ላልይበላ

0
354

ትውልድ አልፎ ትውልድ ሲተካ እነርሱ ግን ከዘመን፣ ከልዩ ልዩ ተፈጥሯዊ ተፅዕኖዎች ጋር እየተጋፈጡ በአንፀባራቂ ውበታቸው እያስደመሙ ዘልቀዋል። ከዘመናት ጋር አብረው እየፈሰሱ የዘለቁ፣ የጥንቱ የኪነ ሕንፃ ጥበብ አሻራ ያረፈባቸው ወደር የለሽ የኢትዮጵያውያን ፍሬዎች ናቸው። የጥንቷን ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያንን ድንቅ ታሪክ፣ ማንነት እና የጥበብ ደረጃ ለዛሬዎቹ የሚያንጸባርቁ፣ ዓለምን ሁሉ ያስደመሙ እፁብ ድንቅ የኢትዮጵያውያን ድንቅ እጆች የሰሯቸው፣ ደጋግመው ቢያዩዋቸው የማይሰለቹ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት የዛሬ የሽርሽር ትኩረታችን ናቸው።

የመካከለኛውን ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ስልጣኔን፣ ባህልን አጣምረው ለመተረክ ለምልክት የቀሩልን ከዓለማችን ሰባቱ ድንቃ ድንቆች ተርታ ለመሰለፍ ምንም የማይጎድልባቸው  የሰሜን ኢትዮጵያ ፈርጦች በቀድሞዋ ሮሃ  በዛሬዋ ላሊበላ በላስታ ምድር ይገኛሉ። ከ1182 እስከ 1217 ዓ.ም  ኢትየጵያን በመራው ንጉሥ ላሊበላ እንደተገነቡ ይታመናል። ንጉሥ ላሊበላ በርካታ ቤተ ክርስቶያኖችን በመገንባት ይታወቃል። ከእነዚህ መካከል እጅግ የጎሉት አስራ አንዱ ሮሃ ውስጥ ከወጥ አለት የተፈለፈሉት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።

ከአክሱም ዘመን የቀጠለው የዛግዌ ስርወ መንግስት የኪነ ሕንፃ ስኬት አብነቶች ናቸው። አይነት እና ስሪታቸው ከአፍሪካ ሆነ ከዓለም የትም የሌለ፣ የኢትዮጵያውያን የኩራት ምንጭ ሆነው ዘመን ተሻግረዋል። ከተለመደው የሕንፃ አሰራር ምህንድስና ባልተለመደ መልኩ ግንባታቸው ከጣሪያ የሚጀምር ስራ ቢፈለግ ከኢትዮጵያ ውጭ የትም የለም ለማለት የሚያስደፍሩ የዘመኑ የኪነ ሕንፃ ምህንድስና ውጤቶች መሆናቸውን ለተመለከታቸው ሁሉ ይመሰክራሉ።

ንጉሥ ላሊበላ ላሊበላ ያሉትን ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ከመገንባቱ በፊት በሌሎች አካባቢዎች ጀምሮ ያልጨረሳቸው ስለመኖራቸው በአንድ ወቅት ጃን አሞራ ለስራ ጎራ ባልንበት ወቅት ተመልክተናል። ሰረባር ባለእግዚአብሔር ይባላል። አሁን ዓለም ከሚያውቃቸው አብያተ ክርስቲያናት በፊት እንደተሰራ አባቶች ያስረዳሉ። ከአለት የተፈለፈለ ዋሻ ነው፡፡ በውስጡ ከአለቱ የተጠረቡ አምዶች ቆመዋል። ነገር ግን አልተጠናቀቁም። አባቶች እንደነገሩን ንጉሥ ላሊበላ ይህን ሳይጨርስ በመለኮታዊ ምሪት ወደ ላሊበላ በመሄድ አሁን ድረስ የሚታወቅበትን ስራዎቹን አሳክቷል። ሰረባር ባለእግዚአብሄር ለንጉሥ ላሊበላ ቀጣይ ስራዎች መሰረት የጣለለት ነው።

እግራችን የላሊበላን ምድር እንደረገጠ አእምሯችን በመቶዎቹ ዓመታት ወደ ኋላ በታሪክ ሰረገላ ላይ ተጭኖ መጓዝ ይጀምራል። ለአብያተ ክርስቲያናት መገንባት መነሻ ምክንያት መሆኑ የሚነገረው በዘመኑ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ለመንፈሳዊ አምልኮ ወደ እየሩሳሌም ይጓዙ ነበር። በዚህም የሚደርስባቸው የጉዞ እንግልት ከባድ ነበር። እናም የምእመኑን ችግር የተመለከተው ንጉሡ ላሊበላ እየሩሳሌም በሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ንድፍ ተመሳሳይ የሆኑ አብያተ ክርስትያናትን በኢትዮጵያ ምድር ለመገንባት መነሳሳቱን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

ባሕሩ ዘውዴ፣ ጥንታዊ እና መካከለኛው የኢትዮጵያ ታሪክ በተሰኘው መፅሀፍ እንደገለፁት ንጉሥ ላሊበላ በኢየሩሳሌም ያሉትን የአብያተ ክርስቲያናት ንድፍ በጥንቃቄ ካጠና በኋላ አምሳያውን በኢትዮጵያ ምድር መገንባት ጀመረ። አብያተ ክርስቲያናቱን መሀል ለመሀል የሚያቋርጥ የዮርዳኖስ ወንዝ ምሳሌን ተከትሎ በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መሀል የሚያልፍ ወንዝ እንዲኖር በማድረግ ለስራው ምቹ ቦታ በመምረጥ ከአንድ ወጥ አለት በመፈልፈል አስራ አንድ አብያተ ክርስቲያናትን ገነባ።

እንደ ፕሮፌሰር ስርግው ሀብለ ሥላሴ ደግሞ ንጉሥ ላሊበላ ወደ መንግሥተ ሰማያት  በራእይ ሄዶ ባለበት እጅግ ውብ ሕንፃዎችን ይጎበኛል። እናም ፈጣሪ  ራሱ ባመላከተው ስፍራ ላይ ተመሳሳይ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲገነባ አዘዘው። በሌላም ስፍራ ንጉሡ ኢየሩሳሌምን ጎብኝቶ ነበር እና ተመሳሳይ አብያተ ክርስቲያናትን በኢትዮጵያ ለመገንባት እንደተነሳሳ ይነገራል።

ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ በሶስት ምድብ የተሰሩ ሲሆን የተለያየ መንፈሳዊ ውክልና አላቸው። የተወሰኑት ለቅዱሳን የተወከሉ ሲሆን ቤተ ማርያም፣ ቤተ ሊባኖስ እና ቤተ ደናግል ናቸው። ሰማእታትን በመወከል መርቆሪዎስ እና ጊዮርጊስ፣ በመላእክታን የተሰየሙት ደግሞ ሚካኤል እና ገብርኤል  ይገኙበታል።

ጉብኝታችንን በየምድቡ ስንቀጥል  በአንደኛው የአለት ምድብ ውስጥ ቤተ መድሀኒአለም፣ ቤተ ማርያም፣ ቤተ ሚካኤል፣ ቤተ መስቀል፣ ቤተ ደናግል እና ቤተ ጎልጎልታን እናገኛለን። ሁለተኛው ምድብ ቤተ አማኑኤል፣ ቤተ መርቆሪዎስ፣ ቤተ ሊባኖስ እና ቤተ ገብርኤልን ያጠቃልላል። ሶስተኛው ምድብ ብቸኛው ቤተ ጊዮርጊስ ይገኛል። ቤተ ጊዮርጊስ በመስቀል ቅርፅ የተገነባው ታዋቂው ደብር ነው።

ንጉሥ ላሊበላ የኢትዮጵያ ክርስትያኖች በህይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ ኢየሩሳሌምን ሄደው ለመሳም ያላቸውን ጠንካራ ጉጉት ወይም ምኞት ጠንቅቆ ይገንዘብ ነበር። ስለሆነም አብያተ ክርስቲያናቱ ሰማያዊ እና ምድራዊውን ሕይወት እንዲወክሉ  ባቀደው መሰረት ገንብቷቸዋል።

እነ ቤተ መድሀኒአለም ያሉበትን የመጀመሪያውን የቤተ ክርስቲያኖች ምድብ ብንጎበኝ ዘመን ተሻጋሪ ውበት፣ አስደናቂ የኪነ ሕንፃ ጥበብ ይንፀባረቅባቸዋል። ሁሉም በአንድ ወጥ ረዥም ወለል ላይ በአንድነት ተያይዘው ተገንብተዋል። የእነዚህ ቤተ ክርስቲያኖች እጅግ የሚያስደንቀው ነገር በአንድ ቋጥኝ ድንጋይ ብቻ ተጠርበው እንደ ዋሻ መሰራታቸው ነው። በዚህ ምድብ ውስጥ ነው ትልቁ ቤተክርስቲያን የሚገኘው፥ 24 ሜትር ስፋት፣ 34 ሜትር ርዝመት ያለው ቤተ መድኃኒአለም መሆኑን አባ ጋስፓረኒ ፅፈዋል።

ፕሮፌሰር ስርግው፣ አኒሸንት ኤንድ ሜዲቫል ሂስትሪ ኤፍ ኢትዮጵያ፣ በሚለው መፅሀፋቸው ላይ እንደፃፉት የመጀመሪያው ምድብ ቤተክርስትያኖች የተሰሩት ምድራዊዋን እየሩሳሌም እንዲወክሉ ተደርገው ነው። ለምሳሌ ቤተ ማርያም ጌተሰማኔን፤ ቤተ መድሀኒት አለም የቃል ኪዳኑን ታቦት የማደሪያ ድንኳን፤ ቤተ ጎልጎልታ ደግሞ የቅዱሱን መቃብር እንዲሁም ቤተ ደናግል የክርስትና እሴቶች የሆኑትን እምነት እና ፍቅርን ይወክላሉ። እንዲሁም የቦታ ስሞች ከቅዱስ ምድር ጋር ይመሳሰላሉ። ከጎልጎልታ ሰሜን ምእራብ በኩል ከአንድ ወጥ አለት የተጠረበ መስቀል፣ በቀራኒዮ የሚል ስም ተሰጥቶት እናገኛለን። ከዚህ ስር ያለው ቦታም የአዳም መቃብር ተብሏል። የተወሰነ ዝቅ ሲል ደግሞ አንድ ወቅት ሰባት የወይራ ዛፎች የነበሩበት ቦታ ዐውደ ፍትሕ ተብሏል፡፡ ይህም ክርስቶስ እንዲሰቀል የተወሰነበትን የፍርድ ስፍራ ይወክላል። የአሁኑ ሰቨን ኦሊይቭ ሆቴል ካለበት ስፍራ ከፍ ብሎ ያለው ተራራ ደብረ ዘይት የሚል ስም ይዟል። ክርስቶስ የተያዘበትን ስፍራ ይወክላል። ክርስቶስ ከትንሳኤው በኋላ የተገለጠበት የመጀመሪያው ስፍራም ቢታኒያ የሚል ስም ተሰጥቶት ይገኛል። በዚህ እግረ መንገዳችንን ለመግለጽ ያህል 11ዱ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የተገነቡበት የመጀመሪያ ስም ወረወር ሲሆን በኋላ ሮሐ በሚል ተቀይሯል።

ከሰሜን ምስራቅ ወደ ደቡብ ምስራቅ የሚፈስ አንድ ወንዝ ዮርዳኖስ ተብሏል። ከሮሃ ከተማ ምስራቅ በኩል ካለው ደብረ ዘይት ከሚባለው ተራራ የሚመነጭ ነው። በክርስትና እምነት መሰረት ዮርዳኖስ ወንዝ የመዳን ምልክት ነው።

ወደ ሁለተኛው ምድብ ስናመራ ቤተ አማኑኤል፣ ቤተ መርቆሪዎስ፣ ቤተ ሊባኖስ እና ቤተ ገብርኤል ተገንብተዋል። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት መንግሥተ ሰማያትን እንዲወክሉ ተደርገዋል፤ ቤተ ገብርኤል የገነትን መንገድ ሲወክል፣ ቤተ ሊባኖስ የእግዚአብሔርን ዙፋን የሚደግፉትን  ኪሩቤልን፤ ቤተ መርቆሪዎስ ገሀነምን እና የስቃይ ቦታን፤ ገነት ደግሞ በቤተ አማኑኤል ሰማያዊዋን እየሩሳሌም እንዲወክሉ ሆነው የተገነቡ ናቸው።

እነዚህ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት እርስ በርስ የሚገናኙበት ጠባብ መተላለፊያዎች አሏቸው። በገድለ ላሊበላ እንደሚነበበው እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን የሚከበርበት የራሱ የንግስ ቀን አለው፣ ለአብነት ሁሌ መስከረም 21 ቤተማርያም፣ የካቲት አራት ቤተ መስቀል እንዲሁም ለታህሣሥ 28 ቤተ አማኑኤል እንደሚከበሩ ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

እኛ ዓለምን ማስደመም ብቻ አይደለም መለወጥ የምንችል ድንቅ ሕዝብ መሆናችንን ሁሌም በእነዚህ ቅርሶቻችን በኩል እናስታውስ። በመጨረሻ ግን በዓለም መታያችን የሆነውን አባቶቻችን የተውልንን አሻራ፣ መሥራቱ እንኳ ቢቀር መጠበቅ መንከባከብ እንዴት ያቅተናል? ላሊበላን እንታደግ እያልኩ ተሰናበትኩ።

(መሰረት ቸኮል)

በኲር መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here