ባቡር ላይ ዓመት ከስድስት ወር

0
185

የ17 ዓመቱ ታዳጊ የወላጆቹን መኖሪያ ቤት ለቆ ባቡር ላይ ውሎ እያደረ ከ18 ወራት ለበለጠ ጊዜ በመጓጓዝ እያሳለፈ መሆኑን ኦዲቴ ሴንትራል ድረ ገጽ ለንባብ አብቅቶታል::

ታዳጊው ላስ ስቶሊ ወላጆቹን አሳምኖ በ17 ዓመቱ ከመኖሪያ ቤቱ ወጥቶ በባቡር መጓጓዝ የሚያስችለውን የቅናሽ ትኬት በአስር ሺህ ዩሮ መግዛቱ ተገልጿል::በዚህም በየትኛውም አቅጣጫ ሂያጅና ተመላሽ ባቡር ላይ ውሎ እያደረ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ቁሶችን በአንድ የጀርባ ቦርሳው አዝሎ ነው መጓጓዝ የጀመረው::

ላስ ስቶሊ የመጀመሪያዎቹ ወራት  ለጉዞው እጅግ አስቸጋሪ እንደነበሩ ነው የተናገረው:: ሁሉም ነገር እሱ  ባቀደው መልኩ አልጋ በአልጋ ሆኖ አለመፈፀሙ ግር አሰኝቶት እንደነበርም አመላክቷል::የዘመነ “ዘላን” አኗኗርን መላመድ ቸግሮት እንደነበር የተናገረው ላስ ስቶሊ ባቡር ላይ ውሎ ባቡር ላይ ማደር፣ ባቡር በሚቆምበት ጣቢያ ፈጥኖ ምግብ መብላት እና ለቀጣይ ጉዞ መዘጋጀት ፈታኝ ሆኖበት እንደነበር ጠቁሟል::

ለመኖር በጣም አስፈላጊ የሆኑ ጥቂት ቁስ መገልገልን ማረጋገጥ ዓላማው አድረጐ ለተነሳው ታዳጊ በቦርሳው የያዘው ላብቶፕ እና የጆሮ ማዳመጫው ብቻ ነበሩ ዋነኛ መገልገያዎቹ::በቀን 600 ማይል  ወይም ከዘጠኝ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ እየተጓዘ ከወላጆቹ መኖሪያ ወጥቶ ጽሑፉ እስከተስተናገደበት ጊዜ ድረስ 300 ሺህ ማይል ተጓጉዟል::

ላስ ስቶሊ በላብቶፑ በማይገለገልበት ጊዜ አንደኛ ማዕረግ ወይም የፊተኛውን የባቡር ክፍል ለቆ ወደ ተጐታቾቹ በመሻገር  ዘና እንደሚል ነው የተናገረው::

በተጓጓዘባቸው የባቡር መስመሮች ባቡሩ በሚቆምባቸው ጣቢያዎች በሚገኙ ምግብ ቤቶች ያገኘውን ቀማምሶ ቀለል አድርጐ መኖር እንደሚቻልም አረጋግጧል::ጥቂት ልብሶቹን ለማጠብም ሆነ ገላውን ለመታጠብ በባቡር መቆሚያ ጣቢያዎች የጋራ መገልገያዎችን መጋራት ፈታኙ የጉዞው አካል እንደነበር አጋርቷል::

ባቡር ላይ ውሎ እያደሩ መኖር ቀላል አለመሆኑን የተናገረው ታዳጊው በቅናሽ ዋጋ የገዛው የጉዞ ትኬቱ ገና ቀጣይ ስድስት ወራትን በባቡር መጓጓዝ የሚያስችለው በመሆኑ እንደገፋበትም ነው ጽሑፉ ያስነበበው::

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here