የሰላም እጦት – ለትውልድ ስብራት

0
214

በአማራ ክልል የተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ብቁ እና ተወዳዳሪ ዜጋ ለመፍጠር በሚያስችለው የትምህርት ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል:: ግጭቱ መፍትሄ ሳያገኝ ከስድስት ወራት በላይ መሻገሩ በተለይ በትምህርት ተደራሽነት እና ጥራት ላይ ጉልህ ተጽእኖ አሳድሯል::
የፀጥታ ችግሩ በክረምት ወቅት የሚከናወኑ የትምህርት ቤቶች የገጽታ ግንባታዎች እንዳይከናወኑ ከማድረግ ጀምሯል:: በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች በተሻለ ደረጃ ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ እንቅስቃሴ ቢጀመርም ግንባታዎቹ በሚፈለገው ልክ እንዳይጓዝ ማድረጉም በመንግሥት አካላት በተደጋጋሚ ተገልጿል:: አስፈላጊ የትምህርት ግብዓቶች ቀድመው ወደ ትምህርት ተቋማት እንዳይገቡ እክል ፈጥሯል:: በተለይ የተማሪ መቀመጫ ወንበሮች፣ የተማሪ መጻሕፍትና ሌሎች መማር ማስተማሩን ሊያግዙ የሚችሉ ግብዓቶች እንደቀደሙት ዓመታት ቀድሞ ወደ ትምህርት ቤቶች ማድረስ አልተቻለም::
ተማሪዎች ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በሁሉም ትምህርት ቤቶች እየተተገበረ ያለውን የአዲሡን ሥርዓተ ትምህርት ይዘት ቀድመው በመመልከት በሥነ ልቦና እንዲዘጋጁ ለማድረግ መጻሕፍትን በወቅቱ ማሰራጨት አልተቻለም:: በበጎ ፈቃደኞች የሚሰጡ የማጠናከሪያ ትምህርቶችን ለመከታተል በርካታ ተማሪዎች ዕቅድ የነበራቸው ቢሆንም በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት አለመቀጠላቸው ህልማቸው እንደ ጉም በኗል::
በየዓመቱ በወርሀ መስከረም አጋማሽ በአንድ ቀን በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ይጀመር የነበረው መማር ማስተማር ዘንድሮ ተገቷል:: የጸጥታ ችግሩ አሁንም ድረስ መቀጠሉን ተከትሎ አሁንም ድረስ የተማሪ ምዝገባ አድርገው መማር ማስተማር ለመጀመር እንቅስቃሴ ላይ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች መኖራቸው ለችግሩ በቂ ማሳያ ሆኖ ይነሳል::
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በትምህርት ዓመቱ ስድስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ቢያቅድም እስካሁን ያሳካው ከ59 በመቶ በላይ አለመሆኑ ለችግሩ ተጨማሪ ማሳያ ነው:: ይህ በእንዲህ እንዳለ ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎች ምዝገባ ለማከናወን የአንድ ወር ጊዜ ሰጥቷል:: ቢሮው አሁንም ትምህርት ያልጀመሩ አካባቢዎችን ትምህርት ለማስጀመር ከመምህራን እና ከትምህርት ተቋማት አመራሮች ጋር በባሕር ዳር ውይይት አካሂዷል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ ደሥታ አስራቴ በክልሉ የተፈጠረው ግጭት /ጦርነት/ በዞኑ በርካታ ትምህርት ቤቶች ከመማር ማስተማር ውጪ እንዲሆኑ ማድረጉን አስታውቀዋል። በዞኑ አንድ ሺህ 80 ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ የገለጹት መምሪያ ኃላፊው፣ በአሁኑ ወቅት በመማር ማስተማር ሂደት ላይ የሚገኙት 352 ብቻ መሆናቸውን ተናግረዋል። ከእነዚህ ውስጥ የአንደኛውን ወሰነ ትምህርት ያጠናቀቁ ደግሞ 307 ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው።
የሰላምና ደኅንነት ችግሩ የትምህርት ግብዓትን በወቅቱ ለትምህርት ቤቶች በማድረስ ውጤታማ የመማር ማስተማር ሥራ ለማከናወን ፈተና መሆኑንም መምሪያ ኃላፊው አስታውቀዋል:: የተማሪ መቀመጫ ወንበር በክልሉ ትምህርት ቢሮ ተሠርቶ እየተሰራጨ ቢሆንም በዞኑ ወደሚገኙ ወረዳዎች ለማድረስ የጸጥታ ስጋቱ እክል መፍጠሩን ገልጸዋል። የአሽከርካሪዎች ፈቃደኛ አለመሆን ደግሞ የትምህርት ግብዓትን በወቅቱ ለማድረስ ዋና ፈተና መሆኑን አንስተዋል:: የመጻሕፍት ክዘና ማዕከሉ ጎንደር መሆኑም ወደየወረዳዎች ተደራሽ ለማድረግ እንዳልተቻለ ተናግረዋል::
