የትኩረት ኃይል

0
617

በሕይወታችን ትልቁን ጉዳይ ለመከወን የሚያችለንን “ትኩረት”ን ዛሬ የምናየው ርዕስ ነው። ሀገርኛ ብሂልም አለን። “ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዛፍ ላይ አይወጣም” የሚል። የሰው ልጅ ቀልብ በብዙ ተግባራት እና ድርጊቶች የተበታተነ አንዱን ጉዳይ ለመከወን የሚቸግር ፍጡር ነው። ዘንድሮ ደግሞ የቴክኖሎጂ መስፋፋት ይዞት የመጣው ጣጣ አለ።

ለአንድ ጊዜ አንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ፣ ተግባር ላይ መስራት የስራ ጥራትን በእጅጉ ያሻሽላል። ሦስት አራት ተግባራትን መከወን ግን ምርታማነትን በ40በመቶ ይቀንሳል፤ በ10በመቶ ጭንቀትን ይጨምራል። አንዱን ማንሳት፣ ያንን መጣል፣ ስልክ መደወል፣ ቲክቶክ መመልከት፣ ቪዲዮ ማቀናበር፣ የኢሜል መልእክት ማየት… ሌሎችንም ተግባራት በአንድ ጊዜ መስራት ውጤቱን ደካማ ያደርገዋል። ለዚህም ይመስላል የባንክ ቤት ሒሳብ ከፋዮች ስልክ እንዳያናግሩ ኢንተርኔት እንዳይጠቀሙ ክልከላዎች  የሚደረጉባቸው።

ዳንኤል ጐሊማን በአስፈላጊው ላይ ማተኮር በሚለው መጽሐፍ “የሰው ልጆች ትኩረት ሁልጊዜ  ከመናጠብ ጋር ይታገላል” በሚል ጽፏል። “ስብሰባ ውስጥ ተቀምጨ አዕምሮዬ  ሌላ ቦታ ሄዷል፣ ስመለስ ስብሰባው ውስጥ ያለፈኝን በማሰብ ተገረምሁ” ይላል። “ሁለት ያሳደደ አንድ አያገኝም፣ ሁለት ድስት የጣደች ሴት አንዱንም አታነድም” በሚለው ሀገርኛ ብሂላችን ውስጥ የምናየው ትኩረት ጥንቃቄ እና እንክብካቤ የሚፈልግ ሀብት (አቅም) መሆኑን ነው።

አዕምሯችን ማለቂያ በሌላቸው የአሁን  ሐሳቦች ተይዟል፣ ትዝታዎች ይዘውታል፣ ቀጥሎ በሚደረጉ ሐሳቦች ተጠምዷል።

ክሬስ ባሊይ ሃይፐር ፎከስ በሚል ባዘጋጀው መጽሐፍ ላይ ትኩረትን ወደ አስፈላጊ ነገር መምራት፣ ያንን ትኩረት ባለበት ማስቀጠል በቀን ውሏችን ከሚገጥሙን ውሳኔዎች አንዱ ሆኖ ማንነታችንን ይወስንልናል ብሏል። ሰዎች አራት ተግባራት አሏቸው የሚለው ክሬስ አስፈላጊ ተግባር፣ ዓላማ ተኮር ተግባር፣ አላስፈላጊ ተግባር እና ትኩረት በታኝ ተግባር  በማለት ይከፍላቸዋል። ሁለቱ የሚጠቅምና ውጤታማ የሚያደርጉ ሲሆኑ ሁለቱ ቀሪዎች ደግሞ አጥፊና በታኝ ናቸው።

ዊልያም ጀምስ ትኩረት የምታደርግበትን ነገር ትሆናለህ እንደሚለው፣ ትኩረት ማድረግ በመልካም ነገሮች ላይ ሲሆን አኗኗርን ውጤታማና መልካም ያደርጋል። የሰው ልጅ ትኩረት የሚናጠብበት ሁለት ምክንያቶችን ክሬስ ሲጠቅስ ብዙ ተግባራትን በአንድ ጊዜ መከወን መሞከርን በቅድሚያ  ያስቀምጠዋል።

ቲዋዙ ሚልሰን በቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ የሳይኮሎጂ ምሁር ናቸው። አዕምሯችን 11 ሚሊየን የመረጃ ቢቶችን በየደቂቃው የሚያመነጭ እና የሚልክ ቢሆንም የሰው ልጅ አዕምሮ ግን ተቀብሎ የሚያተኩርባቸው እና የሚያደራጃቸው መረጃዎች 40 ብቻ ናቸው ይላሉ። ሁለተኛው ደግሞ አንድ ነገር ላይ ትኩረት አድርገን ከቆየን በኋላ ማስታወስ የምንችለው በጣም ትንሽም ነው። 40 ነገሮች ብንመለከት ከደቂቃዎች በኋላ የምናስታውሰው አራቱን ነው ይላሉ።

አንዲት ሴት በእግር ዘና በምትልበት የጣና ሐይቅ ዳርቻ በድምጽ የተቀዳ መጽሐፍ በስልክ እየሠማች ነው እንበል። የትኩረት ቦታዋን እንመልከተው።

እየተጓዘች ነው፣ እየሰማች ነው። እየተነፈሰች ነው፣ ማስቲካ እያኘከች ነው።

ይህንን በልምምድ ላታዳብረው ትችላለች። በዚህ ሒደት ትልቁ ጉዳይዋ የመጽሐፉን ትረካ መስማት ነው። ቀጥሎ መጓዝ ነው። በጉዞዋ መንገድ ስታ ወደ ሐይቁ እንዳትገባ፣ ከቆመ እንጨት ጋር እንዳትጋጭ፣ ጐረምሳ ስልኳን እንዳይነጥቃት መጠንቀቅ አለባት። ማስቲካ ማኘክ እና መተንፈስ የትኩረት ቦታን ይሻማሉ።  ብዙ ተግባራትን በአንዴ መስራት  የትኩረት ቦታችንን (Attentional space) በውጥረት ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል። በሒደቱም ጊዜያችን በከንቱ ይባክናል።

አልፎም መስራት የሚገባንን ሌላ ዋና ተግባር ልንረሳ እንችላለን። ከደቂቃዎች በኋላ በድምጽ የተቀዳውን መጽሐፍ ምን ያህል ሰምታዋለች፣ ምን ያህል ታስታውሰዋለች የሚለውን ስንመለከት ውጤቱ የሚያስደስት አይሆንም። የተበታተነ ትኩረት የሥራ ውጤትን ደካማ ያደርጋልና።

ሰዎች ከሌሎች ፍጡራን የሚለየዩት ማሰብ የሚችል አዕምሮ ስለተሰጣቸው ነው።  አዕምሮ ወደ ሚያተኩርበትና ሚያሰላስልበት ጉዳይ ዓለምን የመረዳት መጡኑ በዚያው ያድጋል። ዳንኤል ጉሊማን ትኩረት ልክ እንደ ጡንቻ ነው ይላል፤ በጣም በተሰራበትና በተመራበት መንገድ ጠንካራ ይሆናል። ወደ ስፖርት ቤቶች የሚሄድ ጡንቻዎቹን እንደሚያጠነክር ሁሉ፣ አዕምሮ ማተኮርን በአንድ ነገር ላይ ካልተለማመደ ደካማ ይሆናል በማለት ዳንኤል ጽፏል።

ሃይፐር ፎከስ (አንድን ጉዳይ በልዩ ተመስጦ መከወን) ለሥራችን ውጤታማነት የጎላ ድርሻ አለው። ከዚሁ በተቃርኖ ደግሞ የትኩረት መበታተን (ስካተርድ ፎከስ) የስራ ጉድለትን ያመጣል። ሐሳብ በባህርይው ለምን ተፈጠር ብሎ የሚቆጣጠሩት ባለመሆኑ፣ በልዩ ልዩ ቦታዎች የመበታተን አደጋ ይገጥመዋል። ወዲያ ወዲህ ሲዋልል ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ የጊዜ ምዕራፎች ውስጥ ይበታተናል። ብዙው ትናንት እና ነገ ላይ በመሆኑ ዋናውን ዛሬን በከንቱ  ያባክናል።

በዚህ ዘመን ትኩረታችንን የሚያናጥቡን እና በሐሳብ እንድንባዝን የሚያደርጉን የቴክኖሎጂ  ውጤቶች ብዙ በመሆናቸው፣ ትኩረትን መሰብሰብና በእቅድ ተግባርን መከወን ሲያስቸግር እናያለን። ሰው ሥራውን ትቶ በቴክኖሎጂ እና በሌሎች ድርጊቶች ተጠልፎ ጊዜው ያልፋል። በግል አኗኗራችንም ኢንተርኔት እና ወሬው ከእቅዳችን ውጪ ያውለናል። ሰዎች፣ የስልክ ጥሪ፣ ስብሰባ፣ ዜናዎች፣ ጨዋታዎች፣ ወሬዎች፣ ፌስቡክ፣ ቲክቶክ፣ ዩቱዩብ፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ ፊልሞች፣ ልጆች፣ ጎረቤቶቻችን እና ሌሎችም ትኩረታችንን ይበትኑታል።

ዳሪየስ ፎረክስ “የሰው ልጅ ካልፈቀደ በቀር አንድም ትኩረቱን የሚሰርቀው ነገር ሥልጣን የለውም” ይላል  ጀስት ዱ ኢት ቱዴይ  በሚለው መጽሐፉ። አንድ ነገር ላይ ትኩረት ሳታደርግ ተዘናግተህ በተቀመጥህ ቁጥር አዕምሮህን እንዲበተን እየፈቀድህለት ነው ይላል።  “በአሉባልታ ወሬ ሕይወትህ አይቀየርም፤ 439 ጊዜ ኢንስታግራም በመመልከት፣ 49 የዩቱዩብ ቪዲዮ በማየት፣ አሉታዊ ሰበር ዜናዎችን በማንበብ አትለወጥም” የሚለው ዳሪየስ ሁለት ነገሮችን በመከወን ትኩረቴ ለማስተካከል ሠርቻለሁ ይላል።

የመጀመሪያው በትኩረታችን እና መንገዳችን ላይ የሚደቀኑብንን፤ በፈለጉት መስመር ሊነዱን የሚፈልጉ ሐሳቦችን እና ተግባራትን መተው ነው ይላል። ሲያብራራም  “አንዳንድ ወዳጆቼ ዩቱዩብ እንድሰራ በተደጋጋሚ ይመክሩኝ ነበር። የሰዎችን ሐሳብ በማድመጥ ለስድስት ወራት በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ በቀረጻ ሥራዎች ራሴን አዘጋጅቼ ዩቱዩብ መስራት ጀመርሁ። ስራዎቼ ጥሩ ምላሽ አገኙ።

የእኔ ዋናው ሥራዬ የነበረው መጽሐፍትን እና ጋዜጦችን ማዘጋጀት፣ ስልጠናዎችን መስጠት በመሆኑ  ዩቱዩብ ትኩረቴን ሰረቀው። መሰላቸትም ውስጥ ገባሁ። በኋላም ራሴን ጠይቄ መተው ያለብኝ አንድ ነገርን ስፈልግ ዩቱዩብ መስራት ነበር ሆኖ ያገኘሁት፤ እናም ተውሁት” ሲል  ልምዱን  ጽፏል። ለዓመታት የሰበሰብናቸው ሐሳቦች፣ ፕሮጀክቶች፣ ሥራዎች፣ ሰዎች እና ትውስታዎችን ከሕይወት ማስወጣት ጥርት ላለ ትኩረት ያግዛል ሲል ይመክራል።

ሁለተኛው የዳሪየስ ምክር ሰዎች ከዚህ ቀደም ስለ ከወኑት ስኬታቸው በማሰብ ለዛሬ ጉልበት አድርገው ይጠቀሙበት የሚል ነው።  “ስለ ስኬታችሁ ስታስቡ ሶሮቶኒን  የተባለው ሆርሞን በሰውነታችሁ ውስጥ ይመነጫል፣ ይህ ሆርሞን ደግሞ ትኩረትን መልሶ የማስተካከል አቅም አለው” ይላል በመጽሐፉ።

ዘመናዊው አኗኗር ውሎና አዳራችንን ከኢንተርኔት ጋር አድርጎታል። ዓለምን በእጅ ስልካችን ይዘን እንዞራለን። በቴክኖሎጂው የሚጠቀሙ ብዙዎች የመኖራቸውን ያህል ፤ቴክኖሎጂው የሚጠቀምባቸውም ብዙ ናቸው ይላል ዳሪየስ። የቴሌቪዥን ዝግጅቶች፣ ጨዋታዎች፣ ማስታወቂያዎች፣ መጣጥፎች እና ሌሎችም የሰዎችን ትኩረት ለማግኘት  በጥናት ተመስርተው ይዘጋጃሉ። ሳንፈልግ፣ በውል ሳንረዳው በሳምንት ውስጥ  በርካታ ሰዓታትን እነዚህን ዝግጅቶች በማየት ጊዜያችንን እናባክናለን። ትኩረታችን የትም ተበትኗል፣ ነገር ግን በሚገባው እና በሚጠቅመው አይደለም። “ሁሉም ቦታ መሆን የትም መሆን አይደለም” የሚለው ጸሐፊው ሕይወትን በማይለውጡ ተግባራት የትኩረት መቃወስ ለጭንቀት፣ ለጊዜ ብክነትና ለድብርት መጋለጥ ምክንያት ነህ በጥናት ተረጋግጧል።

ለስራችን ግዴታ እስካልሆነ ድረስ የኢንተርኔት ግንኙነትን ከስልክ ማጥፋት፣ ስልክን አርቆ ማስቀመጥ ትኩረትን ለመሰብሰብ የሚያግዙ አማራጮች ተደርገው ይወሰዳሉ። ይህ ካልሆነ ግን በየ ደቂቃው ትኩረታችንን ጠልፈው የሚበትኑ መልእክቶችን ለማየት እንናጠባለን።

የሰው ልጅ አዕምሮ አንድ ተግባር ላይ ከ30 ደቂቃ በላይ አተኩሮ መቆየት አይችልም፤ ለዚህም አምስት ደቂቃ እረፍት በየ 30  ደቂቃው ማድረግ ይመከራል። በእረፍቱም ጊዜ ቢሮ ውስጥ መጓጓዝ፣ ሰውነት ማፍታታት፣  ቡና የመጠጣት ተግባራት ቢከወኑ አዕምሮ እረፍት ወስዶ ሲመለስ የበለጠ ትኩረት ያደርጋል። ሌሎች የቅርብ ጊዜ ጥናቶችም የሰው ልጅ የትኩረት ማድረጊያ ቆይታ 20 ደቂቃዎች ስለመሆኑ ይናገራሉ።

ዳሪየስ በሕይወቴ ስኬታማ የሆንሁት የትኩረት መስመሬን በማጥበቤ ነው ይላል። ስኬት  የአንድ ቀን ሳይሆን የዓመታት ጉዞ ድምር ውጤት እና የሒደቶች ጥርቅም ነው ይላል። ለዚህም ምሳሌ ቢሊየነሩን ዋረን ብፌትን ያነሳል። ይህ ባለጸጋ ከ32 እስከ 44 ዓመቱ ድረስ የተጣራ ሀብቱ በ1257 በመቶ እያደገ ነበር። ከ44 እስከ 56 ዓመቱ ደግሞ ሀብቱ በ7268 በመቶ በማደግ ላይ ነበር። ዋረን ብፌት 99 በመቶ የሚሆነውን ሀብቱን ያፈራው ከ50 ዓመታት በኋላ ነበር።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here