አንዳንድ ጊዜያት አሉ፤ ለመለየት ወይም ተቃራኒ አቅጣጫ ለመያዝ ቀላል የሚሆንባቸው:: ነገር ግን በተወሰነ ደረጃ እኔ አንድ ተጨማሪ እርምጃ ባደርግ፣ የሆኑ ሰዎች እኔን እንደሚቀላቀሉኝ ተሰማኝ።
ያንን ውሳኔ በወሰድኩ ጊዜ (ወንበሬን ላለመልቀቅ ስቃወም) የአባቶቼ ጥንካሬ ከጀርባየ መኖሩን አውቅ ነበረ።
– ሮዛ ፓርክስ
በአንድ የወንዶች አልባሳት መደብር ውስጥ ልብስ ሰፊ ናት። ረጅም ስዓት ስትሰራ በመዋሏ የወገብ ህመም ተሰምቷታል፣ ራሷን አሟታል። ስራዋን ስትጨርስ በዚህ የድካም እና የህመም ስሜት ሆና ወደ ቤቷ ለመመለስ የከተማውን አውቶቡስ ትጠባበቃለች። የከተማው አውቶብስ ብዙም ሳይቆይ ከተፍ አለ። ሮዛ ፓርክስ ወደ አውቶቡሱ በምትገባበት ጊዜ ከሾፌሩ ጋር ዓይን ለዓይን ተገጣጠሙ፤አዲስ ፊት አልሆነባትም፤ ጀምስ ኤፍ ብሌክ ነበር። ከአስራ ሁለት ዓመታት በፊት ‘ወንበሬን ለነጭ አልለቅም’ በማለቷ እየገፈታተረ እንዳስወጣት ትዝ ብሏታል። ግን ቆራጧ ሴት ምንም ሳይመስላት ከፊት ለፊት ተቀመጠች።
ሮዛ ያለችበት አውቶቡስ ጉዞውን ቀጠለ። በየመንገዱ ነጭ ተሳፋሪዎችን መሙላት ጀመረ፤ ወዲያውም ሞላ። ጉዞው ቀጠለ። ነገር ግን በርካታ ነጮች በመተላለፊያው ላይ መቆማቸውን በማየት ሾፌሩ አውቶቡሱን አቆመው። ጥቁሮች እና ነጮች የሚቀመጡበትን ቦታ የሚለየውን ምልክት እያሳየ ወንበር ይዘው የተቀመጡ አራት ጥቁሮችን ወንበራቸውን እንዲለቁ ጠየቀ። ይህ በሞንትጎሞሪ ከተማ ህግ መሰረት ሁሉም የከተማ መጓጓዣዎች ጥቁሮችን አግላይ እንዲሆኑ እና ለሾፌሮቹም ህጉን ለማስፈፀም እንዲቻልም የፖሊስ ባለሙያ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል።
ይህ ማለት ሾፌሮቹ ነጭ እና ጥቁር ተሳፋሪዎቹን ወንበሮቻቸውን በመከፋፈል የሚለያይ ነገር ግን እኩል መስተንግዶ መስጠት አለበት። በአውቶቡሱ መካከል ላይ አንድ መስመር ነጮች የሚቀመጡባቸውን የፊት ወንበሮችን እና ጥቁሮቹ የሚቀመጡባቸውን የኋላ ወንበሮችን የሚከፍል አንድ መስመር አለ። አንድ አፍሪካዊ አሜሪካዊ ትኬት ለመቁረጥ ብቻ ወደ ፊት መምጣት አለበት:: ከዚያም ከአውቶቡሱ ይወርድና እንደገና በኋላ በር ይሳፈራል። ነገር ግን ይህን ደንብ የሚጥሰውን ማንኛውንም ጥቁር አሜሪካዊ ከወንበሩ የማስነሳት፤ አለበለዚያም አገልግሎት የመከልከል እንዲሁም በፖሊስ የማስያዝ ስልጣን የሾፌሩ ነው።
ሶስቱ ጥቁሮች የሾፌሩን ትዕዛዝ በማክበር ተነሱ:: ነገር ግን ሮዛ ፓርክስ ተቃወመች እና አልተነሳችም። ሾፌር ብሌክም፣ “ለምን አትነሺም?” ሲል ጠየቀ:: ላቀረበላት ጥያቄ፣ “የመነሳት ግዴታ እንዳለብኝ አላስብም” ብላ ነበር ፓርክስ የመለሰችለት። እርሱም ፖሊስ ጠራ እና አሳሰራት።
ጥቁርነት እንደቆሻሻ ተቆጥሮ ከሰው ተራ እኩል የማያስቆጥርበት አግላይ እና አድሏዊው አስተሳሰብ የህግ ሽፋን አግኝቶ በዘሯ ላይ እየተፈፀመ ያለውን በደል ከመታገል ሌላ አማራጭ አለመኖሩ ቀድሞ የገባት፣ ገብቷትም ራሷን አሳልፋ በመስጠት የተጋፈጠችው ሮዛ ፓርክስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ብትውልም ከዚያው ምሽት የጀመረ ታላቅ የትግል እሳት ለኩሳለች፤ ቁርጠኝነቷ ሌሎቹን አደፋፍሯል።
ስለክስተቱ ፓርክስ እንደተናገረችው፣ “ነጩ ሾፌር እኛ ወደነበርንበት ሲመጣ፣ እጁን ሲያወዛወዝ እና እንድንነሳና ወንበራችንን እንድንለቅ ሲያዝዘን፣ ልክ በክረምት ምሽት እንደሚለበስ ወፍራም ብርድ ልብስ፣ አንዳች ወኔ ሰውነቴን ሲሸፍነው ተሰማኝ።”
ሮዛ ፓርከስ በግለ ታሪኳ ላይ፣ “ሰዎች ሁልጊዜ ወንበሬን አልለቅም ያልኩት ስለደከመኝ እንደሆነ ይናገራሉ፤ ነገር ግን ይህ እውነት አይደለም። በአካል አልደከመኝም፤ በፍፁም። እኔን የታከተኝ ብቸኛው ነገር መሸነፍ ነበር” ብላ ፅፋለች።
እ.ኤ.አ ዲሴምበር 5/ 1955 ላይ ከአራት ቀናት በኋላ ሮዛ ፓርክስ ፍርድ ቤት ቀረበች። በዚያው እለት በሺዎቹ የሚቆጠሩ ጥቁር አሜሪካውያን ሮዛ የተከሰሰችበትን ዘረኛ ሕግ በመቃወም በአላባማ የከተማ አውቶቡሶች ያለመጠቀም አድማ መቱ። አድማው ግን በሮዛ ላይ ፍርድ ከመተላለፍ አልከለከለም:: ሮዛ ፓርክስ አስር ዶላር እንድትቀጣ ተፈረደ። በተጨማሪም አውቶቡስ ስትጠቀም ከሌላው በተለየ ተጨማሪ አራት ዶላር እንድትከፍል ተወሰነ። ሮዛ ውሳኔውን ተቃወመች።
በዚሁ ዕለት ምሽት እውቁ የጥቁሮች እኩልነት ታጋይ ማርቲን ሉተር በሆልት ጎዳና ባብቲስት ቤተ ክርስቲያንን አካባቢ ለተሰባሰቡ ሰዎች ንግግር እያደረገ ነበር። ሕዝቡ አውቶቡሶችን ያለመጠቀም አድማውን እንዲቀጥልበት አበረታታ። በሞንትጎሞሪ የሚኖሩ ከ40 በላይ ጥቁር አሜሪካውያን ለ381 ቀናት ያህል አውቶብስ ያለመጠቀም አድማውን በመምታት የበለጠ ጉልበት በመስጠት አገዙ።
ሮዛ ፍርድ ቤት የቀረበችበት ዕለት የታየው ትልቁ ክስተት የሮዛ ፍርድ ቤት መቅረብ የቀሰቀሰው ክስተት ነበር። አብዛኛው የከተማው አውቶቡሶች ባዶ ነበሩ። አንዳንድ ሰዎች ሰብሰብ ብለው ለብቻቸው በአንድ መኪና የመሄድ እና ሌሎቹ ጥቁር በሚነዳው መኪና የመሄድ እርምጃ ወስደዋል። ነገር ግን አብዛኛው ወደ 40 ሺህ የሚገመት በዚያው ከተማ የሚኖር አፍሪካዊ አሜሪካዊ ከቤት እስከ ስራ ቦታ በእግር መጓዝን መርጦ ነበር፣ እስከ 20 ማይል የተጓዙ እንደነበሩም የታሪክ መዛግብት ያሳያል።
አድማው ለመቶ ቀናት እየተጠናከረ መቀጠሉ በአላባማ ባለስልጣናት ላይ ጫና መፍጠሩ አልቀረም። የሞንትጎሞሪ ከተማ ውጤታማ ሆነ፤ በርካታ የከተማው አውቶቡሶች ስራ ፈትተው ተቀመጡ፤ በውጤቱም ኩባንያውን በገንዘብ ክፉኛ አሽመድምዶታል። ከአድማው መጠናከር ጋር ግን ጠንካራ ተግዳሮት ተፈጥሯል።
አንዳንድ ዘረኞች በሀይል አፀፋዊ ምላሽ ሰጡ። የጥቁሮች ቤተ ክርስቲያኖች ተቃጠሉ። የማርቲን ሉተር እና አድማውን ያስተባበረው የኒክሰን ቤቶች በቦምብ እንዲወድሙ ተደርጓል። አሁንም አድማው እንዲያበቃ ተጨማሪ ሙከራዎች ተደርገዋል። አፍሪካዊ አሜሪካዊያን የሚጠቀሙበት የታክሲ ስርአት የሕይወት መድህን ተሰረዘ። እንዲሁም ጥቁር ዜጎች አድማ የሚከለክለውን ሕግ ተላልፋችኋል በሚል ይታሰሩ ነበር።
በምላሹም የጥቁሮች ማህበረሰብ አባላት ሕጋዊ እርምጃዎችን ወሰዱ። አግላይ ፖሊሲዎች በህዝብ ትምህርት ማእከላት ላይ ምንም ቦታ የላቸውም የሚለውን የትምህርት ቦርዱን ውሳኔ በማበረታታት፣ ጥቁር የሕግ ባለሙያዎች ቡድን በሕዝብ መጓጓዣ ላይ ያለውን የአግላይ ወይም የዘረኝነት ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ወሰዱት። ክሱን ያረቀቀው የሮዛ ፓርክስ ጠበቃ ነበር።
በሰኔ ወር 1946 ዓ.ም ላይ የአውራጃ ፍርድ ቤቱ የዘር ተኮር አግላይ ህጎች (የጅም ክሮው ሎውስ በመባል የሚታወቁት ህጎች) ኢ-ህገ መንግስታዊ መሆናቸውን አወጀ። የሞንትጎሞሪ ከተማ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ብዙም ሳይቆይ ተቀበለች፤ ነገር ግን በህዳር ወር 1947 ዓ.ም ላይ የአሜሪካ ከፍተኛው ፍርድ ቤት በሕዝብ መጓጓዣ ላይ የዘር አድልኦ ተግባራት ሕገ ማንግስታዊ አለመሆናቸውን አወጀ።
የትራንዚት ካምፓኒው እና የከተማ ቢዝነሶች ከገጠማቸው ኪሳራ እና የሕግ አካላት ከእነርሱ ተቃራኒ ውሳኔዎችን ከማስተላለፍ ጋር በተያያዘ የሞንትጎሞሪ ከተማ በአውቶብሶች ላይ የዘር ከፋፋይ ህጎችን ከማንሳት ሌላ አማራጭ አልነበረውም። በመሆኑም ታህሳስ 10 ቀን 1947 ዓ.ም ከ381 ቀን በኋላ አድማው በይፋ አበቃ። ህጋዊ እርምጃ፣ በጥቁር ማህበረሰብ የፀና ቁርጠኝነት በመታገዝ በጥምረት የሞንትጎሞሪ አውቶቡስ አድማሱን በታሪክ ውስጥ የዘር መድልኦ በመቃዎም የተደረገ ትልቁ እና በጣም ውጤታማው ንቅናቄ እንዲባል አድርጎታል።
ለዚህ ሁሉ ለውጥ ምክንያት የሆነችው ሮዛ ፓርክስ ጥር መጨረሻ 1905 ዓ.ም አላባማ ውስጥ ቱስክጊ የተወለደች ሲሆን ሮዛ ሉዊዝ ማኩሊ ትባል ነበር። ወላጆቿ፣ ጀምስ እና ሊዮና ማኩሊ፣ የተለያዩት ገና በሁለት ዓመት የህፃንነት እድሜዋ ላይ ነበር።
የሮዛ እናት ቤተሰቧን ይዛ ወደ ወላጆቿ ሄደች። አላባማ ውስጥ ፓይን ሌቭል። የሮዛ ሁለቱም አያቶቿ በባርነት የቆዩ ሰዎች እንደመሆናቸው ለዘር እኩልነት ጠንካራ ደጋፊዎች ነበሩ። ሮዛ የዘር አድልኦን እና የዘር እኩልነት አንቂነትን አስቀድማ በልጅነት እድሜዋ የተለማመደች ጀግና ሴት ነበረች።
ወጣት ሮዛ ከነጭ ህፃናት ጓደኞቿ የማንቋሸሽ ስድብ ሲገጥማት ትገረም ነበር:: “እስከማስታውሰው ድረስ የአካላዊ ትንኮሳን ያለምንም አፀፋ በፍፁም መቀበል አልችልም” በማለት ተናግራ እንደነበር ታሪኳ ያሳያል።
በልጅ እድሜ ጥቃትን በጀ ብሎ መቀበል ያልፈጠረባት ሮዛ ፓርክስ በ42 ዓመት የጉልምስና እድሜዋም ላይ ያው ባህሪዋ ተከትሏት ዘረኛ ከፋፋይ ህጎችን ያስቀየረ ታሪክ መስራት ችላለች። “የሲቪል ወረት ንቅናቄ እናት” እየተባለች እስከ ዛሬ ትታወሳለች።
ሮዛ ፓርክስ ለጥቁሮች መብት ከሚታገሉት ከእነ ማርቲን ሉተር ከእነ ማልኮልም ኤክስ እና ሌሎች ጥቁር ታጋዮች ተርታ ስሟ እነሆ በአሜሪካውያን ታሪክ ውስጥ ሕያው ሆኖ ሰፍሯል።
ምንጭ፦ሂስትሪ ዶት ኮም
-ሮዛ ፓርከስ አውቶ ባዮግራፊ
-ባዮግራፊ ዶት ኮም
-ፎክስ ኒውስ እና ቢቢሲ ዶት ኮም
(መሰረት ቸኮል)