ከምግብ ባሻገር

0
262

የአማራ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃን ዋቢ አድርጎ በዓመታዊ መጽሔቱ እንዳስነበበዉ ሀገራችን 70 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ዳልጋ ከብቶች፣ 42 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን በጎች፣ 52 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ፍየሎች፣ ስምንት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ግመሎች፣ ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ፈረሶችና 57 ሚሊዮን ዶሮዎች ይገኝባታል:: ይህም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ያላት ሀገር ያደርጋታል። ኢትዮጵያ ካላት የእንስሳት ሀብት ውስጥ 1/3ኛው ወይም 33.3 በመቶዉ በአማራ ክልል እንደሚገኝም መረጃዉ ያሳያል::
የአማራ ክልል ሁሉንም ዓይነት መልክዓ ምድር እና የአየር ንብረት በተፈጥሮ የተሰጠው ነው። ይህም የተለያዩ የእንስሳት ዝርያዎችን ለማርባት ተስማሚ አድርጎታል:: የእንስሳት ሀብት ልማት እርባታ፣ ማድለብ፣ የወተት ላም፣ የዶሮ እርባታ፣ የስጋ ዶሮ፣ የእንቁላል ዶሮ እና ጫጩት ማሳደግን ያካትታል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ 70 በመቶው ያህሉ የክልሉ አካባቢ ለዶሮ እርባታ ምቹ መሆኑን የአማራ ክልል እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ጽ/ቤት የዶሮ ሀብት ልማት ባለሙያው አቶ ሙላቱ ዳኘው ያብራራሉ:: ይሁን እንጂ የእንስሳት ምርት ዝቅተኛ መሆን፣ የገበያ ትሥሥር ችግር፣ በዘርፉ ቀልጣፋ አገልግሎት አለመኖር እና የተሟላ የግብዓት አቅርቦት አለመቅረብ በፀጋው ልክ ተጠቃሚ መሆን እንዳልተቻለ በምክንያት ያነሷቸው ናቸው::
የእንስሳት ልማት ዘርፍ (በተለይ ዶሮ እርባታ) ገበያ ተኮር እየሆነ በመምጣቱ በዘርፉ ለተሰማሩ ዜጐች ከድሕነት መውጫ እንደ ዋነኛ አማራጭ ሆኗል። ለበርካቶችም የሥራ ዕድል የፈጠረ ዘርፍ ነው። ይሁን እንጂ የተሻሻለ የዶሮ ዝርያ እጥረት፣ ባሕላዊ የአረባብ ዘዴ፣ የጤና አጠባበቅና የመኖ አቅርቦት በቂ አለመሆን የዘርፉ ፈተናዎች ናቸው።
የሀገራችን የዶሮ ዝርያዎች የአካባቢውን ሥነ ምሕዳር ለዘመናት ተላምደው የሚኖሩ ናቸው፣ ምርታማነታቸው ሲታይ ግን በጣም አነስተኛ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ:: ይሁን እንጂ የዶሮ ሀብት ልማት በአጭር ጊዜ ገቢ የሚያስገኝ በመሆኑ ተመራጭ ያደርገዋል:: በኢትዮጵያ ያለው የዶሮ እርባታ በኢኮኖሚው እንዲሁም በሕዝቡ ኑሮ ከፍተኛ ሚናን እየተጫወተ ይገኛል::
ዘርፉ ለብዙ ዜጐች የገቢ ምንጭና ለተመጣጠነ ምግብ አገልግሎት እየዋለ ይገኛል:: ከምግብነትና ከገቢ ምንጭነት አልፎ ከዶሮ የሚገኘው ፍግ ወይም ፅዳጅ ለሰብል ምርት ጠቃሚ ማዳበሪያ በመሆን ለግብርና ምርት ማደግ አስተዋፅኦው ከፍተኛ ነው።
የዶሮ እርባታ በሁሉም የሀገራችን ክፍል እየተስፋፋ የሚገኝ ቢሆንም መስኩ ካለው ዕምቅ ሀብት አንፃር ዜጎችን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ቀሪ ሥራዎችን ይጠይቃል::
የአማራ ክልል ሥራና ስልጠና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አወቀ ዘመነ በቀላሉ ወደ ዘርፉ ለሚቀላቀሉ ሥራ ፈላጊዎች አዋጭ ስለመሆኑ ያስረዳሉ::
ሠርቶ ለመለወጥ እና ሀገርን ለመጥቀም የሥራ ፍላጎትን ማወቅ፣ ነባራዊ ሁኔታን መረዳት፣ ፀጋን ለይቶ ማወቅና ተቀናጅቶ መሥራት መሠረታዊ ጉዳይ እንደሆኑ ያብራራሉ:: በዶሮ እርባታ ለሚሰማሩ ግለሰቦች በትኩረት መታየት ያለባቸው መሰረታዊ ነገሮች የተሻለ መኖ፣ ጤና፣ መሥሪያ ቦታ፣ መነሻ ካፒታል፣ የሚራቡበትና የሚኖሩበት ቦታ ከዶሮ ቁጥር ጋር የተመጣጠነ መሆን እንዳለበት ያብራራሉ:: በዘርፉ ለተሰማሩ ዜጐች የቦታ አቅርቦትና መሰል ችግሮች ስለሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የጋራ ስራ ይጠይቃል።
የዶሮ ሀብት ልማት አንድ የቢዝነስ አማራጭ ተደርጎ ይወስዳል ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል እንስሳትና ዓሳ ሀብት ልማት ጽ/ቤት የዶሮ ሀብት ልማት ባለሙያው አቶ ሙላቱ ዳኘው ናቸው። የአማራ ክልል ለዶሮ እርባታ ተስማሚና ምቹ መሆኑን በማንሳት፣ በዶሮ ማሳደግ ሥራ የተሰማሩ ዜጐች ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሆኑና ዘርፉም አዋጭ መሆኑን ይናገራሉ::
የዶሮ እርባታ በአጭር ጊዜ ገቢ የሚያስገኝ፣ በትንሽ ካፒታልና በተወሰነ ቦታ የሚሠራ፣ ፆታ የማይለይ፣ የኘሮቲን መጠኑ ከፍ ያለ እና ለሥርዓተ ምግብ ተስማሚ በመሆኑ ሊሠራበት ይገባል ይላሉ ባለሙያዉ።
በአጭር ጊዜ ገንዘብ ስለሚያስገኝ ወጣቶች ወደዚህ የሥራ ዘርፍ ቢሰማሩ ሕይወታቸውን ብሎም ቤተሰባቸውን ማገዝ ይችላሉ ባይ ናቸው:: ይህ በእንዲህ እንዳለ በሰላም እጦቱ ምክንያት የመኖ ዋጋ መጨመሩን አንስተዋል። ይህም በዘርፉ ለሚሰማሩ ዜጐች ፈተና በመሆኑ የጋራ ሥራ ይጠይቃል ብለዋል::
የገበያ ትሥሥርን ጨምሮ በዘርፉ የታዩ ችግሮችን በመፍታት ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እየተሠራ ይገኛል። ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋርም በቅንጅት መሥራትን ይጠይቃል ብለዋል::
የግብዓት አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት ከሌሎች አቅራቢዎች ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነ አመልክተው አርቢዎች እጃቸው ባለ ጥሬ ዕቃ (ለመኖ የሚሆን) እንዲመግቡ ግንዛቤ እየተፈጠረ ነው ብለዋል።
በዘርፉ ለተሰማሩ ዜጐች የተለያዩ የዶሮ ዝርያዎችን በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል:: የአካባቢያዊ የዶሮ ዝርያን ለማሻሻል በፓኬጅ ተቀርፆ እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል:: በተጨማሪም ዘርፉን ከከተማ ወደ ገጠሩ አካባቢ ለማስፋፋት እየተሠራ እንደሆነ አመላክተዋል::
ባለሙያው እንዳሉት የዶሮ እርባታን ሲታሰብ የአካባቢን ንፅህናን በመጠበቅ ከበሽታ መከላከል ዋናው ጉዳይ ነው። ክትባት መስጠትም ያስፈልጋል።
ዘርፉ በተለይ ድጋፍና ክትትልን ይጠይቃል:: ዶሮ አርቢውና አሳዳጊው በየደረጃው ካለ ባለሙያ ጋር ተቀራርቦ መሥራትን ግድ ይላል:: በተለይ የጫጩት አሳዳጊዎች ከምጥን መኖ ውጭ ሌላ መኖ መጠቀም እንደሌለባቸው ባለሙያው ምክረ ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

(መልካሙ ከፋለ)
በኲር የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here