ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት እና ከፍተኛ የዋጋ ንረት ዓለም አቀፋዊ ችግር እየሆነ መምጣቱ ይነገራል፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ከውጭ ለሚያስገቡ ሀገራት የአቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት ግብርናውን ፈታኝ አድርጎታል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሰው ሠራሽ መዳበሪያ ዘግይቶ በመግባት፣ የዋጋ መናርና ፍትሃዊ ስርጭት አለመኖር አርሶ አደሩን ቅሬታ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል። ይህም በአደባባይ ሰልፍ እስከ ማስወጣት የደረሰ ከባድ ተቃውሞን አስነስቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዲያ የተፈጥሮ ማዳበሪያን ማዘጋጀትና መጠቀም ችግሩን ለማስታገስ የተሻለው አማራጭ ነው። ባለሙያዎች እንደሚሉት የተፈጥሮ መዳበሪያን መጠቀም ጤናማና ለምነቱ የተጠበቀ አፈር እንዲኖር ያደርጋል፤ ይህም የግብርናውን ምርታማነት ለማሻሻል ድርሻው የጎላ ነው።
የተፈጥሮ ማዳበሪያ ምርታማነትን ከማሳደጉ ባሻገር የኬሚካል የአፈር ማዳበሪያ በአፈር ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በመከላከል አፈርን በማከም ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ በተጨማሪም ለሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ የሚወጣውን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪን በከፍተኛ መጠን እንዲቀንስ ያደርጋል። በተመሳሳይ በተለይ በአሁኑ ወቅት በተዳጋጋሚ የሚከሰተውን የሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ለማስቀረት የተሻለው አማራጭ ይሆናል።
የአፈር ለምነትን ለማስጠበቅ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል የተፈጥሮ መዳበሪያ ወይም ኮምፖስት ማዘጋጀት ዋነኛው ዘዴ ነው፡። ለዚህ ደግሞ በግብርና ሥራ የተሰማሩ አርሶ አደሮች ስለ ተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘገጃጀት ግንዛቤ መፍጠር ቁልፍ ተግባር መሆኑን ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት።
ከአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ በተያዘው የምርት ዘመን ስምንት ሚሊዮን ያህል ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ ወደ ተግባር ሥራ ተገብቷል። ከዚህ ባሻገር አርሶ አደሩ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያን በማዘጋጀት እንዲጠቀም አሳስቧል። ለዚህም ድጋፍና ክትትል እያደረኩ ነው ብሏል።
ይሁን እንጂ ክልሉ በግጭት ውስጥ መገኘቱ በሥራው ላይ ችግር ደቅኗል። ችግሩ እንዳለ ሆኖ ታዲያ የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ እጥረትን በራስ አቅም ለመፍታት አርሶ አደሮች የተፈጥሮ ማዳበሪያን እያዘጋጁ መሆኑን አስተያየታቸውን ለበኩር የሰጡ አርሶ አደሮች ተናግረዋል።
ከእነዚህም መካከል “ከአፈር ማዳበሪያ በተጨማሪ ማሳን በድግግሞሽ ማረስና ማለስለስ ምርታማነታችንን ያሳድገዋል” ያሉን አርሶ አደር አደራው አበበ አንዱ ናቸው። በምሥራቅ ጎጃም ዞን ቢቡኝ ወረዳ የደብረ ዘይት ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር እንደነገሩን የተፈጥሮ ማዳበሪያን ወይም ኮምፖስት መጠቀም ከጀመሩ ከሰባት ዓመት በላይ ሆኗቸዋል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያን መጠቀማቸው ለሰው ሠራሽ ማዳበሪያ የሚያወጡትን ወጪ ከመቀነስ ባሻገር የመሬቱ ለምነት እንዲጠበቅና የተሻለ ምርት እንዲያገኙ እንደረዳቸው ለበኩር ተናግረዋል። አርሶ አደሩ የሰብል ምርታቸውን ለማሳደግ ማሳቸውን ደጋግመው በማረስ የተፈጥሮ ማዳበሪያንም በመጨመር ድንች ዘርተዋል። ቀሪ ማሳቸውን (ግማሽ ሄክታር) ላይ የበቆሎ ዘርን የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጨመር ለመዝራት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀም የተሻለ ምርት እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው አቶ አደራው ተናግረዋል። በቀጣይም በጓሯቸው የሚገኙ ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም ኮምፖስት (የተፈጠሮ ማዳበሪያ) በማዘጋጀት እንደሚያመርቱ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
አርሶ አደሩ አክለውም በግብርና ባለሙያዎች አማካኝነት ሙያዊ ድጋፍ (በዋናነት ግንዛቤ ፈጠራ) እንደተደረገላቸው ተናግረዋል። ይህም ለውጤት እንዳበቃቸው ነው የገለጹት። “ባለፈው ዓመት የአፈር ማዳበሪያ ዘግይቶ ነው የገባው- እጥረትም ነበር። በዚህም በጣም ተቸግረን ነበር። በመሆኑም የተፈጥሮ ማዳበሪያን ማዘጋጀት ግድ ይላል” ብለዋል።
ሌላው መሬታቸውን በወቅቱ በማረስ ለዘር ያዘጋጁት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ቢቡኝ ወረዳ ገናምሳ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቀረዓለም ታሪኩ ናቸው። እርሳቸውም የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማዘጋጀት ምርታቸውን ለማሳደግ ተግተው እየሠሩ መሆኑን ነግረውናል። ከሰው ሠራሽ ማዳበሪያ በተጨማሪ የተሻለ ምርት ለማግኘትና የአፈሩን ጤንነት ለመጠበቅ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት ሰብላቸውን ይዘራሉ።
ከዚህ ቀደም የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀማቸው የተሻለ ምርት እንዳገኙ የሚናገሩት አርሶ አደሩ፣ ኮምፖስት ለአምስት ዓመታት ያህል ተጠቅመዋል። የተፈጥሮ ማዳበሪያ የአፈር ለምነቱን ከሁለት ዓመት በላይ ጠብቆ በመቆየት ጉልህ ሚና ይጫወታልም ብለዋል።
ለበቆሎ፣ ለስንዴና ለድንች ዘር ኮምፖስት እንደሚጠቀሙ የነገሩን አርሶ አደሩ፣ ዋጋው እየናረ የመጣውንና እጥረት እየገጠመ ያለውን ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ በተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማካካስ እየሠሩ ይገኛሉ።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ አስላከ የአፈር ለምነትን ለመጠበቅና ምርታማነትን ለማሳደግ ተያለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ይናገራሉ። በክልሉ ለ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት የመኸር እርሻ ጥቅም ላይ የሚውል ከ102 ሚሊዮን 31 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማዘጋጀት አቅዶ ወደ ሥራ መግባቱን ገለጸዋል። ክንውኑም 50 ነጥብ አራት በመቶ (መረጃውን እስካጠናቀርንበት መጋቢት 12 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ መሆኑን ልብ ይሏል) ነው ብለዋል። በሥራውም ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ አርሶ አደር መሳተፉን ተናግረዋል።
ዶክተር ማንደፍሮ አክለውም ከ265 ሺህ በላይ ኩንታል በርሚ ኮምፖስት ለማምረት ታቅዶ እስካሁን ከ181 ሺህ በላይ ኩንታል ተዘጋጅቷል ብለዋል። በተጨማሪም ከ292 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ ባዮሳላሪ ለማዘጋጀት ታቅዶ 69 ሺህ ኪዩብ ያህሉን ማከናወን መቻሉን ጠቁመዋል።
እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግና በውጤት ለማጠናቀቅ የባለፈውን ዓመት የእቅድ ክንውን ታሳቢ መደረጉን አብራርተዋል። የንቅናቄ መድረክ በመፍጠር፣ ለባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት ፈጻሚና አስፈጻሚ አካላት ግንዛቤ እንዲኖራቸው ዝግጅት አድርገው ወደ ሥራ መገባቱንም ገልጸዋል።
አርሶ አደሮች የሚያዘጋጁት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግልና አዋጭ መሆኑን ያስታወሱት ዶክተር ማንደፍሮ፣ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አስገንዝበዋል። ለሥራው ግብዓት የሚሆኑ ተረፈ ምርቶች በአካባቢው በቀላሉ የሚገኙ በመሆናቸው አርሶ አደሩን ለወጭ የማይዳርጉ ናቸው ብለዋል። በቀሪ ጊዚያትም ርብርብ ተደርጎ መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል።
እንደ ባለሙያዉ ማብራሪያ አርሶ አደሩን ያሳተፈ የንቅናቄ መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር። በዚህም የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዴት እንደሚዘጋጅ፣ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውል፣ ያለው ፋይዳ ምንድን ነው የሚሉትን ሐሳቦች በማንሳት ግንዛቤ መፈጠሩን አብራርተዋል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያን የአርሶ አደሩን ወጪ የሚቆጥብ፣ ለጤና ተስማሚ፣ ለአካባቢው ስነ-ምህዳር ተስማሚ፣ የአፈር ለምነትን ለረጅም ጊዜ የሚጠብቅ እና በቀላሉ የሚተገበር በመሆኑ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት አስረድተዋል።
(መልካሙ ከፋለ)
በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም