ከውል ውጪ ኃላፊነት

0
281

ከውል ውጪ ኃላፊነት እንዳለብዎት ያውቃሉ? መልካም፤ የዚህ ዕትም ጽሑፋችን የሚያተኩረው ከውል ውጪ ያለ ኃላፊነት ላይ ነው ::   ኃላፊነቶቹ ምን እንደሆኑ እና እንዴት እንደሚከሰቱም  በፍትሕ ቢሮ በፍትሐብሔር ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የክልል አቃቢ ሕግ  ባለሙያ አቶ ጌታቸው ወርቅነህን  አነጋግረናል::

ከውል ውጪ ኃላፊነት ምንጩ ሕግ ሲሆን ከግዴታ የፍትሐብሄር ሕጎችም አንዱ ነው ይላሉ አቶ ጌታቸው :: ከውል ውጭ ኃላፊነት ዋና ትኩረቱ ደግሞ ውል ሳይኖር ስለሚኖር ኃላፊነት ነው:: የውል ኃላፊነት ማለት  ተዋዋዮች በፍላጎታቸው  በውል ግንኙነት የመሠረቱት  የእርስ በርሳቸው ኃላፊነት ብቻ ነው::

ከውል ውጪ ያለ ኃላፊነት ግን መንግሥት ጥበቃ ባደረገላቸው የሰዎች የንብረት እና የሰውነት መብቶች ላይ ጉዳት ሲደርስ ጉዳቱን ያደረሱ ሰዎች በጉዳቱ ልክ እንዲካሱ   የሚያስገድድ ሕግ ነው:: በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2027 ስር እንደተደነገገው ከውል ውጭ ኃላፊነት በሦስት መንገድ ይመነጫል:: (ጥበቃው በሦስት መንገድ ሊደረግ ይችላል)

አንደኛው በጥፋት ላይ የሚመጣ  (በራስ ጥፋት) የሚደርስ ኃላፊነት ነው:: ይሄም አንድ ሰው በሌላ ሰው ላይ በሚያደርሰው  ጉዳት የሚጠየቅበት ነው :: በፍትሐብሔር ቁጥር 2028  ንኡስ ቁጥር  አንድ ስር የተቀመጠው አጠቃላይ ገደብ  ተፈፃሚነት የሚኖረው በጥፋት ተግባር ምክንያት ጉዳቱን  ያደረሱ ሰዎች ተጎጅውን በገንዘብ  እንዲክሱ፣  ከአድራጐታቸው  እንዲቆጠቡ እንዲሁም  ጉዳቱን  በአይነት እንዲክሱ  ፍ/ቤት  ትዕዛዛ ይሰጣል:: ጥፋቱን በቸልተኝነት፣  አስቦ በማድረግም ሆነ ባለማድረግ እንዲጠየቅ እነዚህን ኃላፊነቶች ፍርቤቶች ወይም  ጉዳት በደረሰበት ሰው ጠያቂነት የሚፈፀም ይሆናል::

ሁለተኛው በፍትሐብሔር ቁጥር  ከ2066 እስከ 2089 በተደነገገው መሰረት አንድ ሰው ጥፋት ሳይኖርበት በንብረቱ ለምሳሌ በእንስሳው ፣ በመኪናው እና በሕንፃው  ተጠያቂ ሊሆን ይችላል:: ለአብነት አንድ ተቀጣሪ ሾፌር በጉዞ ላያ እያለ  በተሳፋሪ አልያም በእግረኛ ላይ  ጉዳት ቢያደርስ ሹፌሩም ባለንብረቱም ተጠያቂ ይሆናሉ::  የተጎዳው ሰው ሁለቱንም መክሰስ እንደሚችል በፍትሐብሔር ቁጥር 2156 ተደንግጎ ይገኛል::

በሌላ በኩል የመጀመሪያ ተጠያቂው ባለንብረቱ እንደሚሆንም ባለሙያው ጠቁመዋል::  ለአብነት የመብራት ኀይል የመስመር ዝርጋታ ሲሠራ ፍንዳታ ቢከሰት “አደገኛ ሥራዎች” በሚል በደረሰው ጉዳት መሥሪያ ቤቱ ተጠያቂ ይሆናል:: እንስሳትም ጉዳት ካደረሱ  ባለቤቶቻቸው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ::

ሦስተኛው በሌላ ሰው ተግባር የሚመጣ ኃላፊነት የሚባለው ነው:: ይሄ በፍትሐብሔር ቁጥር  ከ2124 እስከ 2136 ባሉት ስር ተደንግጎ የሚገኝ ነው:: ይህም በሕፃናት ላይ  ወላጆች፣ ሞግዚቶች እና አሳዳጊዎች ጉዳት ቢያደርሱ  ተጠያቂ እንደሚሆኑ በፍትሃብሔር ቁጥር 2124 እና 25 ተደንግጓል:: ከዚህ በተጨማሪም በሌላ ሰው ተግባር የሚመጣ ኃላፊነት በተቋማት  በኩል በመንግሥት  መሥሪያ ቤት ሊሆን ይችላል:: ይህም ሠራተኞች እና ሹመኞች  በሙያ ሥራ ጥፋት ሲፈጽሙ ሊጠየቁ የሚችሉበት ከውል ውጭ ኃላፊነት ነው::

ባለሙያው እንደሚሉት የዚህ ፅንሰ ሀሳብ ዓላማ  በዳይ ባህሪውን እንዲለውጥ እና  በቸልተኝነት የጥፋት ድርጊት እንዳይፈጽም  ማድረግ  ነው::  በዚሁ ምክንያት  በሁለት መንገድ  በዳይ ድጋሚ  እንዲህ ዓይነት    ተግባር  እንዳይፈጽም ማድረግ  ይቻላል::  ለአብነት በዳይ  ለተበዳዩ የካሳ ገንዘብ  እንዲከፍል በማድረግ ነው::  ይህ ሲሆን  በዳይ ገንዘቡን የሚከፍለው ከሀብቱ ላይ  ቀንሶ  ነው::  ይህ  ደግሞ  ለእሱ  ሀብት  ጉዳት ነው::

ሌላው   በጥሩ ሥራ ያፈራው ሥሙና ዝናው  ይሸረሸራል::  በተለይም ደግሞ  በሞያው  አማካኝነት  አገልግሎት  የሚሰጥ ሰው  ለምሳሌ  የሕክምና ዶክተርና  የሕግ ባለሙያ  በቸልተኝነት  በደንበኛቸው  ላይ ጉዳት  ካደረሱ በወደፊት የሙያ ሕይወታቸው ላይ  ትልቅ  ጉዳት አለው፤ ሌላ ደንበኛ አያገኙም ማለት ነው ::

ከውል ውጪ  ኃላፊነት  ሕግ ሌላው  ዓላማው ተበዳይ  በበዳይ እንዲካስ ማድረግ ነው:: ይህም ብዙ  ጊዜ የሚሆነው  በዳይ ለተበዳይ የገንዘብ  ካሳ በአንድ ጊዜ  እንዲከፈል ይደረጋል::

አብዛኛው ሰው በውል እንጂ ከውል ውጪ ኃላፊነት ያለ አይመስለውም፤ በዋናነትም  የቅጣት  ዓላማ የለውም  ያሉት አቶ ጌታቸው፤ ስምምነት ሳይኖር፣ ጥፋት ሳይኖር እንዲሁም  በሌላ ሰው ተግባር ተጠያቂነት እንዳለበት የኅብረተሰቡ ንቃተ ህሊና ዝቅተኛ እንደሆነ አክለዋል::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here