በምሥራቅ ጎጃም ዞን 924 የመጀመሪያ እና 72 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታውቋል:: በዞኑ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ በሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች 633 ሺህ 326 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር መታቀዱን የመምሪያው ኃላፊው አቶ ጌታሁን ፈንቴ አስታውቀዋል:: በዞኑ የሰፈነውን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ በስምንት ዞኖች የተማሪ ምዝገባ መደረጉን ገልጸዋል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ወጣ ገባ እያሉም ቢሆን በትምህር ገበታቸው ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ቁጥር ከ10 ሺህ የበለጠ እንዳልሆነ ለጸጥታ ችግሩ ማሳያ አድርገው አንስተዋል:: አሁንም አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ትምህርት ለመጀመር እንደሚሠራ ጠቁመዋል::
ችግሩ አማራ ክልል እንደ ሀገር ተወዳዳሪ እንዳይሆን የሚያደርግ በመሆኑ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታትን ማስቀደም እንደሚገባ መምሪያ ኃላፊው ጠቁመዋል:: የሕዝብ ጥያቄዎች ሊፈቱ የሚችሉት በተማረ ዜጋ በመሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ እና ለሰላምም ዘብ መቆም እንዳለባቸውም ጠይቀዋል::
አቶ መኳንንት አደመ የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ናቸው። በክልሉ በተፈጠረው የጸጥታ መደፍረስ ምክንያት ሦስት ሺህ የአንደኛ ደረጃ እና 225 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስካሁን ትምህርት እንዳልጀመሩ አሳውቀዋል።
በትምህርት ዘመኑ ስድስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዕቅድ ቢኖርም እስካሁን ማሳካት የተቻለው ሦስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብቻ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ማብራሪያ የትምህርት ጥራት ሊረጋገጥ የሚችለው ቢያንስ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሰረት የታቀደውን የትምህርት ይዘት ማጠናቀቅ ሲቻል ነው:: ነገር ግን አሁናዊ አካሄዱ ከዚህ በተቃራኒ መሆኑ አሳሳቢ ነው። ከዚህ በተጓዳኝ የሰሜኑ ጦርነት፣ በተፈጥሯዊ ሁኔታ የተከሰተው ድርቅና አሁንም ድረስ በክልሉ የቀጠለው ግጭት እንደ ሀገር የሚኖርን ተወዳዳሪነት እየገታ ነው::
በችግሮቹ የተጎዱት ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ መምህራንም ጭምር ናቸው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊው፣ ስለሆነም ብቁ እና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን ለማፍራት መምህራንንም በሥነ ልቦና ማብቃት እንደሚገባ ጠቁመዋል። ተማሪዎችም ሙሉ ጊዜያቸውን በትምህርት ቤቶች ካላሳለፉ ተወዳዳሪ ይሆናሉ ተብሎ ስለማይታሰብ ሁሉም ወገን ለሰላም ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

(ስማቸው አጥናፍ)
በኲር የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here