ቀይ ባሕር ወደ አውሮፓ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ሰሜን እና ምሥራቅ አፍሪካ እንዲሁም ወደ እስያ ለሚላኩ ሸቀጦች እና የተለያዩ ምርቶች ቁልፍ መተላለፊያ ነው። በሰሜን በኩል የግብፁን ስዊዝ ካናል እንዲሁም በደቡብ አቅጣጫ ጂቡቲ፣ የመን እና ኤርትራን በሚያዋስነው የባብ አል-ማንዳብ መካከል ይገኛል፤ ቀይ ባሕር የዓለማችን 12 በመቶ ወይም አንድ ትሪሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ምርት በየዓመቱ የሚተላለፍበት የውኃ ክፍል ነው።
ቀደም ሲል ይህን አካባቢ ዋና ትኩረታቸው አድርገው የነበሩት እንደ አሜሪካ እና ቻይና ያሉ ኃያላን ሲሆኑ፣ አሁን ግን የአፍሪካ ቀንድ ለአዳዲስ ተወዳዳሪዎች ወሳኝ የፉክክር ሜዳ ሆኗል። ሳዑዲ ዐረቢያ፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች፣ ቱርክ፣ ኳታር፣ ኢራን እና ግብፅ በአፍሪካ ቀንድ ጥቅሞቻቸውን በአካባቢው ለማስጠበቅ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ዋና ቀጣናዊ ተዋናዮች ናቸው።
በአሁኑ ጊዜ አሜሪካን፣ ፈረንሳይን፣ ጃፓንን፣ ቻይናን፣ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶችን እና ቱርክን ጨምሮ ዐሥራ አንድ ሀገራት በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ የጦር ኃይል ሰፈር አላቸው፡፡
ይሁንና የቅርብ ጊዜ ጂኦፖለቲካዊ ክስተቶች የአካባቢውን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ በማሳደጉ ቀይ ባሕር ታላቅ የኃይል ሽኩቻ ምህዋር ሆኗል።
የፋይናንስ መረጃዎችን በመተንተን የሚታወቀው ኤስ ኤንድ ፒ ግሎባል ማርኬት ኢንተሊጀንስ (S&P Global Market Intelligence) በቅርቡ በሠራው የገበያ ጥናት እንዳሳየው አውሮፓ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ወደ ሀገር ውስጥ ካስገቧቸው ምርቶች 15 በመቶ ያህሉ ከእስያ እና ከባሕረ ሰላጤው ሀገራት በቀይ ባሕር በኩል ያለፈ ነው።
ቀይ ባሕር ከፍጆታ ዕቃዎች በተጨማሪ ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ እና የጋዝ ምርት መተላለፊያም ነው።
ማሪን ኢንሳይት (Marine Insight) እንዳስነበበው በቀይ ባሕር ጠረፎች ዐሥር ግዙፍ እና ሥራ የሚበዛባቸው ወደቦች አሉ፡፡ የጂዳ ወደብ አንዱ ሲሆን፣ በዓመት ወደ 52 ሚሊዮን ቶን ጭነትን፣ አራት ሚሊዮን ኮንቴይነሮችን (TEU) እና ሦስት መቶ ሺህ ገደማ መንገደኞችን ያጓጉዛል።
ስምንት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ቶን ጭነት እና 431 ሺህ ኮንቴይነሮች የሚጓጓዙበት ደግሞ ፖርት ሱዳን ነው።
ሌላው ቀይ ባሕር ላይ የሚገኘው የጂቡቲ ወደብ፣ ከአምስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ቶን በላይ ጭነት እና 293 ሺህ ኮንቴይነሮች በዓመት ይተላለፍበታል። በኤርትራው ምፅዋ ወደብ ደግሞ በዓመት ከስምንት መቶ ሺህ ቶን በላይ ጭነት ያልፋል።
የሳዑዲ ዓረቢያ ንብረት የሆነው ያንቡ የንግድ ወደብም አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ በዓመት 13 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቶን ጭነት የሚያስተናግዱ 12 ማረፊያዎች እና አንድ ሺህ 500 መንገደኞችን ማስተናገድ የሚችል ልዩ የመንገደኞች ተርሚናል አለው።
የግብፅ ንብረት የሆነው ሳፋጋ ወደብም አንድ መቶ ሺህ ቶን የመጫን አቅም ያለው የእህል ሲሎ ያለው ነው፤ በዓመት ወደ 742 መርከቦችን በማስተናገድ ከሦስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ቶን በላይ ጭነት እና ከ876 ሺህ በላይ መንገደኞችን ያጓጉዛል።
