውርሶች መሆናቸውን አብራርተዋል:: ቀዳሚው የድል መሰረት ኢትዮጵያዊ አንድነት እና አብሮነት እንደሆነም ተናግረዋል::
የኢትዮጵያ ሕዝብ ነባር እሴቱ ሃይማኖት፣ ጎሳ፣ ዘውግ፣ ሰፈር… የመለያየት ምክንያት ሳይሆን ሀገርን እንደ ሀገር የሚቀበል በሰውነት ላይ የተመሰረተ አስተሳሰብ ስለነበረ ለድል መብቃቱንም ምሁሩ አስረድተዋል:: የትውልዱ እንደ እሳት የሚንቀለቀል የነጻነት መንፈስ፣ የሕዝቡ በፈጣሪው ጹኑ አማኝ መሆን፣ የመሪዎቹ ጠንካራ እና የማይበገር ሥነ ልቦና ኢትዮጵያ በድል ጎዳና እንድትራመድ አስችሏታል::
የአፍሪካ ታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አየለ በከሪ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ በበኩላቸው የዓድዋ ድል ውጤት ሁሉም በሃይማኖት፣ በብሄር፣ በቋንቋ… ሳይለያይ ሀገሩን አስቀድሞ መነሳቱ እንደሆነ ይገልጻሉ:: ድሉ ለአውሮፓውያን ድንጋጤን፣ ለአፍሪካውያን ኩራትን ያቀዳጀ ስለመሆኑም አስታውሰዋል::
ከድል በኋላ ከሰባተኛው ዓመት ጀምሮ በየዓመቱ በአደባባይ የሚከበረው የዓድዋ ድል ዘንድሮም ለ128ኛ ጊዜ ይከበራል:: የኢትዮጵያውያን የአንድነት ምሳሌ የሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የካቲት 03 ቀን 2016 ዓ.ም መመረቁና በቀጣይ ለጎብኝዎች ክፍት መሆኑ ደግሞ አከባበሩ ከወትሮው የተለየ እንዲሆን እንደሚያደርገው ከኢሳት ዕለታዊ ፕሮግራም ጋር ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ተናግረዋል:: የአድዋ ሙዚየም በአዲስ አበባ መገንባቱ ታሪኩን በአሁኑ ትውልድ ላይ ይበልጥ በማስረጽ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለመፍጠር እንደሚረዳ ገልጸዋል:: ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ጎብኝዎችም ዓድዋን ከአፈ ታሪክ ባለፈ በጦርነቱ ወቅት የተማረኩ የጦር መሳሪያዎችን በተግባር አይተው እውነታውን በማረጋገጥ ለኢትዮጵያ የሚገባትን ቦታና ክብር እንዲሰጡ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ያምናሉ::
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዓድዋ ድል መታሰቢያ ከ128 ዓመታት በኋላ ኢትዮጵያን መስሎ እና አክሎ ለትውልድ እንዲተላለፍ ተደርጎ መገንባቱን ገልጸዋል:: ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው ጭቁን ሕዝብ የነጻነት በር የሆነውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ ለማሳነስና ለማራከስ የሚደረግ ጥረት መኖሩንም በዚህ ወቅት ገልጸዋል:: ይህ ግን የዓድዋ ዘማች ባለድሎችን አጥንት እና ደም ከማራከስ ተለይቶ የማይታይ መሆኑን አስገንዝበዋል::
ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሀሳብ በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ እና ቅርስ አስተዳደር መምህሩ መሰረት ወርቁ ማስረጃ እየጠቀሱ ያጠናክሩታል:: በዜጎች ውድ የሕይወት መስዋዕትነት እና በመሪዎች ብልጠት ዛሬ ላይ የደረሰችው ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጀግኖቿ ሳይዘከሩ እየተዋረዱ፣ ከአራቱ የኢትዮጵያ ማዕዘን ተሰልፈው የተገኘውን ድል ማሳነስ በጋራ ታሪክ ኢትዮጵያዊነትን ለማሻገር ዘመነኛ ፈተና ሆኖ ብቅ ማለቱን ያነሳሉ:: በጋራ ታሪክ በጋራ የምታግባባዋን ኢትዮጵያ አጽንቶ ላለመቆየት ሥረ ምክንያቱ የባዕዳን ተልዕኮ መሆኑን ደግሞ “ይህ ሀሳብ ከየት መጣ?” ለሚሉት ምላሽ እንዲሆን ጠቅሰዋል::
እንደ ታሪክ መምህሩ ገለጻ በተለይ ምእራባውያን አፍሪካን በቅኝ ግዛት ሊቀራመቱ ሲፈልጉ ይከተሉት የነበረው የመከፋፈል መንገድ ለዛሬ የኢትዮጵያ አንድነት ፈተና ሆኖ ዘልቋል:: ጣሊያን በዓድዋ ጦርነት የተከናነበችውን ሽንፈት ለማደስ ለ40 ዓመት ስትዘጋጅ የኢትዮጵያውያንን አንድነት እንዴት መበታተን እንደሚቻል፣ የትኛውን ማኅበረሰብ፣ እምነት… ማዕከል ማድረግ ለዕቅዳቸው ውጤታማነት እንደሚያበቃቸው አቅደው ሠርተዋል:: የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያም አልፎ የአፍሪካ እና የሌሎች ጥቁር ሕዝቦች ድል መሆኑ አሁንም ድረስ የሚያንገበግባቸው የውጭ ጠላቶች ባሉበት ወቅት በጋራ ታሪክ እና ድል አለመኩራት ለጠላት አባሪ ከመሆን የሚተናነስ እንዳልሆነ የታሪክ መምህሩ አስገንዝበዋል::
ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው ዓድዋን የምናወሳው ሀገርን ለማዳን የተሰለፉትን መሪውን አፄ ምኒልክን፣ እቴጌ ጣይቱን፣ የጦር መሪዎችን ለማስታወስ እና የሚገባቸውን ክብር ለመስጠት ነው ብለዋል:: ዓድዋ “አልገዛም! አልበገርም!” ያለ ሕዝብ ግዙፍ ታሪክ መሆኑንም ተናግረዋል::
ዓድዋ ቅኝ አገዛዝ ተስፋፍቶ አፍሪካን እንደ ቅርጫ ለመቀራመት ድግስ በተደገሰበት ወቅት በምንም አቻ ካልሆነ ወራሪ ጋር ፊት ለፊት ገጥሞ ድል ማድረግ የተቻለበት እንደሆነ ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል:: ይህም ዓድዋ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ጭቆናን እና ቅኝ ግዛትን ለሚታገል ሕዝብ ሁሉ መሰረት የጣለ መሆኑን አክለዋል::
እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለጻ በዓድዋ ታሪክ ላይ የተለያዩ ሐሳቦችን እየመዘዙ መጨቃጨቅ ለታሪኩ ባለቤት (ኢትዮጵያ) የማይመጥን ነው:: የዓድዋ ዘማች ባለድሎች በዘመናት ሲታወስ የሚኖር ድል የተቀዳጁት ቀድሞውኑ ልዩነቶች ሳይኖሯቸው ቀርተው ሳይሆን ከሀገር የሚቀድም ነገር እንደሌለ በመገንዘባቸው ነው:: በመሆኑም ኢትዮጵያውያን የሚለያይ ግንብ ከመገንባት ወጥተው ሀገር እና አህጉራትን ተሻግሮ በሌሎች ሀገራት በባለቤትነት እየተከበረ ያለውን ድል ጠብቀው ለትውልድ ማሻገር አለባቸው ብለዋል::
የአንድ ሕዝብ ታላቅነት የሚለካው ታሪክ ሠሪ በሆነ ሕዝብ ነው:: ይሁን እንጂ በዚህ ዘመን ችግሮችን ለመፍታት ቃታ መሳብ እየቀደመ መሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቷ፣ የዓድዋ መታሰቢያን የሀገር ፍቅር መማሪያ ማድረግ፣ ልዩነቶችንም በሰላማዊ መንገድ መፍታትን መለማመድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል::

Bekur /በኲር, [2/26/2024 4:34 PM]
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው የዓድዋ ዘማቾች የግል ግጭታቸውን ወደ ጎን በመተው የተወረረች ሀገራቸውን በጋራ ተጋድሏቸው ነጻ ለማውጣት በአንድነት መዝመታቸው ለድል እንዳበቃቸው አንስተዋል:: በመሆኑም የዓድዋ ዘማቾች ነጻነት እና ክብርን ለመጎናጸፍ የሄዱበትን ስልት ይዞ መጓዝ ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር የሚያደርጋት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል::
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንደገለጹት የአድዋ ድል የተገኘው በአንድነትና በሕብረት ነው:: በዘመኑ ከግዛትና ከሹመት ጋር በተገናኘ ልዩነቶች እንደነበሩ፣ ነገር ግን የመጣው የጠላት ኀይል ነጻነትን እና ሀገርን የሚያሳጣ በመሆኑ ልዩነቶቻቸውን በይደር ትተው በአንድነት ወደ አድዋ መዝመታቸውን አስታውሰዋል:: የአሁኑ ትውልድም ውስጣዊ አንድነቱን እንዲያስጠብቅ ከአድዋ አደራ እንዳለበት አስታውቀዋል:: የኢትዮጵያ ትልቅነት ነጻነቷ፣ ሉዓላዊነቷ እና አንድነቷ ላይ በመሆኑ የሀገር ምልክት የሆኑ እንደ ሀገር መከላከያ ሰራዊት ያሉ ተቋማትን እና ሌሎች ሐብቶችን መጠበቅ እንደሚገባ ገልጸዋል::
የጥቁር ሕዝብ ነጻነት መረጋገጥ ዋልታ የሆነው የዓድዋ ድል ለዛሬዋ ኢትዮጵያ ጥሎት ያለፈው አደራ ምን እንደሆነ በበርሊን ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር) ይገልጻሉ:: መምህሩ በኢትዮጵያን ዛሬ (ethiopiazare.com) ድረ ገጽ ላይ ባሰፈሩት ሀተታ ዲሞክራሲያዊት፣ የበለጸገች፣ ያማረች እና እያንዳንዱ ዜጋ በነፃነት የሚኖርባትን ሀገር መፍጠር ከዓድዋ አደራዎች መካከል ቀዳሚው መሆኑን ጠቅሰዋል::
ሕዝባዊ ፍቅር፣ በወንድማማችነት እና በእህትማማችነት ላይ የተገነባ ጠንካራ መስተጋብር እንዲፈጠር የዓድዋ ድል መንገድ መጥረጉንም ፀሐፊው ያነሳሉ:: አክለውም “የዓድዋ መልዕክት ሕዝቦቿ በነፃነት እና በመከባበር የሚኖሩባትን ሀገር መፍጠር ነው። የዓድዋ መልዕክት መንግሥት በታንክና በአውሮፕላን በመታጀብ ሕዝብን የሚያስፈራራበትን ሀገር ማየት ሳይሆን መንፈሱ የታደሰና በራሱ የሚተማመን ዜጋ መኮትኮት ነው” ሲሉ ሀሳባቸውን አስፍረዋል።
(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here