መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም
“ታጁ” በተሰኘው አስቂኝ ዘውግ ባለው የፊልም ሥራው ተወዳጅነትን አግኝቷል:: በተለያዩ ድራማዎች፣ ቲያትሮች እና ፊልሞች ላይ በደራሲነት፣ አዘጋጅነት እና ተዋናይነት ተሳትፏል:: በአማራ ክልል የፖሊስ ሙዚቃ እና ቲያትር ክፍል የቲያትር ደራሲ፣ አዘጋጅ እና መሪ ተዋናይ ሆኖ እየሠራ ይገኛል:: ለዘመናት ያካበተውን የትወና ጥበብ ለተተኪው ትውልድ ለማሻገር እየጣረ ነው:: በዚህም ለሦስት ተከታታይ ጊዜ ሰልጣኞችን አብቅቶ አስመርቋል:: የተቀዛቀዘው የፊልም እና ቲያትር ጥበብ እንዲያንሠራራ ዓላማ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል:: የዚህ እትም የበኲር እንግዳችን ሁለገቡ ከያኒ ታጠቅ ለገሰ (ታጁ) ነው:: መልካም ንባብ!
የትውልድ፣ የእድገት እና የትምህርት ሁኔታህ ምን ይመስላል?
የተወለድኩት ደሴ ከተማ ነው፤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን እዛው ወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት ነው የተማርኩት:: የፖሊስ ልጅ ነኝ፤ እናም የፖሊስ ልጅ መንደር የለውም ይባላል እና ሰባተኛ እና ስምንተኛ ክፍልን በጅማ ከተማ ነው የተማርኩት:: ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ ወደ ደሴ ተመልሼ በወይዘሮ ስህን (በዛን ጊዜ የካቲት 66 ነበር የሚባለው) ጨረስኩ::
ወደ ትወናው እንዴት ገባህ?
ሰው ወደ አንድ ነገር የሚሳበው ወይም የሚገባው በተለያየ መንገድ ነው፤ እኔም ለትወና ልዩ ፍቅር ነበረኝ:: ጎበዝ ተማሪ ስለነበርኩ ትምህርቴን እንዳይጎዳብኝ ስለምፈራ ለመጀመር አመነታ ነበር:: አንድ ጊዜ ግን አንድ ፈገግ የሚያሰኝ አጋጣሚ ገፍቶ አስገባኝ:: ጉዳዩ እንዲህ ነው፤ እኔ መምህር ክፍል ውጥ በሌለ ጊዜ መውጣት እና በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ መዞር አላውቅም፤ አልወድምም ነበር:: መምህር ከክፍል ከሌለ አርፌ ቁጭ እላለሁ ወይም መጽሐፌን አነባለሁ::
ታዲያ አንድ ቀን ግን መምህር በመቅረቱ ልጆች ሲወጡ እኔም ምን እንዳነሳሳኝ አላውቅም ተከትየ ወጣሁ:: እንደ አጋጣሚ በትምህርት ቤታችን የሚፈሩ ርዕሰ መምህር አዩኝ:: በዚህ ጊዜ በደመ ነፍስ ከእሳቸው ለማምለጥ ወደ አዳራሽ አቀናሁ:: ከኋላየ እሳቸውም ዝም ብለው ይከተሉኛል:: ወደ አዳራሹ ስደርስ ከውስጥ መድረክ ላይ መዓዛ ፍቅሩ የምትባል ልጅ ተማሪዎችን በቲያትር ክለብ ትመዘግባለች:: ወደ ውስጥ ስገባ “አንተ ልጅ ልትመዘገብ ነው የመጣህ?” አለችኝ:: “አዎ” አልኩ፤ ርዕሰ መምህሩ ወደ እኛ ተመለከቱ እና ተመልሰው ሄዱ::
ለትወና ፍላጎት በጣም ነበረኝ:: ግን ሳመነታ ትወናን ሳልጀምረው ቆይቻለሁ፤ በዛች አጋጣሚ ከርዕሰ መምህሩ ለማምለጥ ስል ግን ተመዘገብኩ፤ በዚያው ዕለት የትወና ድርሻ ተሰጠኝ:: በዚያን ዘመን የቲያትር ባለሙያው ከበደ መስፍን ይባሉ ነበር፤ በዚያው ትወናውን ጀመርኩ፤ ተቀባይነቱ በወቅቱ እጅግ ትልቅ ነበር:: በትምህርት ቤቱ ሳይወሰን ዝናችን በደሴ ከተማ ሁሉ ናኘ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከትወና ተለያይቼ አላውቅም::
ከትወና ውስጥ ወደ አስቂኝ ዘውግ የበለጠ ትሳባለህ። ይህ ከምን መጣ?
የትወና ችሎታ እንዳለህ የምታስመሰክረው፣ ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከሰፈር ከትምህርት ቤት እያለ በሚሰጥህ አስተያየት ነው:: ይህ እንዳለ ካወኩ በኋላ በዘመናችን ይሰሩ የነበሩ የመድረክ እና የፊልም የኮሜዲ ሥራዎች ነበሩ፤ ለምሳሌ እነ መላኩ አሻግሬ ነበሩ:: መላኩ አሻግሬ ይሄኛው ትውልድ ብዙም ባያውቃቸውም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር ስር ሆነው እየዞሩ የሚያሳዩት የኮሜዲ ቲያትር ነበር:: እሱን እና ሌሎችን ማየቴ ተጽዕኖ አድርጓል:: የምሰራቸው ቲያትሮች ላይም ተጽዕኖው እንዳለ ሰዎች ይነግሩኝ ነበር::
በኋላ የቲያትር ትምህርት ስማር እና ስልጠናዎችን ስወስድ ወደ ኮሜዲው የበለጠ መሳብ ጀመርኩ:: ኮሜዲ እንደ ሌላው ትወና ቀላል አይደለም:: ኮሜዲ ማለት በተለያየ ነገር አዕምሮው ተወጥሮ እና ተይዞ የሚመጣን ሰው ዘና ማድረግ ነው:: አንዳንድ ጊዜ ሰው እንኳን ቀልደኸው ኮልኩለኸውም አይስቅም:: በሌላ በኩል ደግሞ ኮሜዲ ህክምናም ነው፤ ሰውን ከያዘው ጭንቀት መፈወስ:: በኮሜዲው ዘርፍ ተሳክቶልኛል ብየ ነው የማስበው:: ለዚህም ማሳያው ታጁ የሚባለው ከሰው አዕምሮ የማይጠፋው ገጸ ባሕሪ ነው:: ይህ አድጎ በቴሌቪዢን እና በማሕበራዊ መገናኛዎች ተከታታይ ሥራዎችን እየሠራሁበት ነው፤ አቀባበሉም ጥሩ ነው::
ከታጁ በፊት የተሳተፍክባቸውን ሥራዎች ንገረን?
በ1980ዎቹ በነበሩ ትምህርት ቤቶች ይሠሩ የነበሩ ቲያትሮች በብዛት የእነ ሞሊየር ድርሰቶች ነበሩ፤ ለአብነት “የፌዝ ዶክተር” ተጠቃሽ ነው:: በሀገራችን ደግሞ እነአስታጥቃቸው ይሁን “የመንደሩ መርፌ ወጊ”፤ በኋላ ደግሞ የእነ ደበበ ሰይፉ ከባሕር የወጣ አሳ አለ:: ከትምህርት ቤት ከወጣን በኋላ የቲያትር ቡድን አቋቁመን መሥራት ጀመርን:: ቲያትርን ከትምህርት ቤት ውጪ የጀመርኩት የመንደሩ መርፌ ወጊ በሚለው ነው:: በአማተር ደረጃ በወሎ እና በአፋር እየዞርን እናሳይ ነበር፤ የራሴንም ድርሰቶች መጻፍ ጀመርኩ:: በኋላ በአማራ ፖሊስ ሥር ፕሮፌሽናል {ሙያተኛ} የሆኑ አባሎችን ለመመልመል ማስታወቂያ ሲወጣ ተወዳድሬ አለፍኩ:: እዚህ ከመጣሁ በኋላ በተዋናይነት፣ በደራሲነት፣ በአዘጋጅነት እና በመድረክ መሪነት ለረጅም ዓመታት እያገለገልኩ እገኛለሁ::
በድራማ፣ ቲያትር እና ፊልም መካከል ያለውን ልዩነት አስረዳን፤ አንተስ የትኛውን የበለጠ ትመርጣለህ?
ቲያትር የምንለው ሰፊ ነው:: አጠቃላይ መድረኩን፣ ሙዚቀኛውን፣ ተዋናዩን፣ ድራማውን የሚይዝ ነው:: ድራማ ደግሞ በንግግር እና ድርጊት የተሞላ አንድ የቲያትር ክፍል ነው፤ ፊልም በቀረጻ የሚከወን የሚቀናበር እና የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች የሚጨመሩበት አዘጋጁ አፍርሶ የሚሠራው የስክሪን ሥራ ነው:: ከእነዚህ ከሦስቱ የበለጠ የትወና ክህሎት የሚጠይቀው እና አድካሚው ቲያትር ነው፤ በቲያትር ተመልካቹ ሳይቀር ተሳታፊ ነው:: በተዋናዩ እና በታዳሚው መካከል መስተጋብር አለ:: በመሆኑም ቲያትር የበለጠ ይስበኛል::
የትወና ፍላጎት ያላቸውን ልጆች ታሰለጥናለህ፤ እስኪ ስለ እነሱ ንገረን?
ረጂሙን ጊዜየን ያሳለፍኩት በስልጠና ነው፤ ስልጠና የሚሰለች እና የሚቆም አይደለም:: ይሄን ለ30 ዓመታት ያክል በስልጠና ያካበትኩትን ልምድ፣ እውቀት እና ክህሎት እኔ ጋር ብቻ እንዲቀር አልፈልግም፤ ስልጠናውን ለመስጠት አንዱ ያነሳሳኝ ምክንያት ይሄ ነው:: ሌላው ደግሞ የጀመርኳቸው ፊልሞች፣ የቴሌቪዢን ተከታታይ ድራማዎች እና ሌሎች ሥራዎች አሉ፤ እነዚህን ለመሥራት ለተዋናዮች ምልመላ ማስታወቂያ እናወጣለን:: ለትወና ትልቁ መስፈርት ሥነ ምግባር ነው:: በፈለክ ጊዜ ክህሎት እና ሥነ ምግባር ያለው ተዋናይ ማግኘት ይከብዳል፤ ያንን ብታበቃው እንኳ ቀጣይነት አይኖረውም፤ ሥራው ካለቀ በኋላ ዳግም ላትገናኝ ትችላለህ::
በዚህኛው ስልጠና መፍጠር የፈለኩት ግን ማስታወቂያ ለጥፌ የአንድ ቀን ቀረጻ እና ምልመላ ከማድረግ ይልቅ ከእኔ ጋር እንደ ቤተሰብ የሆነ፣ በተፈለገው ጊዜ የሚገኝ፣ የሙያው ፍቅር፣ ስነ ምግባር እና የትወና ችሎታ ያለው የሰለጠነ ሰው ነው:: ስለሆነም ስልጠና መስጠት አስፈላጊ ነው:: በተለይ ዋናው ያጣነው ስነ ምግባር ስለሆነ፣ ስነ ምግባር የተላበሱ ሙያተኞችን በተከታታይ እና በብዛት ማፍራት ያስፈልጋል::
ስልጠናውን ከጠበኩት በላይ ነው ያገኘሁት፣ የክልሉ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ አድርጎልኛል። ብሔራዊ ቲያትር ባለሙያዎችን መድቦልኝ ነው ስልጠናው ሲሰጥ የቆየው፣ በዓይነቱ ያልተለመደ በመሆኑ ከሚገባው በላይ ተቀባይነት አግኝቶ ስኬታማ ሆኗል:: ወጣቶቹም በንቃት እና በፍቅር የተከታተሉበት ነው:: በቀጣይ ከትወና ባሻገር በአጠቃላይ በሥነ ጥበቡ ሁለገብ ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት ላይ ነን::
ይቀጥላል
(ቢኒያም መስፍን)
በኲር መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም