“ቴያትር እና ፊልም የነፍስ ጥሪ ባላቸው ሰዎች ነው መሠራት ያለባቸው”

0
263

በክፍል አንድ ጽሑፋችን ከተዋናይ፣ ደራሲ፣ አዘጋጅ እና የመድረክ መሪ ከሆነው ታጠቅ ለገሰ (ታጁ) ጋር ቆይታ አድርገናል:: በዝግጅታችን ስለ ልጅነት ጊዜው፣ ወደ ትወና የገባበትን አጋጣሚ እና ቀደምት ሥራዎቹን በተመለከተ አስቃኝተናችኋል:: ቀጣዩን እና የመጨረሻውን ክፍል እንደሚከተለው አቅርበነዋል::

መልካም ንባብ!

የፊልም እና የቲያትር ጥበብ በሀገራችን ያለበትን ደረጃ እና ተቀባይነት እንዴት ታየዋለህ?

ቲያትር በዐፄ ምኒልክ ዘመን ነው የተጀመረው፤ በመስኩም ከፀጋዬ ገብረ መድህን አሁን እስካሉት እነ ውድነህ ክፍሌ ድረስ ጥሩ ጥሩ ደራሲዎች ወጥተዋል:: ሌሎች ትልልቅ ተዋንያን ማለትም እንደነ ወጋየሁ ንጋቱ፣ ተክሌ ደስታ፣ አለማየሁ ታደሰ እና ሌሎች የወጡበትም ነው:: ቲያትር ላይ ፍላጎት፣ ችሎታ እና ፍቅር ኖሯቸው ጥቅም ሳይፈልጉ የሚሠሩ ሰዎች ነው የነበሩት፤ እነዚህ ሰዎች ዋጋ ከፍለው ቲያትርን አሳድገውታል:: ከዚህ ባሻገር ከስንት አንዴ እንኳ ለሚወጡ ጥሩ ፊልሞች ቲያትር የገራቸው (ያስተማራቸው) ተዋንያን አስተዋጽኦ የጎላ ነው::

የፊልም ኢንዱስትሪውን ስንመለከት በቂ እውቀት እና ሀብት ሳይኖር የተወሰኑ ሰዎች በፍላጎት ይሄ ቢሆን ብለው የጀመሩት እንደሆነ ይሰማኛል:: ከዚያ በኋላ ግን ነጋዴዎች ተረከቡት፤ በዘርፉ የተሰማራ ሰው ለፊልም ጥበብ ፍቅር፣ ፍላጎት እና እውቀት ከሌለው ወሳኝ ስለሆኑት ስለትወናው፣ የፊልሙ ሴራ መርቀቅ፣ ጠንካራ መልዕክት ማስተላለፍ፣ የሀገር ገጽታ ማስተዋወቅ፣ የባሕል እድገት፣ የሀገር ልማት እና ሌሎች የሚጨነቅበት ነገር አይኖርም:: ነጋዴው ከሙያው ይልቅ ወደ ገንዘብ መሰብሰብ ያዘነብላል፤ በተግባርም የታየው ይሄው ነው::

ፊልማችንም እድገት ማሳየት ተስኖት ቁልቁል ወርዷል:: ይሄ አልበቃ ብሎ ሰውን በማስነፍ ወደ ቲያትር ቤት ገብቶ እንዳያይ አስተዋጽኦ አድርጓል:: በእርግጥ አሁን አሁን ነገሮች እየተቀያየሩ ነው:: ተመልካቹ አንድ ዓይነት ታሪክ በተለያዩ ፊልሞች እና ተዋንያን ማየት ሲሰለቸው ፊቱን ወደ ቲያትር እያዞረ ነው::

ባለሙያዎች ወደ ዘርፉ መግባት አለባቸው፤ ጽሑፍ መረጣ፣ ተዋናይ መረጣ እና ሌሎች በእነዚሁ ባለሙያዎች መሆን አለበት:: ቆንጆ ወንድ ወይም ሴት ብቻ ተመርጠው አስቂኝ ይዘት ያለው (ያውም የእውነት እንኳ የሚያስቅ አይሆንም) ፊልም እየሠሩ መነገድ መቆም አለበት:: አንድን ሰው በተለያዩ ፊልሞች አንድ ገጸ ባሕርይ መስጠት መቆም አለበት፤ ለምሳሌ አንድ ሰው ሰባት ፊልም ላይ ዶክተር ሆኖ ሊሠራ ይችላል፤ ሰውየውም ረስቶት በእውነተኛው ዓለም ዶክተር የሆነ ሊመስለው ሁሉ ይችላል (ሳቅ)፤ ቲያትር እና ፊልም የነፍስ ጥሪ ባላቸው ሰዎች ነው መሠራት ያለበት፤ በተጨማሪ የፊልም ጥበባችን ከችግር ወጥቶ እድገት እንዲያሳይ መንግሥት ድጋፍ ማድረግ አለበት::

ቲያትር እንደፊቱ ቢቻል በሳምንት አሊያ በሁለት ሳምንት አንድ ጊዜ በመድረኮች እንዲታይ ምን የታሰበ ነገር አለ?

ይህ የብዙ ሰው ጥማት ነው፤ ቢያንስ እሁድ ከሰዓት በኋላን አዳራሽ ገብቶ ቲያትር ዓይቶ ለመውጣት የሚመኘው ሰው ብዙ ነው:: ይህን ለማሳካት ስልጠናዎችን መጨመር እና ተዋንያንን ማበራከት ያስፈልጋል:: በፊት በተወለድኩባት ደሴ ከተማ ውስጥ ስድስት ክበቦች ነበሩ:: ስድስቱም ክበቦች በወሎ ባሕል አምባ ቲያትር ለማሳየት ከፍተኛ ፉክክር ያደርጉ ነበር:: የሚቀርቡት ቲያትሮች ደግሞ የይድረስ ድረስ የሚሰሩ አልነበሩም፤ ጥበብ፣ እውቀት እና ክህሎት የተጨመረባቸው ናቸው:: ለዚህ ደግሞ ባለሙያዎቹ በበርካታ ስልጠናዎች ማለፋቸው ያበረከተላቸው ጸጋ ነው::

አሁንም ደግሞ እንደኔ ያሉ ሌሎች ተዋንያን ስልጠናዎችን እያመቻቹ፤ ክበቦች እየመሰረቱ ብቁ ልጆችን በብዛት ማፍራት ከተቻለ አይደለም በሳምንት አንዴ ከዛ በላይ ቀናት ቲያትሮችን አዘጋጅቶ ለታዳሚ ማድረስ ይቻላል:: እኔም በበኩሌ ቀደም ሲል ያሰለጠንኳቸውን እና ወደ ፊት የማሰለጥናቸውን ሰብሰብ አድርጌ ቡድኖችን በመክፈል ለማሰራት አስቤያለሁ:: ለምሳሌ አራት ትልልቅ ቡድኖች ቢኖሩ እና 25 ሰዎች በእያንዳንዱ ቡድን ስር ቢገቡ፤ አንድ ወር ሙሉ እሁድ እሁድ አራት ቲያትሮችን ማቅረብ ይቻላል ማለት ነው፤ ይህን አስቤያለሁ፤ የቲያትር ጥማት ያለው ሰው ብዙ ነው፤ ስለዚህ ሰው ይረዳኛል ይሳካልኛል ብየ አስባለሁ::

ጥበብ ሰላምን፣ አንድነትን እና እድገትን ከማምጣት አንጻር ያለውን ፋይዳ በፊት ከነበረው ተሞክሮ ጋር አያይዘህ ንገረን?

አንድ የተባበሩት መንግሥታት በሰጠው ስልጠና ላይ ተሳታፊ በነበርኩበት ጊዜ እንደተረዳሁት ማንኛውም የሰለጠነ ሀገር ያደገው ጥበብን ድጋፍ አድርጎ ነው:: ጥበብን ለአንድነት፣ ሀገርን እና ገጽታዋን ለማስተዋወቅ፣ ኢኮኖሚውን ለመደገፍ እና ለሌሎች የተለያዩ ጉዳዮች ያውሉታል:: ስለዚህ ጥበብ እና ሀገር አብረው ይሄዳሉ::

በእኛ ሀገር በቀደሙት ጊዜያት ለጥበብ ጥሩ ግምት ይሰጥ ነበር፤ ለምሳሌ በዐፄ ምኒልክ ዘመን “ፋቡላ” የሚባል አሊጎሪያዊ (እንስሳ ገጸ ባህሪያትን እንደ ሰው የሚጠቀም) ቲያትር ቀርቦ ነበር፤ ንጉሡም ታድመውታል፤ ቲያትሩ በሾርኔ እስዎን የሚነካ ነው ብለው አማካሪዎቻቸው ሲነግሯቸው “ተዋቸው ልጆቻቸው ሌላ የተሻለ ይሰራሉ” ብለው አልፈውታል፤ በዐፄ ኀይለ ሥላሴ ዘመንም ቲያትር ቤቶች፣ መሰልጠኛዎች እና ሌሎች የጥበብ ማዕከላት ታንጸዋል:: በደርግ ጊዜም ከፍተኛ እንቅስቃሴ ነበር፤ አሁን ያለው ትልቁ አሻራ እንዳውም በዛን ጊዜ የተሠራ ነው:: የምናያቸው ጥሩ ጥሩ ተዋንያን እና ድምጻዊያን በዛን ጊዜ የተኮተኮቱ ናቸው፤ ምክንያቱም በቀበሌ፣ ከፍተኛ፣ ወረዳ፣ አውራጃ እና ክፍለ ሀገር  ደረጃዎች ኪነት ቡድኖች ነበሩ:: ለቀደሙት መንግሥታት እንደየ ደረጃው ሕዝቡን አንድ አድርጎ ለማስተዳደር አግዟቸዋል:: ለምሳሌ ስለ አብዮቱ በሙዚቃ እና በተለያዩ የጥበብ ሥራዎች ወደ ሕዝቡ ማስረጽ ተችሏል:: አንድ ዘመቻ ከመጀመሩ በፊት በኪነት ማነቃቂያ እና ግንዛቤ ፈጠራ ይካሄድ ነበር::

ከዚያ በኋላ የመጣው መንግሥት ልማታዊ ሲባል ይሰማል፤ ልማቱ በምን ይታገዛል ለሚለው ትኩረት የለም፤ ጥበቡንም ረስተውታል:: በአንድ የጥበብ ሰው ለሚሊዮኖች መድረስ ይቻላል፤ ያውም ከተቀባይነት ጋር:: ከዚህ ባሻገር ሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን በጥበብ ማስረጽ እና አንድነትን ማጎልበት ይቻላል::

ወደ ታጁ አንምጣና ታጁ እንዴት ተሠራ? ገቢህስ ስንት ነበር?

(ሳቅ) ልጆች ሆነን የህንድ ፊልም እናይ ነበር:: ህንድ ፊልም ላይ ደግሞ ራጁ፣ አንጁ፣ ታጁ… የሚሉ ስሞች የተለመዱ ናቸው:: ፊልሙን ዓይተን ስንወጣ በእነዚያ ስሞች እንጠራራለን፤ በዚያው ለኔ ታጁ የሚለው ቅጽል ስም ሆኖ ቀረ:: ከዓመታት በኋላ ነው የፊልሙ ሀሳብ የመጣው፤ አጠቃላይ ሁሉም ነገር ካለቀ በኋላ ታጁ የሚለው ስም አጭር እና በሁሉም ሰው  በቀላሉ የሚታወስ ስለሆነ መጠሪያ አደረኩት፤ ሌላ ምንም የተለየ ታሪክ የለውም፤ አንዳንዱ “ታ” ታጠቅ ነው፤ “ጁ” ምንድን ነው? ብሎ ከመጠሪያ ስሜ ጋር አያይዞ ይጠይቀኛል::

ሥራውም ስሙም ከጠበኩት በላይ ተቀባይነት አግኝቷል:: በመሆኑም ስሙን ሳንቀይር የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራን ነው፤ በቅርቡ የቴሌቪዢን ትዕይንት እንጀምራለን፤ ታጁ በሚለው ርዕስ ማለት ነው፤ ዩቲዩብ እና ቲክ ቶክን ጨምሮ በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾችም አማራጮች ቀርበናል::

ገቢውን በተመለከተ በጣም ብዙ ነው ያገኘሁት፤ ብዙ ኔጋቲቭ ብሮችን አግኝቻለሁ (ሳቅ) ስም ከፍሎኛል፤ በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይ የባሕር ዳር ሕዝብ ተገኝቶ በደንብ አበረታቶኛል፤ ያ ቀጣይነት ላለው ሥራዬ እንደ ስንቅ ነው የሆነኝ፤ ስም እና ዝናው ብዙ ነበር:: ኢቢኤስ ቴሌቪዢን በተደጋጋሚ በማስተላለፍም አስተዋውቆኛል፤ ሲዲ ሽያጩ ኮፒ ራይት ችግር ባይኖር ጥሩ ነበር:: የራሴን ሥራ አራብተው “አዲስ አሪፍ ኮሜዲ” ትገዛለህ ይሉኝ ነበር::

አሁን ያለው የቴክኖሎጂ ሁኔታ ጥሩ ነው፤ ካንተ የሚጠበቀው ጠንክረህ ሠርተህ ለተደራሽህ ጥሩ ሥራ በዩቲዩብ፣ ቲክ ቶክ እና ሌሎች አውታሮች ማቅረብ ነው:: ይህ ዓለም አቀፍ እና የሰለጠነ ስርዓት ስለሆነ ጥሩ ውጤት ታገኝበታለህ:: እኔም ልምዴን ተጠቅሜ የበሰለ ሥራ ይዤ መቅረቤን እቀጥላለሁ::

ከጋዜጣችን ጋር ለነበረህ ቆይታ ከልብ እናመሰግናለን!

እኔም በጋዜጣዋ ለተሰጠኝ እድል ምስጋናዬ ከልብ ነው!

(ቢኒያም መስፍን)

በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here