የአፍሪካ ሕብረት ከየት ወደየት?

0
163

የካ“ዛሬ የገጠመን ዕድል በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ መቼም ያልተገኘ ትልቅ ዕድል ነው:: በፊታችን የተደቀኑት ችግሮች ያንኑ ያህል ከፍ ያሉና ከባድ ናቸው:: ታሪክና ጊዜ የጣሉብን ከፍተኛ ኃላፊነት ሁላችንም ረጋ ብለን እንድናስብና እንድናመዛዝን ያስገድደናል:: የተነሳንበትን ከፍተኛ ተግባር በመልካም አከናውነን ብንገኝ ስማችንና ተግባራችን በታሪክ መልካም ስም ይኖረዋል:: ተግባራችንን ሳንፈጽም ብንቀር ግን ይታዘንብናል:: ስለዚህ እምነታቸውን የጣሉብንን ሕዝቦቻችን በሚመጡት ጊዜያት ውስጥ ከእኛ የሚጠብቁትን ሁሉ ለመፈጸም እንዲያበቃን ሁሉን የሚችለውን ፈጣሪያችን ጥበብንና አስተዋይነትን እንዲሰጠን እናምነዋለን፣ እንለምነዋለንም’’
ከላይ የሰፈረው ጽሑፍ ግርማዊ ቀዳማዊ ዐጼ ኃ/ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር ነው። ንግግሩ ደግሞ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥረት የአፍሪካ ሀገራትን ወደ አንድ ያሰባሰባቸውን የዚያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የአሁኑን የአፍሪካ ሕብረት ምሥረታ ላይ የተስተጋባ ነበር።
በመጀመሪያ መጠሪያው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአፍሪካ ሕብረት በሚል ስያሜውን የለወጠው ድርጅት የተመሠረተው ግንቦት 16 ቀን 1955 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ ነበር:: ለምሥረታው ዕውን መሆን ግርማዊነታቸው ላደረጉት ጉልህ ሚናም የአፍሪካ አባት የሚል መጠሪያም አስችሯቸዋል።
ለአብነትም ሰንዴይ ኦብዘርቨር የተባለው የናይጄሪያ ጋዜጣ ግርማዊነታቸውን “የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባት” በሚል ርዕስ ሰፊ ሐተታ ማስነበቡ ይታወሳል።

የሕብረቱ ዓላማዎች
ድርጅቱ ከመነሻው በቅኝ አገዛዝ ሥር የነበሩ አገሮችን ነጻ ማውጣትን ዓላማው አድርጎ ነበር የተመሠረተው። ከሕብረቱ ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ በወቅቱ ነጻ ሀገራት 32 ብቻ ነበሩ። ይህንን መነሻ በማድረግም ታዲያ በቅኝ አገዛዝ የሚማቅቁ የአፍሪካ ሀገሮች ነጻ እንዲወጡ ጥረት አድርጓል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ተለዋዋጩ የዓለም ነባራዊ ሁነት ሕብረቱም ከወቅቱ ጋር ራሱን እንዲያዛምድ ግድ ብሎታል። በዚህም ከስያሜ ለውጥ ጀምሮ ለአህጉሪቱ ሁለንተናዊ ዕደገት ይበጃል የተባሉ አጀንዳዎችን በማስቀመጥ እየተጓዘ 60 ዓመታትን የተሻገረ አዛውንት ሆኗል።
ይሁን እንጂ አዛውንቱ ሕብረት፣ ያከናወነው ተግባር ከዕድሜው ጋር የማይመጣጠን ሲሉ ይተቹታል። ለአብነት ደግሞ የአህጉሪቱ ሕዝቦች በድህነት ወልወል የሚኖሩ መሆናቸው፣ የግጭት ማዕከል መሆኗ፣ በመልካም አስተዳደር እጦት እና በመሰል ምክንያቶች መፈንቅለ መንግሥት በተደጋጋሚ የሚካሄድባት መሆን፣ የሀገራት መሪዎችም ስልጣንን የዕድሜ ዘመን ስጦታ አድርጎ የማየት አባዜ ውስጥ የገቡ መሆናቸው ተጠቃሾች ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ውስን ስኬቶችን ማስዝገቡን ከአፍሪካ ኒውስ ድረ ገጽ (Africa News) ያገኘነው መረጃ ይዘረዝራል። ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ እንዲወጡ ጉልህ ሚና መጫወቱ፣ ፈጣን ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት መመዝገቡ፣ የአህጉሪቱ ዓለም አቀፍ ተሰሚነት (በተለይ የዓለም ኢኮኖሚንና የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ አንድ አቋም መያዝ) የሕብረቱ ዋና ዋና ስኬቶች መሆናቸውን ነው የዘረዘረው።

የሕብረቱ አጀንዳዎች
ከዕቅድነት የተሻገሩ ባይሆኑም ሕብረቱ በሂደት ምላሽ ያገኛሉ በሚል በርካታ አጀንዳዎች አሉት። አጀንዳ 2063 የሚባለው ደግሞ በርካታ አፍሪካዊ ጉዳዮችን ያካተተ የሕብረቱ ዕቅድ ዋነኛው ነው። ይህም በ50 ዓመታት ውስጥ አሳካቸዋለሁ ያላቸው ግቦች የተያዙበት ግዙፍ ውጥን ነው። በአካታች ዕድገትና ዘላቂ ልማት ላይ በመመሥረት የበለፀገች አፍሪካን ማየት፣ በፓን አፍሪካኒዝምና በአፍሪካ ህዳሴ ላይ የተመሠረተች የተሳሰረች አህጉርና የፖለቲካ አንድነትን ማምጣት፣ መልካም አስተዳደር፣ ዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ፍትሕና የሕግ የበላይነት የሰፈነባት አፍሪካን ማረጋገጥ፣ ሰላማዊና ደህንነቷ የተረጋገጠላት አፍሪካን ማየት፣ ጠንካራ ባሕላዊ ማንነትት፣ የጋራ ቅርስ፣ የጋራ እሴትና ሥነ ምግባር የሚታይባት አፍሪካን መፍጠር፣ ልማቷ በሰዎች ላይ ያተኮረ፣ በአፍሪካውያን አቅም፣ በተለይም በሴቶችና ወጣቶች ላይ የተመረኮዘ፣ እንዲሁም ልጆች እንክብካቤን የሚያገኙባትን አፍሪካ ማረጋገጥ፣ ብሎም አፍሪካን ጠንካራ፣ የተባበረች፣ አይበገሬና ተፅዕኖ ፈጣሪ ዓለም አቀፋዊ ተዋናይና አጋር ማድረግ የሚሉ የተለጠጡ ዕቅዶችን ያካተተ ነው።
ዕቅዱ ከታቀደ ታዲያ ዐሥር ዓመታትን ቢሻገርም አህጉሪቱ ግን አሁንም በድህነት፣ በግጭት፣ በጦርነት፣ በአምባገነናዊ የሀገራት መንግሥታዊ ሥርዓት፣ በመፈንቅለ መንግሥት፣ በሙስና እና በመሰል ችግሮች ማዕከልነት ቀጥላለች።

ሕብረቱ የዕድሜውን ያህል ለምን አልተሳካለትም?
የሕብረቱ ጉባዓ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል። በወቅቱ ንግግር ያደረጉት የሕብረቱ ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሕማት ሽብርተኝነት፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ድርቅና ድህነት ብሎም የፀጥታ ችግር አሁንም አፍሪካን አላራምድ ያሉ አሳሳቢ ችግሮች ናቸው ብለዋል። ኢ – ሕገ መንግሥታዊ የመንግሥት ለውጦች መበራከት መሪዎቹ ያን የመመከት አቅም እንደሚያስፈልጋቸው ጠቋሚ መሆኑንም ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም የትብብር፣ የአፍሪካ አንድነት እና የፓን አፍሪካን (የአፍሪካዊነት) ስሜት እየተዳከመ መምጣቱንም ነው ያነሱት።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በተለይ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ግጭት ውስጥ መገኘታቸው፣ በብዙ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት መፈንቅለ መንግሥት መበራከት እና መሰል ችግሮች የሕብረቱን ጥንካሬ ጥያቄ ውስጥ የያስገባ መሆኑን ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት።
በዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ፕሮፌሰር ማቻሪያ ሙኔን ለዶይቼ ቬለ የሕብረቱን አሕጉራዊ መፍትሔ ሰጪነት በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዚህም በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት በተመለከተ ድርጅቱ እያደረገ ስላለው ጥረት የተጠየቁት ፕሮፌሰሩ፣ ጉዳዩ በሕብረቱ ጥንካሬ ላይ የሚወሰን መሆኑን በማንሳት፣ ሕብረቱ የአባል ሀገራቱን ችግሮች በመፍታት ረገድ ችግር ያለበት መሆኑን ተናግረዋል።
ሕብረቱ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ከመሥራት ይልቅ የተለጠጠ ዕቅድ በመያዝ የማሳካት አቅሙን የማያሳይ መሆኑንም ባለሙያዎች ሐሳብ ያቀርባሉ።
ከላይ የተዘረዘሩት በርካታ ችግሮች መኖራቸው እየታወቀ ታዲያ ሕብረቱ በሚያደርጋቸው ጉባዓዎች አሳሳቢ ናቸው ከማለት በዘለለ አንዳች ጠብ የሚል መፍትሔ ባለመስጠቱ ብዙዎች ጥርስ የሌለው አንበሳ ሲሉ ነው የሚጠሩት።
አልጀዚራ እንዳስነበበው የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጡ ጀምሮ (አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡት በ1960ዎቹ መሆኑን ልብ ይሏል) 200 ያህል የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ተደርገዋል።
በቡርኪና ፋሶ፣ በጊኒ ቢሳው፣ ማሊ፣ ጊኒ፣ ማዳጋስካር፣ ኮት ዲቯር፣ ቶጎ፣ ጊኒ፣ ሱዳን፣ ዚምባብዌ፣ መፈንቅለ መንግሥት የተደረገባቸው ወይም የተሞከረባቸው ሀገራት ናቸው ሲል አብነት አንስቷል። በአጠቃላይ “አፍሪካ የመፈንቅለ መንግሥት ወረርሽኝ ማዕከል ሆናለች” ነው ያለው ዘገባው። ለዚህ ሁሉ መሠረታዊው ምክንያት ደግሞ የዴሞክራሲ መቀጨጭ መሆኑን ጠቅሷል።በዚህ ሁሉ ሂደት ታዲያ የሕብረቱ ሚና ከዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ውሳኔውም ተፈጻሚ ሲሆን አይታይም። ለዚህ በምክንያትነት የሚነሳው ደግሞ ሕብረቱ ከቀጣናዊ ተቋማት ጋር ያለው ግንኙነት በበታችነት የሚያሳየው እንደሆነ ይጠቀሳል። ለአብነትም ከዓመታት በፊት የሕብረቱ የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት በማሊ ላይ ያስተላለፈው የዕግድ ውሳኔ በኤኮዋስ አለመከበሩ ይታወሳል።
በተመሳሳይ በጀት የሕብረቱን ውጤታማነት ፈተና ውስጥ ካስገቡት መካከል አንዱ እንደሆነ ይነገራል። ከአፍሪካ ኒውስ ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው፣ ከሕብረቱ ጠቅላላ በጀት በአባል ሀገሮች የሚሸፈነው 38 በመቶ ብቻ ነው። 61 በመቶ ደግሞ ከአጋሮች የሚገኝ ነው። ከዚህ ባለፈም ሁሉም አባላት በታማኝነት የሚጠበቅባቸውን መዋጮ አያደርጉም። ይህም በሌሎች ላይ ጥገኛ እንዲሆን አይሰጡም።
የአፍሪካ አሕጉር አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ገደማ ሕዝብ አላት። በ55 ሀገራት ይህንን ያክል ሕዝብ የሚወክለው ሕብረቱ ታዲያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያለው ተደማጭነትና ውክልና አናሳ መሆኑ በስኬት ላለመጓዙ የሚነሳ ምክንያት ነው። የአፍሪካ ሕብረት ዋነኛ ድክመት ለውጭ ርዕዮተ ዓለም ተጋላጭ እንደሆነ በማንሳት ዋነኛ ድክመት በማለት ብዙዎች ይተቻሉ።

በ37ኛው ጉባዔ ምን ተባለ?
37ኛው የሕብረቱ መደበኛ ጉባዔ ከሰሞኑ በሕብረቱ የምሥረታ ቦታ እና መቀመጫ በአዲስ አበባ ከተማ ተካሂዷል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአፍሪካ ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በተለያዩ ችግሮች (ጦርነትን ጨምሮ) ከትምሕርት ገበታ ውጪ ሆነዋል። ይህን ታሳቢ በማድረግም ሕብረቱ ትኩረቱን ትምሕርት ላይ አድርጎ ነበር። ሠላም፣ ፖለቲካ፣ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲም ተጨማሪ አጀንዳዎቹ እንደነበሩ ከሕብረቱ ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
አፍሪካ በመፈንቅለ መንግሥት፣ በጦርነት፣ በሽብርተኝነት፣ በድህነት፣… እየታመሰች በምትገኝበት ወቅት የተካሄደው ጉባዔው የእስራኤል – ጋዛ ጦርነት ጎልቶ የተደመጠበት እንደነበር ተነግሯል። ሕብረቱም ከፍልስጤም ጎን እንደሚቆም ተገልጿል። እስራኤልን ተጠያቂ ለማድረግ የተጀመረውን የደቡብ አፍሪካን እርምጃ በማድነቅም መሪዎቹ በጋራ ዕውቅና ሰጥተዋል።ቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም

(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here