የእስራኤሉ ኢላት ወደብ ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ቶን ደረቅ ጭነት፣ 70 ሺህ መኪኖችን እና 50 ሺህ ኮንቴይነሮች በየዓመቱ ያልፉበታል። ሆዴዳ ወደብ የየመን ንብረት ነው፤ አንድ ሚሊዮን ቶን የፔትሮሊየም ምርቶችን ጨምሮ አምስት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ቶን ጭነት ያስተናግዳል።
የኤርትራው አሰብ ወደብ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ቶን ደረቅ ጭነት፣ 32 ሺህ ኮንቴይነሮች እና አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ቶን ፈሳሽ ጭነት ይተላለፍበታል። የየመኑ ኤደን ወደብም በዓመት ሁለት ሺህ መርከቦችን የማስተናገድ አቅም ያለው ነው፤ ዐሥራ አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ቶን ጭነትና 380 ሺህ ኮንቴይነሮች ይተላለፉበታል፡፡
ይህን ያህል ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ ያለውና የኃያላኑ የዐይን ማረፊያ የሆነው ቀይ ባሕር ታዲያ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ይገኛል፤ ሁቲ የተሰኘው የየመኑ አማጺ ቡድን ደግሞ የስጋቱ ባለቤት ነው፡፡
አማጺያኑ በቀይ ባሕር ላይ የሚያልፉ ዕቃ ጫኝ መርከቦችን በሚሳኤል እና በድሮን ዒላማ ካደረጉ ውለው አድረዋል፤ በዚህም ምክንያት ግዙፍ የመርከብ ድርጅቶች በቀይ ባሕር መስመር ከመጓዝ ታቅበዋል፤ ይህም የነዳጅ እና የሌሎች ምርቶችን ዋጋ ከፍ አድርጓል።
ሰፊ የየመን ግዛትን ተቆጣጥረው የሚገኙት የሁቲ አማጺያን ከእስራኤል እና ከሐማስ ጦርነት መቀስቀስ ወዲህ በቀይ ባሕር በኩል በሚያልፉ ግዙፍ የጭነት መርከቦች ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።
አማጺያኑ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ ለገባው ሐማስ ያላቸውን ድጋፍ በይፋ ከገለጹ በኋላ፣ በቀይ ባሕር በኩል አድርገው ወደ እስራኤል የሚያቀኑ መርከቦችን ዒላማ እንደሚያደርጉ አሳውቀዋል።
አማጺያኑ ባለፉት ወራት ወደ ተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ነዳጅ እና የተለያዩ ምርቶችን ጭነው የሚንቀሳቀሱ ግዙፍ መርከቦችን በሚሳኤል እና በድሮን ሲያጠቁ እና እገታ ሲፈጽሙ ነበር።
ታዲያ ይህ ስጋት ውስጥ የከተታቸው የዓለማችን ዋነኛ የመርከብ ጭነት ማጓጓዣ ድርጅቶች ቀይ ባሕርን ከመጠቀም ይልቅ ረዥም ጊዜ እና ብዙ ነዳጅ አባክነው በደቡብ አፍሪካ በኩል አድርገው ወደ መዳረሻቸው እያቀኑ ነው።
የሁቲ አማጺያን በቀይ ባሕር ላይ በፈጠሩት የደኅንነት ስጋት ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ በነዳጅ እና በሌሎች ምርቶች ዝውውር ላይ ጫናን በመፍጠር የዋጋ ጨማሪ ሊያስከትል እንደሚችል ቢቢሲ ዘግቧል።
ባሳለፍነው ታኅሳስ ወር 2016 ዓ.ም በነዳጅ ዋጋ ላይ አነስተኛ ሊባል የሚችል ጭማሪ የተመዘገበ ሲሆን፣ የዋጋ ጭማሪውም እየናረ መሄዱ የሚቀር አይመስልም። ይህ ደግሞ አጠቃላይ የዋጋ ንረትን ሊያስከትል እንደሚችል ነው የተሰጋው፡፡
በመርከብ የንግድ ሥራ ላይ ዘገባዎችን የሚሠራው ሎይድስ ሊስት ጋዜጣ ዋና አርታኢ የሆኑት ሪቻርድ ሜድ የንግድ መርከቦች የጉዞ አቅጣጫቸውን መቀየራቸውን የሚቀጥሉ ከሆነ፣ በዓለም አቀፍ የምርት አቅርቦት ሰንሰለት ላይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ ስለሚያስከትል በዋጋ ላይ የሚመጣው ጭማሪ ቀላል አይሆንም ይላሉ።
ሪቻርድ ሜድ በየዓመቱ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ምርት የሚመላለስበት የቀይ ባሕር መስመር ከአገልግሎት ውጪ መሆን የሚያስከትለው ጭማሪ በነዳጅ ዋጋ ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቀር እንዳልሆነ ያሳስባሉ።
ከቀናት በፊት ኤቨርግሪን ላይን እና ሜርስክ የተባሉት የዓለማችን ግዙፍ የመርከብ ጭነት ማጓጓዣ ድርጅቶች እና ብሪቲሽ ፔትሮሊየም (ቢፒ) የተባለው የነዳጅ አምራች ኩባንያ በደኅንነት ስጋት ምክንያት በቀይ ባሕር በኩል ጉዞ እንደማያደርጉ አሳውቀዋል። የጋዜጣው ዋና አርታኢ ታዲያ “የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶችን፣ አልባሳትን፣ የጉዞ አቅጣጫ እየቀየሩ ያሉት የፍጆታ ዕቃዎችን እና ሌሎችን የሚጭኑት ግዙፍ ኮንቴይነር ተሸካሚ መርከቦች ናቸው” ብለዋል፤ ይህም የዋጋ ጭማሪው ከነዳጅ በተጨማሪ በሌሎች ቁሶች ላይ ሊከሰት እንደሚችል ማሳያ መሆኑን ይገልጻሉ።
የኤክስፖርት ኤንድ ኢንተርናሽናል ትሬድ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ማርኮ ፎርጂኦና ደግሞ መርከቦች አቅጣጫ እንዲቀይሩ መገደዳቸው ከምርት ዋጋ በተጨማሪ የመርከቦችን የነዳጅ እና የመድን ወጪን ይጨምራል ይላሉ። ይህ ብቻም ሳይሆን በወደቦች መጨናነቅ እና መዘግየት ሊፈጥር ይችላል ባይ ናቸው። ይህ የነዳጅ እና የሌሎች ምርቶች ዋጋ ጭማሪ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና በተለያዩ ጦርነቶች ጫና በደረሰበት የሀገራት ምጣኔ ሀብት ላይ ሌላ ዙር የዋጋ ንረትን ያስከትላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ቀይ ባሕር ላይ የተፈጠረው የደኅንነት እጦት ብዙ ካከሰራቸው ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ ግብፅ ናት። መርኮቦች ወደ ቀይ ባሕር የውኃ ክልል የሚገቡት ወይም የሚወጡት የሱዊዝ ካናል መተላለፊያ ቦይን ተጠቅመው ነው። ግብፅ በዚህ ሰው ሠራሽ በሆነው መተላለፊያ ከሚያልፉ መርከቦች ከፍተኛ ገንዘብ ትሰበስባለች። ሰዊዝ ካናል ከግብፅ ዋነኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ መንገዶች መካከል አንዱ ነው። የቻይና ዜና ወኪል ዢንዋ የግብፅ የስዊዝ ካናል አመራሮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ግብፅ በአውሮፓውያኑ 2022 – 23 የበጀት ዓመት ከመተላለፊያው ዘጠኝ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ችላለች። በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥም አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ቶን ጭነት የያዙ 25 ሺህ 887 መርከቦች በካናሉ በኩል አልፈዋል፡፡
በቀይ ባሕር በሚተላለፉ መርከቦች ላይ የሁቲ ታጣቂዎች የደቀኑት ስጋት መንገዳቸውን እንዲቀይሩ በማድረጉ ገቢዋ አደጋ ላይ የወደቀው ግብፅ ባለሥልጣናት ሁኔታው እንዳሳሰባቸው እና በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑን ገልጸዋል።
የስዊዝ ካናል ባለሥልጣን ዋና ሰብሳቢ ኦሳማ ራቢ ከሁለት ቀናት በፊት ባወጡት መግለጫ ከኅዳር 9/2016 ዓ.ም ወዲህ 55 መርከቦች የጉዞ አቅጣጫቸውን ቀይረዋል ስለማለታቸው ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል። አንዳንድ ሪፖርቶች ግብፅ በስዊዝ ካናል በኩል ከሚያልፉ መርከቦች በአማካይ 250 ሺህ ዶላር እንደምታስከፍል ይጠቁማሉ።
ምዕራባውያን ግዙፍ መርከቦቻቸው በሚቀዝፉበት ቀይ ባሕር ላይ የጦር መርከቦቻቸው ይገኛሉ። በርካቶቹም ለባብ አል-ማንደብ ቅርብ በሆነችው ጂቡቲ ውስጥ የጦር ሰፈር በመገንባት ወታደሮቻቸውን አስፍረዋል።
ታዲያ ይህን በዓለም የንግድ ሰንሰላት ላይ ስጋት የደቀነውን የየመን ሁቲ አማጺያን ጥቃትን ማስቆም ለምን ከባድ ሆነባቸው? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። በሰሜን ካሮላይና ክምፕቤል ዩኒቨርሲቲ የባሕር ኃይል ታሪክ መምህር የሆኑት ሳል ሜርኮጂሊያኖ የሁቲ አማጺያን ጥቃትን መከላከል ከባድ ያደረገው አማጺያኑ የሚተኩሱት ተወንጫፊ ሚሳኤል በመሆኑ ነው ይላሉ።
“ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን መካላከል በጣም ከባድ ነው። በታሪክ መርከቦች በባሊስቲክ ሚሳኤል ዒላማ ሲደረጉ ስንመለከት ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው” ብለዋል፡፡ መምህሩ ጨምረውም ባሊስቲክ ሚሳኤሎች ዒላማቸውን ከመምታታቸው በፊት አየር ላይ እንዳሉ መትቶ የመጣል ወታደራዊ አቅም ያላቸው በጣም ውስን መርከቦች ብቻ መሆናቸውን ያነሳሉ።
በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማጺያን ከሳዑዲ ዐረቢያ መራሹ ኃይል ጋር በየመን ለዓመታት ሲዋጉ ቆይተዋል፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ቀይ ባሕርን ዒላማቸው አድርገዋል፡፡
የሁቲ አማጺያን ሚሳኤል እና ሰው አልባ አውሮፕላን እየተጠቀሙ ደኅንነቱን ያራቁበትን የቀይ ባሕርን ሰላም መልሶ ለማረጋገጥ አሜሪካ ቆርጫለሁ እያለች ነው። አሜሪካ መስተጓጎሉን ለማስቀረት እና በቀይ ባሕር ላይ የሚንቀሳቀሱ መርከቦችን ደኅንነት ለመጠበቅ ከሌሎች ሀገራት ጋር በመጣመር ዓለም አቀፍ የባሕር ላይ ዘመቻ ጀምራለች። ይህን ጥምረት እንደ ዩናይትድ ኪንግደም (እንግሊዝ)፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ባሕሬን፣ ኖርዌይ እና ስፔንን የመሳሰሉ ሀገራት ተቀላቅለዋል።
በጉዳዩ ላይ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ከ40 በላይ ከሚሆኑ ሀገራት ከተወጣጡ ሚኒስትሮች ጋር በነበራቸው ውይይት ሌሎች ሀገራት ለደኅንነት ሥራው የበኩላቸውን እንዲያዋጡ ጠይቀዋል። “ግድየለሽ የሆነው የሁቲ አማጺያን ጥቃት ጠንካራ ዓለም አቀፍ ምላሽን የሚፈልግ ከባድ ዓለም አቀፍ ችግር ነው” ብለዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም መከላከያ ሚኒስቴር የሚሳኤል ጥቃቶችን ማክሸፍ የሚችለው ግዙፍ የጦር መርከብ ዓለም አቀፍ ጥረቱን እንደሚቀላቀል አስታውቋል። ምዕራባውያኑ የቀይ ባሕር ደኅንነትን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ አቋማቸውን ቢያሳዩም አጓጓዦች ግን አሁንም ደኅንነት አይሰማንም በማለት ጊዜ እና ነዳጅ የሚጨርሰውን ረጅሙን የሕንድ ውቅያኖስ መስመርን እንደመረጡ ናቸው።
ግዙፉ የዴንማርክ የመርከብ ጭነት ማጓጓዣ ድርጅት ሜርስክ የቀይ ባሕርን ደኅንነት ለማረጋገጥ ዓለም አቀፍ ጥረቶች መጀመራቸው እጅግ የሚበረታት ነው፤ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ መርከቦቹ ወደ ቀይ ባሕር መቼ እንደሚመለሱ ለመወሰን ከባድ ነው ብሏል።
ግዙፎቹ የመርከብ ጭነት አጓጓዦች ቀይ ባሕርን ትተው በደቡብ አፍሪካ ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ በኩል ስድስት ሺህ 400 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ለተጨማሪ 10 ቀናት መጓዝ ይጠበቅባቸዋል።
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም