በዕውን ያልተፈጠረ ድምጽ አስቸግርዎታል?

0
260

“ወጣቱ በወላጆቹ ጥሩ እንክብካቤ እየተደረገለት ትምህርቱን በንቃት ይከታተላል:: በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ደረጀ ትምህርትም ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ ዩኒቨርሲቲ ገባ:: በተለያዩ መመዘኛዎች የተሻለውን የትምህርት ዘርፍ መከታተልም ጀመረ፤ በቆይታውም ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገብ ቻለ:: አራተኛ ዓመት ሲደርስ ግን ራሱን ማግለል እና መጠራጠር ጀመረ:: ከጓደኞቹ እና ከሚያውቃቸው ጋር መጣላት አዘወተረ:: ትምህርቱ ከዳር ሳይደርስ አቋረጠ::
ነገን በእሱ ተስፋ የጣሉ ወላጆቹ፣ እህቱ እና ሌሎችም ተስፋቸው መከነ:: በመንግሥት ሥራ የሚተዳደሩት ወላጆቹ በልጃቸው ጤና መቃወስ ግራ ተጋቡ:: አባቱ የትምህርት ደረጃቸውን ለማሻሻል ትምህርት ጀምረው ነበር፤ ነገር ግን በተፈጠረው ችግር ትምህርታቸውን አቋረጡ:: በዩኒቨርሲቲ ተማሪው ያልተጠበቀ ነገር ቤተሰቡ ለከፋ ምስቅልቅል ተዳረገ:: ለአንድ ዓመት ቤተሰቡ ሁሉን ሥራ ትቶ ልጁን ለማዳን ትልቅ ዋጋ ከፈሉ:: ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ዘመናዊ ሕክምና መጡ::”
ከባድ የአዕምሮ ህመም በጤና፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ መስተጋብር እና በማኅበረሰብ ዕድገት ሊያደርሰው የሚችለውን አሉታዊ ተጽእኖ ለማስረዳት ታሪኩን ያጋሩን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአዕምሮ ሕክምና ስፔሻሊስት ሃኪሙ ዶ/ር ግዛቸው አስናቀ ናቸው::

ለመሆኑ ከባድ የአዕምሮ ህመም (ስኪዞፍሬኒያ) ምንድን ነው?
ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሕይወት ገጾች ፕሮግራም ላይ ቆይታ ያደረጉት ዶ/ር ግዛቸው አስናቀ በሚያስከትሉት ጫና፣ በሚቆዩበት የጊዜ ርዝማኔ እና በሚያሳዩት የህመም ፀባይ በዓለም ላይ ከ400 በላይ የአዕምሮ ህመም አይነቶች ይገኛሉ:: ከባድ የአዕምሮ ህመም (ስኪዞፍሬኒያ) ደግሞ አደገኛው የአዕምሮ ህመም አይነት ነው። እንደ ስፔሻሊስቱ የዚህ አይነቱ የአዕምሮ ህመም ዋና መገለጫ የተዛባና ወጣ ያለ አረዳድ፣ ግንዛቤ እና አተያይ መኖር ነው::
የአዕምሮ ህመም የተከሰተበት ሰው ቀድሞ ከነበረው ማንነት ውጭ የበዛ ወይም ከልክ በላይ ያነሰ ባህሪ ያሳያል:: በዚህ ጊዜ የንግግር፣ የአካል እና የስሜት እንቅስቃሴ ለውጦች መታየት ይጀምራሉ:: የጊዜ ቆይታው ደግሞ ስድስት ወር እና ከዚያ በላይ እንደሚሆን ዶ/ር ግዛቸው አመላክተዋል::

መነሻው ምንድን ነው?
ሁሉም የአዕምሮ ህመም አይነቶች መነሻቸው ሥነ ሕይወታዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ማኅበራዊ መሰረትን መነሻ ያድርጋሉ:: የአንጎል ተፈጥሯዊ አሠራር፣ ቤተሰባዊ ቅርርብ፣ ማኅበራዊ መስተጋብር፣ የስነ ልቦና ውቅር፣ ከባቢያዊ ሁኔታዎች፣ የታለፈባቸው የሕይወት መስመሮች ለተለያዩ የአዕምሮ ህመም አስተዋጽኦ ሊኖራቸው እንደሚችል ዶ/ር ግዛቸው አስታውቀዋል::
እንደ ዘርፉ ባለሙያ ማብራሪያ ከከባድ የአዕምሮ ህመም ቅርበት ባለው ዝምድና አማካኝነት በዘር ተወራራሽነት የመከሰት ዕድሉ ሰፊ ነው:: ስፔሻሊቱ ይህንን ሲያብራሩ በአንድ የቅርብ ቤተሰብ (እናት፣ አባት፣ እህት፣ ወንድም) ላይ የተከሰተ ከባድ የአዕምሮ ህመም የቅርብ ቤተሰብን በስምንት እጥፍ ተጋላጭ ሊያደርገው ይችላል:: የተጋላጭነት አድማሱ በመንትዮች ላይ ደግሞ ከ50 በመቶ በላይ ይደርሳል::
ዕድሜ ሌላው የከባድ አዕምሮ አጋላጭ ምክንያት መሆኑን ዶ/ር ግዛቸው ጠቁመዋል:: ወላጆች በተለይ የአባት ዕድሜ ከ40 በላይ ከሆነ የሚወለዱ ልጆች የአዕምሮ ህመም ተጋላጭነታቸው ከፍ ይላል:: ከባድ የአዕምሮ ጤና የስርጭት ምጣኔው ከፍ ብሎ የሚስተዋለው በወንዶች ከ10 እስከ 15 እና በሴቶች ከ25 እስከ 35 ባሉት የዕድሜ ክልሎች ነው::
አንጎል እና የአንጎል የነርቭ ሥርዓት ሥራውን በአግባቡ እንዲሠራ የሚያደርገው የዶፓሚን ንጥረ ነገር ማነስ እና መብዛት ለከባድ የአዕምሮ ህመም መከሰት እንደ ምክንያት ይጠቀሳል:: ንጥረ ነገሩ በተለዩ የአዕምሮ ክፍሎች በሚበዛበት ወቅት ሰዎች ለፀብ እንዲነሳሱ፣ ከልክ በላይ ጉልበታምነት (ኀይለኛነት) እንዲሰማቸው እና ብቻቸውን እንዲያወሩ ያደርጋቸዋል:: በሌላ በኩል የዶፓሚን ንጥረ ቅመም ሲያንስ ከሰው የመነጠል፣ በዝምታ የመዋጥ እና ራሳቸውን ያለመጠበቅ አይነት ባህሪያትን እንዲያሳዩ ያደርጋቸዋል::
በአንጎል ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጉዳት የሚያመጡ አደጋዎችና አካላዊ ሕመሞች አንጎል የዘወትር ተግባሩን በትክክል እንዳያከናውን በማድረግ ለአዕምሮ መታወክ ሊዳርግ እንደሚችል የአማኑኤል የአዕምሮ ሕክምና ማዕከል በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ያሰፈረው ጽሑፍ ያስረዳል:: በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ኢንፌክሽን መፈጠር፣ የተለያዩ የሰውነት ንጥረ ነገሮች ማነስ ወይም መብዛት፣ በራስ ቅል (ጭንቅላት) ላይ የሚደርስ አደጋ፣ የደም ብዛት እና የአንጎል መሳሳት ዋና ዋና ምክንያት አድርጎ አንስቷል::
ሥነ ልቦናዊ ማኅራዊ ምክንያቶችም ለከባድ የአዕምሮ ህመም የተለየ አበርክቶ እንዳላቸው የስነ ልቦና ባለሙያዎች ይስማማሉ:: ጭቆና የበዛበት አስተዳደግ ደግሞ ለአዕምሮ ህመም አጋላጭ መሆኑን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስነ ልቦና መምህር ሙሉዓዳም ታምሩ ያስረዳሉ:: አንድ ሕጻን በአስተዳደግ ሂደቱ ውስጥ በየጊዜው የሚያያቸው፣ የሚሰማቸው እና የሚደርሱበት አካላዊ ቅጣቶች በስነ ልቦና ስሪቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖን በመፍጠር ለከባድ የአዕምሮ መቃወስ ተጋላጭ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል::
አካባቢያዊ ሁኔታዎች በተለይ በተደጋጋሚ ጦርነት የሚካሄድባቸው፣ ለኑሮ ምቹነት የሌላቸው ማኅበራዊ መስተጋብር ለችግሩ የመጋለጥ አጋጣሚን እንደሚያሰፋውም የስነ ልቦና ባለሙያው ገልጸዋል:: በእርግዝና ወቅት እናት ጽንሱን ታሳቢ ያደረጉ የተመጣጠኑ የምግብ አይነቶችን በበቂ ሁኔታ መውሰድ የማትችል ከሆነ ሕጻኑ ከተወለደ በኋላ ለከባድ የአዕምሮ ችግር የመጋለጥ አጋጣሚው የሰፋ ሊሆን እንደሚችልም አስገንዝበዋል::
ቤተሰብ ለልጁ ስሜት፣ ሐሳብ እና ፍላጎት የሚሰጠው ምላሽ ጭቆና የበዛበት እና የታፈነ ከሆነ በቀጣይ የአዕምሮ ጤናማነቱ ላይ ተጽኖ እንደሚያሳድር አስረድተዋል:: የተገደበ የስነ ልቦና የዕድገት ደረጃ፣ ለራስ የሚሰጥ የተጋነነ የበታችነት ወይም የበላይነት ስሜት ለከባድ የአዕምሮ ህመም አጋላጭ ነው::
የአማኑኤል የአዕምሮ ሕክምና ማዕከል ለአዕምሮ ህመም ማህበራዊ ምክንያቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ያስገነዝባል:: አደንዛዥ ዕጾችን የመጠቀም እና የሕይወት ውጣ ውረዶችን ለችግሩ ዐቢይ ምክንያት አድርጎ ያነሳል:: በሰዎች አብሮ የመኖር ሁኔታ ውስጥ፣ በእርስ በርስ ግንኙነቶች እና በተለያዩ ማኅበራዊ መስተጋብሮች ወቅት አለመግባባቶች እና ግጭቶች በየጊዜው ይፈጠራሉ:: ሰዎች ልዩነትን ተቀብለው ተቻችለው እና ግንኙነቱን አስተካክለው ለመኖር ሳይችሉ ሲቀር እና የአዕምሮ መረበሽ ሲከሰት ለአዕምሮ ህመም ሊዳረጉ እንደሚችሉ መረጃው ጠቁሟል::

ነጋሪዎቹ
የአዕምሮ ሕመም ምልክቶች እንደ ህመሙ ዓይነት፣ ደረጃ እና የጊዜ ቆይታ የተለያዩ ናቸው:: ዶ/ር ግዛቸው እንዳስታወቁት የአዕምሮ ህመም በመጀመሪያ ሲጀማምር እና ሥር ሲሰድ የተለያዩ ምልክቶችን በነጋሪነት ያሳያል::
እንደ ስፔሻሊስቱ ከባድ የአዕምሮ ህመም የሚጀምረው “እኔ ማነኝ?” ብሎ በሚጠየቅበት የዕድሜ ደረጃ ላይ ነው:: ይህም ለመጠነኛ የስነ ልቦና ምስቅልቅል ሊዳርግ እንደሚችል ጠቁመዋል:: በዚህ ጊዜ ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ እና ከሌላውም የማኅበረሰብ ክፍል የመገለል፣ ራስን የመጣል ስሜቶች መንፀባረቅ ይጀምራሉ:: የሃይማኖታዊ፣ የፍልስፍና፣ ከነባራዊ ሀቅ ያፈነገጡ ጥያቄዎችን የማንሳት አዝማሚያም ይስተዋላል::
የህመሙ ዋና መገለጫዎች ከወራት በኋላ ሲጀምሩ የተዛባ ግንዛቤ ጎልቶ መውጣት ይጀምራል:: በዚህ ጊዜ የችግሩ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ምንም አይነት ድምጽ ሳይኖር ድምጽ ይሰማቸዋል:: ይህ ድምጽ አስተያየት ወይም ትዕዛዝ የሚሰጣቸው ሊሆን እንደሚችል ስፔሻሊስቱ ጠቁመዋል::
ወጣ ያለ እና በሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ባሕል እና እምነት የማይደገፍ የተዛባ አስተሳሰብ ወይም አተያይ መንጸባረቅ ሌላው የችግሩ ምልክት ነው:: በዚህ ጊዜ “እናቴ ልትመርዘኝ ነው፣ ልትገድለኝም እየተከታተለችኝ ነው፣ መንግሥት እየፈለገኝ ነው፤ ሰዎች መተት አድርገውብኛል…” የሚሉ እና ሌሎች መሰል ከፍተኛ ጥርጣሬዎች ህመሙ ከፍተኛ ደረጃ መድረስን የሚጠቁሙ ናቸው::
ከራስ ማንነት ውጭ ለራስ የተጋነነ ግምት መስጠት፣ መሰረትነት የሌለው ቅናት፣ ድርቅ ያለ አቋም መያዝ፣ የበዛ ባህሪ ማሳየት (መውጣት፣ መግባት፣ መተኛት፣ ሲያወሩ መዋል፣ ዝምታ፣ መተናኮል…)፣ በኃላፊነት ልክ ዕለታዊ ተግባርን መፈጸም አለመቻል ከባድ የአዕምሮ ህመም ለመከሰቱ ሁነኛ ማመሳከሪያዎች መሆናቸው ተመላክቷል::

ተጽእኖዎቹ
የአማኑኤል የአዕምሮ ሕክምና መረጃ እንደሚያመላክተው ከባድ የአዕምሮ ህመም (ስኪዞፍሬኒያ) ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድ በመቶ የሚሆነውን ያጠቃል:: ከባድ የአዕምሮ ህመም ሰዎችን ለከፋ የጤና እክል፣ ለኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መስተጋብር መቃወሶች እንደሚዳርግ የአዕምሮ ሕክምና ስፔሻሊስቱ አስገንዝበዋል::
ሰዎችን ለልብ ህመም እና ለኢንፌክሽን በማጋለጥ፣ ራሳቸውንም እንዳይጠብቁ በማድረግ ከዕድሜ ጣሪያቸው ቀድመው ለሕልፈት እንዲዳረጉ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል::
የማይፈልጉትን ድምጽ ሁልጊዜ መስማት የሚያስከትለው ጭንቀት በራሱ ሌላ ጉዳት መሆኑንም አንስተዋል:: ችግሩ በራስ ላይ ጉዳት እስከማድረስ እና ከችግሩ ለመሸሽ ሱስ ውስጥ እስከመግባት ሊያደርስ እንደሚችልም ገልጸዋል::
በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደ ሰው ያለመቆጠር አስተሳሰብ ስለሚሰርጽ የመገለል፣ የመድልኦ፣ የመብት መጣስን ያስከትላል:: ከሥራ ውጭ መሆን፣ ቤት አልባ መሆን፣ ትዳርን መበተን፣ ከህመሙ ለመዳን የሚወጣው ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ መቃወስ እንደሚዳርግ ጠቁመዋል::

የሕክምና አማራጮች
ከባድ የአዕምሮ ህመም ስነ ልቦናዊ መንስኤው ጎልቶ እንደሚታይ ስፔሻሊስቱ አንስተዋል:: በዚህም የመድሃኒት ሕክምናው ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል:: የመድሃኒት ሕክምናው የህመሙን ደረጃ መሰረት አድርጎ በመርፌ እና በእንክብል መልክ የሚሰጥ ስለመሆኑም ገልጸዋል:: የአዕምሮ ህመም የተኝቶ የመድኃኒት ሕክምና እንደሚታዘዝም ዶ/ር ግዛቸው አስታውቀዋል::
የተኝቶ ሕክምና ዋና ግብ በራስ እና በሌላ አካል ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ማድረግ፣ የተረጋጋ ማኅበራዊ መስተጋብርን መፍጠር ነው:: መድሃኒቶቹ ታካሚዎች ወደ ቀደመ ሕይወታቸው እንዲመለሱ የሚያደርግ ሲሆን እስከ ሁለት ወራት የሚወሰድ መሆኑን ጠቁመዋል:: ከዚያም የመረባበሽ ስሜቱ ጠፍቶ ወደ ጤናማነት ከተመለሱበት ጊዜ ጀምሮ ማገርሸትን መከላከል ላይ ያተኮረ የመድኃኒት ሕክምና እንደሚታዘዝ ዶ/ር ግዛቸው አስታውቀዋል:: ይህም የሕክምና አማራጭ በቤተሰብ ታሪክ ላይ የሌለ እና በራሱ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተ ሆኖ ከተረጋገጠ ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት እንደሚቀጥል አስታውቀዋል:: ይሁን እንጂ ታካሚዎች መሻሻል ሲያሳዩ መድሃኒቱን እንደሚያቋርጡ፣ ይህም ህመሙ እንዲያገረሽ እንደሚያደርግ ተናግረዋል::
የአዕምሮ ህመም ስነ ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ሕክምናዎች እንዳሉት ዶ/ር ግዛቸው ገልጸዋል:: የስነ ልቦና ሕክምና በዋናነት የተዛቡ አተያዮችን እና አስተሳሰቦችን በማስወገድ ታካሚው ወደ ቀደመ ሕይወቱ እንዲመለስ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል:: ለረጅም ጊዜ የቆየ ከሆነ ደግሞ የማኅበራዊ ድጋፍ (ሁሉን ዓቀፍ የመልሶ ማገገም) ሕክምና በአማራጭነት እንደሚሰጥ ገልጸዋል::
ዶ/ር ግዛቸው እንደገለጹት የአዕምሮ ህመም በሕክምና መዳን የሚችል በሽታ ነው:: በመሆኑም ሁሉም ሰው የአዕምሮ ህመም ነጋሪ ምልክቶችን ሲመለከት ፈጥኖ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ፣ በተገቢው ባለሙያ መታየት፣ ሕክምናውን ጀምሮ እንዲያጠናቅቁ ማገዝ ከሁሉም እንደሚጠበቅ አሳስበዋል::

(ስማቸው አጥናፍ)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here