ግጭት የለውጥ መነሻ የሚሆነው መቼ ነው?

0
271
ወጣትነት በሰው ልጅ የሕይወት ዘመን ውስጥ ወርቃማው የዕድሜ ክልል ነው:: ስለሆነም ከውስጣዊ በተጨማሪ ውጫዊው ፈተና የራሱ ተጽዕኖ የሚፈጠርበት ዘመን እና እውቀትን ለማስፋት ተጋድሎ የሚደረግበት ወቅት እንደሆነ ወርልድ ፕረስ ዶት ኮም (wordpress.com) በድረ ገጹ አስፍሯል::
ዩ ኤን ዲ ፒ እ.ኤ.አ በ2017 ባደረገው ጥናት 70 ከመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች መሆኑን ነው:: በዚህ የዕድሜ ክልል የሚፈጠር አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ክስተት በቀጣይ ሕይወት ሥነ ልቦናዊ እና ማህበራዊ ግንባታ ላይ የራሱ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ያብራሩልን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሥነ አዕምሮ ትምህርት ክፍል ኃላፊ እና መምህር መሰረት ጌታቸው (ዶ/ር) ናቸው::
እንደ ኃላፊው ገለጻ ወጣትነት አዕምሮ ብዙ አዳዲስ ነገር ለመሞከር፣ ለመማር እና ለመፍጠር የሚተጉበት የዕድሜ ክልል ነው:: ሃሳብን በማራመድ በኩልም ብዙ ግጭት የሚኖርበት ዕድሜ ነው::
ግጭት የሚባለው ደግሞ ሁለት እና ከዛ በላይ በሆኑ ኀይሎች በሃሳብ፣ በፍላጎት እና በግብ መካከል የሚፈጠር አለመግባባት እንደሆነ መሰረት ጌታቸው (ዶ/ር) ጠቁመዋል:: ይህ አለመግባባት ውጥረት ፣ግጭት ከፍ ሲልም ወደ አስከፊ ብጥብጥ ያድጋል::
እንደ ሥነ ልቦና ባለሙያው ገለፃ ታዲያ ግጭት ሁልጊዜ መጥፎ አይደለም:: ግጭትን በበጎ ከተጠቀምንበት ለለውጥ እና እድገት እንደ መነሻ ሃሳብ መቀያየሪያ መሳሪያ ማዋል ይቻላል:: ግጭት መጀመሪያ የሚመጣው ከግለሰብ ሥነ ልቦና ስለሆነ ጭንቀት፣ አለመግባባት ከፍ ብሎ ደግሞ በግጭት ምክንያት የሚፈጠር የአዕምሮ ችግር ያስከትላል:: ይህን ተከትሎም መጥፎን ብቻ የማሰብ፣ ማዳላት፣ ሰዎችን መፈረጅ፣ እንቅልፍ ማጣት፣ በጣም ተጠራጣሪነት…ይከሰታል:: ይሄ ስሜት ተጠራቅሞ ደግሞ በዙሪያው ካሉ ሰዎች ጋር እንዳይግባቡ እና እንዲርቁ ያደርጋል:: ይሄ ስሜት ደግሞ አዕምሮ ውስጥ ያለውን አስተሳሰብ ሁሉ ያውካል::
ሰዎች በግለሰብ ደረጃ አዕምሯቸው ከታወከ እንደ ማህበረሰብ ያላቸው ግንኙነት ይበላሻል ፤ ግጭት ሲጀምር እንደግለሰብ ባህሪን ይቀይራል፤ ሲያድግ ደግሞ ተፅዕኖው እንደማህበረሰብ እንደሚሆን ምሁሩ አስረድተዋል::
ይህ ማለት ከሰዎች ጋር ያለን መስተጋብር በማበላሸት ግንኙነታችን በጭቅጭቅ እና በንትርክ የተሞላ ያደርገዋል፤ በዚህ ግንኙነቱ ተገድቦ የማህበረሰቡ ባህል ሁሉ እንደሚጎዳ ማሰብ እና መኮነን ይሸጋገራል:: ዛሬ ላይ በሀገራችን እንደምናየው ይህ ስሜት አድጎ እንደማህበረሰብ ወደ መፈራረጅ እና ጽንፍ እስከ መያዝ ያደርሳል፤ ይሄ ሃይማኖት፣ ይሄ ማህበረሰብ ብሎ ወደ መጠላላት ይደረሳል::
እንደ ምሁሩ ማብራሪያ ግጭት እንደ ሰው ከሌሎች ሊያስፈልገው (ሊያገኝ) የሚችለውን ትብብር፤ እሱ ደግሞ እንደግለሰብ ሊያበረክት የሚችለውን ነገር የሚያበላሽ ደረጃ ላይ መድረስ የለበትም:: አብዛኛውን ግጭት ስናይ እንደማህበረሰብ ከሥራቸው፣ ከአካባቢያቸው፣ ከኑሯቸው እንዲፈናቀሉ ያደርጋልና::
“የወጣትነት የዕድሜ ክፍል በአዕምሮ ብዙ ነገር መሞከር፣ መማር፣ አዳዲስ ነገር ለመፍጠር የሚተጉበት ጥሩ የዕድሜ ክልል ነው” ካልን ወጣቱ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ በአሉታዊ መልኩ ሁኔታዎችን ካሳለፈ በቀላሉ ለብዙ ችግር ተጋላጭ ይሆናል:: ግጭትን የምናይበትም ሆነ የምንፈታበት መንገድም ከእውቀት እና ከልምድ ጋር ስለሚያያዝ በወጣትነት ጊዜ (ዕድሜ) ይሄ ልምድ ገና እየተገነባ ስለሆነ ተጽእኖው ከባድ ነው:: በግጭት ወቅት የተጎዱ ወጣቶች (ችግር የደረሰባቸውን) በአካል ፣ በስሜት እና በባህሪ ለይቶ መግለጽ ይቻላል::
በአካላዊ ደረጃ ግጭት ተፅእኖው ራስ ምታት፣ ጭንቀት፣ እንቅልፍ ማጣት ፣ ብዙ መተኛት ፣ ድካም ፣ የመሥራት ተነሳሽነት ማጣት ነው:: እነዚህ ተደማምረው ጤናን እስከማዛባት ይደርሳሉ::
ስሜት ላይ ደግሞ ትዕግስት የሌላቸው ፣በትንሹ የሚያዝኑ ፣ተስፋ የሌላቸው ፣ከብዙ ሰዎች የሚነጠሉ፣ ለሥራም ሆነ ለምግብ ፍላጎት የሌላቸው ወጣቶች ይታያሉ:: በባህሪ ደግሞ ጭቅጭቅ እና ክርክር የሚወዱ፣ በጣም ትንሿን ነገር አንስተው እያጎሉ በማውጣት ሌሎችን የሚኮንኑ ፣ ጠብ ፈላጊነት፣ ሥራን መቀያየር (እርካታ የሌላቸው) ከፍ ሲል ደግሞ ራሥን ሱስ ውስጥ የመደበቅ ሥሜት ይታይባቸዋል::
ችግሮቹ ከሰዎች ጋር ያላቸው ተግባቦት በጣም እንደሚያዛባ ማመን እንደሚገባ መሰረት ጌታቸው (ዶ/ር) ጠቁመዋል:: ለዚህ መውጫ መንገዱ ደግሞ ወጣቱ እንደ ግለሰብ ወደ ግጭት ሊያስገባ የሚችል ነገር ምንድን ነው? ብሎ በደንብ ወደ ውሥጥ ማየት፣ አለመፍራት፣ የሰዎች ሥሜት መለዋወጥን መረዳት፣ ራስን መንከባከብ እና ደስ በሚል ሁኔታ ውስጥ ለማስገባት መሞከር፣ ለወደፊቱ ጥሩ ነገር ማቀድ፣ በቂ እንቅልፍ መተኛት…ተገቢ ነው::
ነገሮችን እንደ አመጣጣቸው በሚቻል አግባብ ለመረዳት መሞከር ተገቢ ነው፤ ሰዎች ለሌሎች የሚሰጡትም የሚቀበሉትም ነገር እንዳለ አምኖ ራስን ብቻ ሳይሆን እንደማህበረሰብ የሚፈለግብኝ ምንድን ነው? ብሎ ራስን ለዛ ማብቃት አስፈላጊ እንደሆነም መሰረት ጌታቸው (ዶ/ር) ይገልፃሉ::
ይሄ ካልሆነ ግን ወደ ቀጣይ ደረጃ ማለትም የሌሎችን እገዛ ፍለጋ መሄድ ይገባል ያሉት የዘርፉ ምሁር፤ በግለሰብ ጭንቀት ውስጥ የሚፈጠርን ችግር ሊፈታ የሚችለው ጓደኛ፣ የሃይማኖት አባት፣ ቤተሰብ… ምክር ነው:: “ተሳስተሀል/ሻል አልተሳሳትክም/ሽም” የሚለውን በመነጋገር የሰው ምክርን መጠቀም ካልተቻለ ግን ወደ ባለሙያ ምክክር በመሄድ ከተቻለ የግጭትን ጉዳት ማስታገስ፣ ማጥፋትም ይቻላል::
እንደ ምሁሩ ገለጻ ማህበረሰቡም ወጣቱም መረዳት ያለበት አለመግባባትን በራሱ ባለመግባባት መጨረስ እንደሚቻል ነው:: ግጭትን መረጃ በመቀያየር ለመረዳዳት መሞከር እንጂ ከዛ አልፎ ወደ ስሜት እንዳይሄድ ጥረት ማድረግም ተገቢ ነው::
ክስተቶች ወደ ግጭት የሚያመሩት የሰዎችን እይታ ባለማክበር ነው:: ነገር ግን ወደ ግጭት ሳያመሩ ባለመስማማት መስማማት እንደሚገባ መሰረት ጌታቸው (ዶ/ር) ጠቁመዋል:: ግጭት የሃሳብ ሲሆን ደግሞ ለለውጥ ይረዳልና የሚዳብርበትን መንገድ ፈልጎ መወያየት፣ መከራከር፣ በሃሳብ መፋለጥ… መልመድ ይገባል ይላሉ::

(ማራኪ ሰውነት)
በኲር ታኀሣሥ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም
በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘወትር ሰኞ የምትታተመውን የበኲር ጋዜጣን ሙሉ ፒዲኤፍ
በhttp:// www.ameco.et/Bekur
በቴሌግራም – https://t.me/bekur123 ላይ ማግኘት ይችላሉ። 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here