የግዕዝ ቋንቋን ለትውልድ ለማሻገር እና የአብነት ትምህርት ቤቶችን ለመታደግ የሚያስችል የሁለት ዓመት ንቅናቄ ተጀምሯል። “በእንተ ስማ ለማርያም ለእኔ ተማሪ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ፕሮጀክቱ በቁስቋም ቅድስት ማርያም መንፈሳዊ ማኅበር አማካኝነት የሚተገበር ነው።
ማኅበረ ቁስቋም የተለያዩ መንፈሳዊ እና ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ሥራዎችን እየሠራ የሚገኝ ተቋም ነው።
ማኅበሩ በሱስ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን በዕውቀት እና በክህሎት ማብቃት፣ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን ማስከፈት፣ ገዳማትን መደገፍ፣ በሰው ሠራሽ እና በተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ችግር ውስጥ የሚገኙ ገዳማትን እና አድባራትን በማቋቋም የምጣኔ ሀብት ነጻነት እንዲኖራቸው ማድረግ፣ ለሴት መነኮሳት እና ለአቅመ ደካማ አረጋዊ መነኮሳት የንጽህና መጠበቂያ ቁሶችን ማሟላት እንዲሁም የሕክምና አገልግሎት የመስጠት ተግባራትን እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለዘመናት ጥንታዊውን የአብነት ትምህርት ቤትን ይዛና ጠብቃ አሁን እስካለንበት ትውልድ ያደረሰች ናት፡፡
የጥበብ መፍለቂያ ከሆነው የአብነት ትምህርት ቤት ውስጥ የሚያገለግለው የግዕዝ ቋንቋ ደግሞ ጥልቅ እና ሰፊ ምስጢራትን የያዘ ባለፀጋ ቋንቋ ነው፡፡
ነገር ግን ይህ የሀገር ሀብት የሆነው ቋንቋ የቤተክርስቲያን ንብረት ብቻ ተደርጎ ከተወሰደ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ይህም ማንነትን የዘነጋ ትውልድ ስለመኖሩ ማሳያ ነው ተብሏል።
ማኅበረ ቁስቋም ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በሰሜን እና በደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ የአብነት ትምህርት ቤት ዙሪያ ሥራዎችን ለማከናወን ማቀዱ ተነስቷል፡፡
ለዚህም “በእንተ ስማ ለማርያም ለእኔ ተማሪ” በሚል መሪ መልዕክት ከመጋቢት 4 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የዘመቻ ሥራዎቹን እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡
ማኅበሩ የቤተክርስቲያኗን ዶግማ እና ቀኖና በጠበቀ መልኩ በሀገራዊ ጥናት እና ምርምር የሚዘጋጅ ዶክመንተሪ ለማቅረብ ስለመታሰቡም ነው የተገለጸው፡፡
በዘመመ የሳር ጎጆ ውስጥ ለሚገኙ ሁለት የአብነት ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች እና የመምህራን ማረፊያ፣ የመማሪያ ጉባኤ ቤት፣ የምግብ ማብሰያ፣ የተሟላ ቤተ መጻሕፍት፣ የማምረቻ ሼድ ግንባታ ከሙያዊ ሥልጠና ጋር መገንባት፣ በሃያ የአብነት ትምህርት ቤት ውስጥ ለሚገኙ ለአንድ ሺህ 200 የአብነት ተማሪዎች የሁለት ዓመት ቀለብ እና አልባሳት የማሰባሰብ እንዲሁም የሊቃውንት መምህራን ደምወዝ ክፍያ መፈጸም ላይ ማኅበሩ እንደሚሠራም ነው የተገለጸው፡፡
በአብነት ትምህርት ቤቶች አስከፊ የሆነውን ተላላፊ በሽታ ታሳቢ በማድረግ የሙሉ ጤና ምርመራ የሙያ ፍቃድ ባላቸው ብቁ የጤና ባለሙያዎች ለማድረግ ማኅበሩ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጿል።
ማኅበሩ በገዛ ሀገሩ ተናጋሪ ያጣውን የግዕዝ ቋንቋን በመታደግ ሂደት ውስጥ አሻራን ለማሳረፍ የራሳችንን አንድ ተማሪ እናስተምር የሚል ጥሪ አቅርቧል፡፡
(ድልነሳ መንግሥቱ)
በኲር መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም