ግንባታው ከተጀመረ 13 ዓመታትን ሊደፍን የቀናት ዕድሜ የቀረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሙሉ ሥራው በቀጣይ ዓመት ይጠናቀቃል ተብሏል፤ በአምስት ዓመታት እንደሚጠናቀቅ ታቅዶለት የነበረው ግድቡ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው መጓተቱ ይታወቃል:: በችግር ውስጥ ሆኖም ታዲያ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግንባታው እየተፋጠነ ነው ተብሏል::
የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ሰሞኑን እንደተናገሩት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ማመንጫው ግንባታ በሰባት ወራት ይጠናቀቃል፤ ድልድዩና ሙሉ ሥራው ደግሞ በቀጣዩ ዓመት (በ2017 ዓ.ም) ያልቃል::
በእስካሁኑ የግንባታ ሂደት ከ184 ቢሊዮን ብር በላይ የወጣበት ግድቡ 145 ሜትር ከፍታ ይኖረዋል፤ 16 የኃይል ማመንጫ ዩኒቶችም (ተርባይን) አሉት። እያንዳንዱ ዩኒት የሚያመነጨው የኃይል መጠን ደግሞ 375 ሜጋዋት እንደሆነ ነው ከፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ የሚያመላክተው።
ሥራ አስኪያጁ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ለኢትዮጵያ ፕረስ ድርጅት እንዳመለከቱት፤ የግድቡ ግንባታ የሲቪል ሥራው 99 በመቶ ተጠናቋል። ለዚህም ቀንና ሌሊት የሚሠሩ ባለሙያዎች ይመሰገናሉ ብለዋል::
በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎ የሚገነባው የታላቁ ግድብ ግንባታ ከዚህ መድረስ ታዲያ የዘመናት ተስፋችን ዕውን ለመሆን መቃረቡን ማሳያ ሆኗል፤ ይህም ከ65 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የኮረንቲ መብራት ተጠቃሚ ላልሆነባት ሀገራችን ትልቅ ስኬት እንደሚሆን ይጠበቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ85 በመቶ በላይ የታላቁ (ዓባይ) ወንዝ ባለቤቷ ኢትዮጵያ ግድቡን ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ካስቀመጠች ማግስት በተለይ ግብጽ ከፍተኛ ቅሬታዋን አሰምታለች፤ የግድቡ ግንባታ እንዲቋረጥም ያላደረገችው ሙከራ የለም:: ይሁን እንጂ እውነትን ይዛ የተነሳችው ሀገራችን የግድቡን ግንባታ ሳታቋርጥ ቀጥላለች:: በአሁኑ ወቅትም የማጠናቀቂያው ምዕራፍ ላይ ይገኛል::
የግድቡ መጠናቀቅ ከኃይል አቅርቦት ባሻገር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪና የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን አባል ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዕውን መሆን ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታው እና ማኅበራዊ አበርክቶው የጎላ እንደሆነ ያብራራሉ። የሕዳሴውን ግድብ ከዚህ ደረጃ ለማድረስም “በአጠቃላይ የተሠራው ተግባር በመላው ዓለም የሚያስከብር ነው፤ የምንከብርበትም የምንከበርበትም ተግባር ነው” ብለዋል።
ሁለቱ ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት መጀመራቸው ይታወቃል። ተጨማሪ አምስት ተርባይኖች ደግሞ በዚህ ዓመት ኃይል እንደሚያመነጩ ይጠበቃል። ይህ ስኬት ታዲያ “የአንድነታችን፣ የትብብራችን፣… የአሸናፊነታችን ምሥጢር መሆኑን ያረጋገጠ ነው” ብለዋል ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ።
“ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት አንድ በመሆን የቅርብ እና የሩቅ ባላንጣዎችን ያሸነፍንበት ብሔራዊ ፕሮክጀት ነው” ሲሉም አክለዋል።
በዓለም ረጅሙ ወንዝ ዓባይ (ናይል) የስልጣኔ ምንጭ ነው። ይሁን እንጂ መዳረሻውን እንጂ መነሻውን አልጠቀመም። ይህ እንጉርጉሮ ታዲያ ታሪክ ሊሆን ጊዜው ደርሷል። ዓባይ ወንዝ ግንድ ይዞ በመዞር ማደሪያ ማጣቱ በቅቶት በእናቱ ቤት ኢትዮጵያዊያንን የሚክስበት ዋዜማ ላይ ደርሰናል። ለአብነትም ሁለቱ ተርባይኖች ኃይል በማመንጨት ውጤት መስጠት ጀምረዋል።
በዓባይ ተፋሰስ ከሚካተቱ ሀገራት ግብፅ 66 በመቶውን፣ ሱዳን 22 በመቶውን የዓባይን ውኃ በብቸኝነት ይጠቀማሉ። የ85 በመቶ ባለድርሻዋ ኢትዮጵያ ግን ተጠቃሚነቷ ምንም ነበር። ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ደግሞ ይህን ታሪክ የቀየረ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን አሻራቸውን ያሳረፉበት ፕሮጀክት ነው።
በ187ሺ 400 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ግድቡ 74 ቢሊዮን ኪውቢክ ሜትር ውሃ ይይዛል። በአራት ዙር ሙሌቱ 40 ቢልዮን ውሃ ተሞልቷል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ 6450 ሜጋዋት ኃይል ማምረት የሚችል ሲሆን፣ ከግድቡ የሚገኘውን ኃይል ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ከማዋል ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት በመሸጥ በዓመት እስከ 580 ሚሊዮን ዶላር (34 ቢሊዮን ብር ገደማ) ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ታዲያ ኬንያን ጨምሮ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር የኃይል ሽያጭ ስምምነት ፈጽመዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ ግንባታው መጀመሩ ይታወሳል።
(መሰረት ቸኮል)
በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም