ሶፍ ኡመር በባሌ ተራሮች ላይ የሚገኝ ተፈጥሯዊ ዋሻ ነው፡፡ በ1972 እ.አ.አ በተደረገ አሰሳ በወይብ ወንዝ 15 ኪሎ ሜትር ርዝመት ውስጥ ለውስጥ የተቦረቦረ ድንቅ ተፈጥሯዊ ዋሻ መሆኑን ድረ ገፆች አስነብበዋል፡፡
የወይብ ወንዝ ከባሌ አራት ሺህ ሜትር ከፍታ ካለቸው ተራሮች ቁልቁል አንድ ሺህ ሜትር ወርዶ ወደ ቀኝ በመታጠፍ ሶፍ ኡመር ዋሻ ውስጥ ይገባል፡፡ በዋሻው ውስጥም 15 ኪሎ ሜትር ውስጥ ለውስጥ ግራና ቀኝ ግድግዳዎቹን እየጠረበ እስከ 20 ሜትር ቁመት ያላቸው ምሰሶዎች ጣሪያውን የተሸከሙ አስመስሎ አቁሟቸዋል-የወይብ ወንዝ፡፡
ሶፍ ኡመር ዋሻ ለአካባቢው ነዋሪዎች በአምልኮ ቦታነትም አገልግሏል፡፡ ከዋናው 15 ኪሎ ሜትር ከሚረዝመው ከምስራቅ ወደ ምዕራብ ከተቦረቦረው ዋሻ ግራና ቀኝ የሚታጠፉ በርካታ አነስተኛ ዋሻዎችንም ይዟል፡፡
በዋሻው ጣሪያ እና ግድግዳ የተንጠለጠሉ የለሊት ወፎች ይታዩበታል፡፡ የተለያዩ የሸረሪት እና የእባብ ዝርያዎችም ይገኙበታል፡፡ የዋሻው ውስጥ ግድግዳዎች ጥንታዊ ስዕሎች እና ቅርፃችንም ይዘዋል፡፡ በውስጡ በሚያልፈው ወንዝ በጐርጓዳ ስፍራዎች አልፎ አልፎ ውሀው አቁቶ ኩሬዎችን ፈጥሯል፡፡
ለተፈጥሯዊ ዋሻ መጠሪያ ስም “Sof” ቀዝቃዛ “Omar” ወተት ከሚል መነሻ መሆኑ ነው በድረ ገፆች በሰፈረው ጽሑፍ የተጠቆመው፡፡
የሶፍ ኡመር ዋሻ በአፍሪካ በወንዝ ውስጥ ለውስጥ የተቦረቦረ ረዥም እና ጥንታዊ ተፈጥሯዊ ዋሻ ነው፡፡ በዙሪያው የሚገኘው ሥነ ምህዳር በቀጣይ በሥነ ምድር አጥኚዎች ሊፈተሽ የሚጋብ ድንቅ ቦታ ነው፡፡
ሶፍ ኡመር ዋሻ ሳቢ፣ ዘመን አመጣሽ ሰው ሰራሽ እንከኖች ያላጠሉበት ወይም ያላደበዘዙት የጉብኝት መዳረሻ ስለመሆኑ በተለያዩ ጊዜያት ለምርምር ወደ አካባቢው ያቀኑ ምሁራን እማኝነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በመረጃ ምንጭነት ኬክ ኬቭ፣ አዋዝቱር እና ዊኪፒዲያ ድረ ገፆችን ተጠቅመናል፡፡
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም