የዚህ እትም እንግዳችን ተወልዶ ያደገው በአማራ ክልል፣ አዊ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ቻግኒ ከተማ ውስጥ ልዩ ስሟ መድሃኒዓለም በተባለችው ሰፈር ነው::
ከአንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያለውን ትምህርቱንም በቻግኒ ከተማ ተከታትሏል:: መርጡለማርያም በሚገኘው የግብርና ኮሌጅ በዲኘሎማ ከተመረቀ በኋላ በዚገም እና ዳንጉር ቀበሌዎች ለአራት ዓመታት በግብርና ባለሙያነት ሠርቷል::
ከግብርና ባለሙያነቱ በተጓዳኝ ክራር ለተባለው ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ ልዩ ፍቅር የነበረው እንግዳችን የሙዚቃውን ዓለም በተቀላቀለ አጭር ጊዜ ውስጥ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ ከያኒ ሆኗል:: በተለይም በነጠላ ዜማነት ለሕዝብ ጆሮ ያደረሳቸው ”እናትዋ ጐንደር” እና ”ካሲናው ጐጃም” የተሰኙት ሙዚቃዎቹ በሕዝብ ዘንድ በእጅጉ ተቀባይነት አስገኝተዉለታል::
በጥር ወር 2016 ዓ.ም ቀደም ብሎ በነጠላ ዜማነት የለቀቃቸውን እናትዋ ጐንደር እና ካሲናው ጐጃምን ጨምሮ ”እንገር ወሎ፣ ስለ ሽዋ፣ ዐድዋ፣ ዓባይ” እና ሌሎች ርዕሰ ጉዳዮችን የያዙ 10 ሙዚቃዎችን ለአድማጮቹ አድርሷል:: በባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች የተቀናበሩ 10 ዘፈኖችን ለአድማጮቹ አድርሶ ይበልጥ ተወዳጅነቱን ካተረፈው ከያኒ አስቻለው ፈጠነ ጋር በሙዚቃ ሥራዎቹ ዙሪያ ቆይታ አድርገናል፤ መልካም ንባብ!
ወደ ሙዚቃ ሥራ እንዴት ገባህ?
ወደ ሙዚቃ ሥራ ገባሁ ብዬ የማምነው የአባቴን አርዓያነት በመከተል ነው:: አባቴ እኔ ሕፃን ካለሁበት ጊዜ አንስቶ ክራር አብዝቶ ይጫወታል:: እኔም ከአባቴ አጠገብ ተቀምጨ አባቴ የሚጫወተውን ክራር በማድመጥ ነው የሙዚቃን ህይወት መለማመድ የጀመርኩት:: አባቴ ሲጫወትበት የቆየውን ክራር እኔ እንድጫወትበት በመስጠትም የእሱን አርዓያነት እንድከተል አድርጐኛል::
አባቴ ብቻ ሳይሆን ወንድሞቼ እና አንዱ አጐቴም ጭምር ክራር ይጫወቱ ስለነበር ክራር በኛ ቤተሰብ ውስጥ ተወዳጅ የሙዚቃ መሣሪያ ነው:: አጐቴ እና ወንድሞቼ ከሙዚቃ በተጨማሪ መዝሙር ላይም ያተኩሩ ስለነበር እኔም እነሱን ተከትዬ መዝሙርም እዘምር ነበር፤ በተለይ ግን አባቴ የክራር ፍቅር እንዲያድርብኝ እና ገና በልጅነቴ ክራር መጫወት እንድችል ትልቁን ድረሻ ተወጥቷል:: አባቴ በህይወት ቢኖር እና የእሱን የክራር ቅኝቶች ተከትዬ አሁን የደረስኩበት ደረጃ ላይ መድረሴን ቢያይ ደስተኛ ነበርኩኝ::
በሙዚቃ ሥራ ውስጥ እንድትቀጥል የቤተሰቦችህ ድጋፍ ነበረህ?
ቤተሰቦቼ ሙዚቀኛ እንድሆን ድጋፍ ያደርጉልኝ ነበር ማለት አልችልም:: ምክንያቱም እኔ ያኔ በትምህርቴ በጣም ጐበዝ ስለነበርኩኝ በትምህርቴ እንድገፋበት እንጂ ሙዚቀኛ እንድሆን የሚፈልግ የቤተሰቤ አባል የለም:: ይልቁንም ትላልቅ ወንድሞቼ፣ አባቴ እና አጐቴ ክራር በጣም ይጫወቱ ስለነበረ የእነሱን አርዓያነት እንድከተል በተዘዋዋሪ መንገድ ተፅዕኖ አሳድረውብኛል ማለት እችላለሁ::
ከኛው ሰፈር የጋሽ ሽባባው ልጅ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ታዋቂ ሙዚቀኛ መሆኗ የመንደራችንን ሰው ቢያስደንቀውም አስቻለውም ታዋቂ ሙዚቀኛ ይሆናል ብሎ አንድም ሰው እንዳልገመተ ግን እርግጠኛ ነኝ:: በዚያን ወቀት ለጓደኞቼ ክራር ስጫወትላቸው እና “ፋኖ ፋኖ…” እያልኩኝ ሳዜምላቸው “አስቼ ትችላለህ” ከሚለው አድናቆታቸው አልፎ እኔን ታዋቂ ሙዚቀኛ ትሆናለህ ያለኝ አንድም ጓደኛ አልነበረኝም::
ምንም እንኳን ሙዚቀኛ እንድሆን የቤተሰቦቼ ግፊትም ሆነ ድጋፍ ባይኖረኝም የአባቴ፣ የወንድሞቼ፣ የአጐቴ እና የሠፈር ጓደኞቼ አድናቆት በተዘዋዋሪ ወደ ሙዚቃው ዓለም ገፍቶኛል ብዬ አምናለሁ:: በተለይ የአባቴ ተፅዕኖ ቀላል እንዳልነበረ የተረዳሁት አሁን ሙዚቃው ውስጥ ሰምጨ ከቀረሁ በኋላ ነው::
አዲሱ አልበምህ በሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ምን ይመስላል?
አዲሱ አልበሜ በሕዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት እኔ ከጠበኩት በላይ ነው:: በአማራ ክልል ባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ኢንተርኔት የተቋረጠ ቢሆንም አብዛኛው ሰው በተለያዩ አማራጮች ሙዚቃዎቼን ሰምቶልኛል:: የአማራ ክልልን ጨምሮ ከተለያዩ አካባቢዎች ስልክ እየተደወለልኝ በሙዚቃ ሥራዎቼ ደስተኛ እንደሆኑ የሚገልፁልኝ ሰዎችም ብዙ ናቸው::
ሙዚቃዎች በዩቲዩብ በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እና ኤፍ ኤም ራዲዮዎች በስፋት እየተደመጡ ነው:: በተለይም አዲስ አበባ ውስጥ የኔ ሙዚቃዎች በተለያዩ የኤፍ ኤም ጣቢያዎች እና በየምሽት ቤቶቹ እየተደመጡ በመሆኑ አልበሜ በሕዝብ ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት አግኝቷል ብል የተሳሳትኩኝ አይመስለኝም::
ከያኒዎች በሙዚቃ ሥራዎቻችሁ ተጠቃሚ ናችሁ ወይስ አይደላችሁም?
ከድሮው ይሻላል ነው እንጂ ተጠቃሚዎች ነን ማለት አልችልም:: እኛ ሀገር ዘፋኝ ስትሆን ደስ የሚለው ነገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ትንሽ ሠርተህለት ብዙ የሚሸልምህ መሆኑ ነው:: አስቻለው ሀብታም መሆን ቢፈልግ ኖሮ ቻግኒ ውስጥ ሆኖ በመንገድ ወይም በግብርና ሥራው በመቀጠል ሀብታም መሆን ይችል ነበር:: ያ ግን የተፈጥሮ ጥሪዬ ባለመሆኑ ከነጋዴነት ይልቅ ሙዚቀኛነትን ተቀላቅያለሁ::
እኔ ጥበብን በሳንቲም አልለካትም፤ በህይወቴ ደስተኛ የምሆነው ብዙ ብር ሳገኝ ሳይሆን አንድ ግጥም ስፅፍ ወይም አንድ ዜማ ስደርስ ነው:: አሁን ላይ የተሳፈርኩበት ባቡር የት እንደሚያደርሰኝ ባላውቅም እስካሁን ከሕዝቡ እያገኘሁት ያለው ምላሽ ግን እኔን በጣም ደስተኛ አድርጐኛል:: ደስታ አንፃራዊ ነው:: ብዙ ገንዘብ በማግኘት የሚደሰቱ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ ብዙ አድማጭ እና አድናቂ በማግኘት የምንደሰት ሰዎችም አለን:: አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ገንዘባችንም ሆነ ደስታችን ከሕዝብ የምናገኘው ፍቅር ነው:: ይሄንን ለማረጋገጥ ደግሞ የብዙ ሙዚቀኞችን ህይወት ማየቱ በቂ ነው::
እስካሁን ድረስ በሙዚቃዎቼ መድረክ ላይ ወጥቼም ሆነ ገንዘብ አግኝቼባቸው አላውቅም:: የሙዚቃ ሥራዎቼን ወጪዎች የሸፈነልኝ ‘ኘሮዲዩሰሬ’ ሰው መሆን ይስማው ነው:: እኔ እና ሰው መሆን የኢትዮጵያ ባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች በዓለም ላይ እንዲታወቁ የማድረግ ትልቅ ራዕይ አለን:: ይህንኑ ራዕያችንን ለማሳካትም ጠንክረን እየሠራን እንገኛለን::
በሙዚቃ ሥራዎቼ ገንዘብ ማግኘት ስፈልግ ከውጭ ሀገር በብዛት እየቀረቡልኝ ላሉት ጥሪዎች መልስ በመስጠት ገንዘብ ማግኘት እችላለሁ:: በሀገር ውስጥም የተለያዩ መድረኮች ላይ እየሠራሁ ገንዘብ ማግኘት ይቸግረኛል ብዬ አላስብም:: ባጠቃላይ ነገሩን እንደ ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ እንየው ካልን ግን በሙዚቃ ሥራዎቻችን ተጠቃሚ ነን ማለት ይቸግረኛል::
የሀገራችን ሙዚቃ እያደገ ወይስ እየቀጨጨ ነው?
ይሄንን ጥያቄ ለመመለስ ጥልቅ ጥናት ማካሄድ የሚያስፈልገው ይመስለኛል:: በኔ አመለካከት ግን የኢትዮጵያ ሙዚቃ የምንለው የትኛውን ሙዚቃ ነው? የሚል ትልቅ ጥያቄ አለኝ:: እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የኢትዮጵያ ሙዚቃ የሚባሉት በኢትዮጵያ የባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች የተሠሩት ናቸው:: በዚህ መንገድ ካየነው ደግሞ በኢትዮጵያ ባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ብቻ ወይም በኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶች ብቻ የተሠሩ ሙሉ አልበሞች አሉ ማለት ያስቸግራል::
በውጭ የሙዚቃ መሣሪያዎች እየተሠሩ ያሉ በርካታ የኢትዮጽያ ዘፈኖች አሉ:: በአንድ የሙዚቃ ማቀናበሪያ ስቱዲዮ ውስጥ እና በአንድ ማቀናበሪያ የሚሠሩ በርካታ የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችም አሉ:: እነዚህን ሙዚቃዎች የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች ናቸው ብዬ አድገዋል ወይም አላደጉም ለማለት እቸገራለሁ:: እንደ ግል ሃሳቤ ግን የኢትዮጵያ ሙዚቃዎች መባል ያለባቸው በሀገራችን የሙዟቃ መሣሪያዎች እና በሀገራችን የሙዚቃ ቅኝቶች የተሠሩት ናቸው::
የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖረው ሙሉ በሙሉ የውጭ የሙዚቃ መሣሪያዎችን መጠቀም አለብን ከሚሉት ወገን አይደለሁም:: የኢትዮጵያ ሙዚቃ በኢትዮጵያ የባሕል የሙዚቃ መሣሪያዎች እና በኢትዮጵያ የሙዚቃ ቅኝቶች ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን ማግኘት ይችላል ብዬ የማስብ ሙዚቀኛ ነኝ:: ይህ ደግሞ በቅርብ ጊዜ እንደሚሆንም እርግጠኛ ነኝ:: እስከዚያው ድረስ ግን የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከዓለም ሙዚቃ ጋር እያነፃፀርኩኝ አድጓል ወይም አላደገም ለማለት እቸገራለሁ:: በግል እይታዬ ግን አላደገም ከሚሉት ወገን ነኝ::
ከከያኒ አስቻለው ፈጠነ ጋር በቀጣይ እትማችን የባህል ሙዚቃ ላይ ለምን አተኮርክ? የባህል ሙዚቃ መሣሪያዎቻችን ምን አዲስ ቀለም አመጡ? ከሀገር ውስጥ ሙዚቀኞች ማንን አርዓያህ አደረክ? ለውጭ ሙዚቃዎች ያለህ አተያይ ምንድነው? ሙዚቃዎቻችን በዓለም እንዲታወቁ ምን ይሠራ? የብሔረሰብ ሙዚቃዎችን ለመሥራት ያለህ ሃሳብ ምን ይመስላል? በሚሉ እና ሌሎችም ጥያቄዎች እንመለሳለን::
(እሱባለው ይርጋ)
በኲር የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም