“ሳያሽ የበላ ዝንጀሮ ሲስል ያድራል”

0
466

ስነ ቃል ከህብረተሰብ ኑሮ ጋር እጅግ የተሳሰረ ነው። በሠርግ፣ በጦርነት፣ በፍቅርና ጥላቻ፣ በኃዘን በደስታ፣ በዕለት ኑሯቸው፣ በአደን፣በከብት ጥበቃ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና መንፈሳዊ ጉዳዮችን ለማንሣት ጥቅም  ላይ ይውላል።

ስነ ቃል ዓይነቱና መልኩ ብዙ ነው። አፈ ታሪኮች፣ ቀልዶች፣ ተረቶች፣ እንቆቅልሾች፣ ምሳሌያዊ ንግግሮች፤ የሥራ፣ የፍቅር የለቅሶ፣ የልመናና ጀግንነት ግጥሞች እና የጨዋታ ግጥሞችን ያካትታል። ስነ ቃል ማህበራዊ ቅርስ ነው። ለመኖር መሠረት፣ ለዕድገት ምክንያት፣ ለስርጭቱ ብቃት እንዲኖረው ማሟላት ያለበትን ጉዳዮች “የአማርኛ ምሳሌያዊ ንግግሮች” በሚል የኢትዮጵያን ቋንቋዎች አካዳሚ ባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር በ1982 ያሳተመው መጽሐፍ አስፍሯል።

አንደኛው ጉዳይ ምክንያት እና አጋጣሚ ነው። ለፉከራ ግጥሞች መደርደር የጀግንነት ተግባር፣ ለሠርግ ግጥሞች የሠርግ ዝግጅት ተረት ተረት ለማለትም ሁኔታው እና አጋጣሚው ተሟልቶ መገኘት አለበት።

የሚከወኑት አካላት መኖር ደግሞ ለስነ ቃል መገኘት እና መከወን ሁለተኛ አስፈላጊ ጉዳዮች ናቸው። “እንቆቅልህ” የሚሉ እና “ምን አውቅልህ” የሚሉ፤ ግጥም አውራጅ እና ተቀባይ መኖራቸው ለስነ ቃል መገኘት ግዴታ ናቸው።

የወል ትውስታ ሦስተኛው ጉዳይ ነው። ስነ ቃል ከጥንት አባቶች የተወረሰና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ፣ የቀደሙትን አባቶች ስርዓትና አኗኗር ያስታውሳል። ጥንታዊ ባህል በስነ ቃል አማካይነት የቆየው በየዘመኑ በነበሩ ክዋኔዎች የማስታወስና የሌላ ስነ ቃል ማፍለቅ ችሎታ መሆኑ እሙን ነው። ለስነ ቃል ህልውና ከከዋኒዎች በተጨማሪ ተደራሲያን መኖራቸው አራተኛ ጉዳይ ነው። ያለ ህብረተሰብ የስነ ቃል ሕልውና አይታሰብም። ስነ ቃል ሲከወን የአድማጭና ተመልካች ትችት አስተያየቶችና ጥቆማዎች የስነ ቃሉን ጥራትና ምሉዕነት ያጠነክሩታል። በመጨረሻ የምናየው ክዋኔ ነው። ተረት በንግግር ክዋኔ ይቀርባል። ዘፈን ይዘፈናል፣ እንቅስቃሴዎች ጭፈራዎችና ውዝዋዜዎች ያደምቁታል።

ከላይ በጠቀስሁት መጽሐፍ ውስጥ ምሳሌያዊ ንግግሮችን በሚመለከት ባህሪያቸው ተዘርዝሮ ቀርቧል። እምቅና ሚስጢራዊነትን በውስጡ ለማስተላለፍ የተለያዩ ስልቶች አሉ። ንጽጽር፣ ግነት፣ ሰውኛነት፣ ምጸት፣ ጥያቄና መልስ፣ ድርጊትና ውጤት፣ ውድድር ከስልቶቹ መካከል ይጠቀሳሉ።

በዛሬው ጽሑፍም ከስነቃል ዓይነቶች አንዱን ምሳሌያዊ አባባሎችን ብቻ መርጠን ሐሳብ እናነሳለን።

በሰውኛ ስልት የቀረበውን አንድ ምሳሌ ላስቀምጥ። “ሺህ ቢታሰብ ያው በግል አለች ድመት” በማለት በሚስጢር አንድ ግለሰብ ሀብትና ጸጋ ቢትረፈረፍ ለእኔ ምኔም አይደለም የሚል የምን አገባኝ ስሜትን  ሲናገር እንመለከታለን። “እኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል አለች አህያ” የሚለውም እንዲሁ አጥፊነትና አባካኝነትን የሚገልጽ ነው። ለሀገር፣ ለትውልድና ለአካባቢ አለማሰብን የሚያትት ነው። በቁጥብ ቃላት በአቋራጭ ሐሳብን መናገሪያም ነሳሌያዊ ንግግር። ሐሳብን ለማጠናከር፣ ለማጉላት፣ ብሶትንና ምሬትን ለመናገር፣ ደስታና ሐዘን፣ ባህሪና አመለካከትን የሚገልጹበት፣ ድጋፍና ነቀፌታን ለማሳየት፣ ለምስጋና እና ተግሳጽን ለማስተላለፍ ጥቅም ላይ  ይውላሉ።

ዳንኤል አበራ የተባሉ ምሁር የአማርኛ ምሳሌያዊ አባባሎች   በሚል 20 ሺህ ምሳሌያዊ አነጋገሮችን በ1998 ዓ.ም አሳትመዋል። አንዳንድ ምሳሌያዊ ንግግሮቻችን የታሪካችን እና የማንነታችንን ገጽታ በአስደማሚ መልኩ ቀርጸውታል ይሉና ዳንኤል አበራ “ሴት በማጀት  ወንድ በችሎት” የሚለውን አባባል ታሪክና እውነት ያስታውሳሉ። ጥሬ ፍቺው በቀደመው ዘመን ሴት መስራት ያለባት፣ የምትሠራው፣ ሙያዋ እና መገኛዋ፣ ማዕድ ቤት፣ ጓዳ ነው የሚል ትርጉም ይሠጡታል።

ሆኖም ልማዳዊው ትርጉሙ ግን ከዚህ የተለየ ስለመሆኑ ያብራራሉ። በባልና ሚስት መካከል ግጭቶች ሲፈጠሩ በገጠሩ አኗኗር የሚገላግል ጎረቤት በቅርበት በማይገኝበት ሁኔታ ሴቷ ወደ ውጪ ከመውጣት ይልቅ ወደ ማጀት (ጓዳዋ) እንድትገባ የሚመክር ነው ይላሉ። ማጀት ከጓዳነት ውጪ የሴት የማይደፈር፣ የማይገሰስ፣ግዛት፣ ክልል ነው። ማጀቱ በር ኖረው አልኖረው፣ ተሸነጎረ፣ ተዘጋ ወንድ ዝር የማይልበት ስፍራ ነው ይላሉ።

ወንድየው እሳት ለብሶ ሊደበድባት ሲመጣ ሴቷ ዘላ ወደ ማጀቱ ትገባለች። ያን ጊዜ ከመሳደብ ባለፈ ወንድ ወደ ጓዳ ገብቶ ሊደበድባት አይችልም። ሴቷ የፈለገችውን ትሰድበዋለች፣ ትረግመዋለች። ግዛቱ የግሏ በመሆኑ ያለ ከልካይ ብስጭቷን  ትወጣበታለች።

በወቅቱ ልማድ ወንድ ልጅ ማጀት ከረገጠ ወንድነቱ ያበቃለታል። ትዳሩም ይበተናል። ማህበረሰባዊ ቦታውንም ያጣል። ሴት በማጀት ወንድ በችሎት የሚለው ሐሳብ መነሻው እንደዚህ ነበር ሲሉ ዳንኤል አበራ ጽፈዋል።

ምሳሌያዊ አባባሎች (ንግግሮች) የጋራ የሕዝብ ሀብት ናቸው። የእገሌ ናቸው አይባሉም። በቁጥብ እና ምርጥ ቃላት ይቀርባሉ። ከማህበረሰቡ ልማድና አኗኗር  በመነሳት የሰዎችን ህይወት ያሳያሉ። አፋዊ በመሆናቸው  ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ በንግግር ፣በቃል ይተላለፋል።

ምሳሌያዊ ንግግር በሐረግ፣ በዓረፍተ ነገር፣በግጥም እንዲሁም በጥያቄና መልስ ቅርጾች ሊቀርብ ይችላል።

ዳንኤል አበራ “ምሳሌያዊ አባባሎች የዘመናት የህብረተሰብ የእውቀት፣ የታሪክ፣ የፍልስፍና፣ የኑሮ መርህ፣ የቋንቋ፣ ባህል እና የጋራ ውጤቶች በመሆናቸው በራሳቸው ለሚኖራቸው ግለሰባዊ ወይም የተናጋሪውን ራስን የማግነን ተፅእኖ እጅግ በጣም አናሳ ነው” በማለት ያብራራሉ። ይህን ያለው ቀበሮ ነው፣ ጅብ ነው፣ ድመት ነው፣ጅብ ነው፣ ወ.ዘ.ትርፍ ከማለት በቀር አንድ ግለሰብን በደራሲነት ወይም በባለቤትነት አይጥቅሱም። ተደረገ፣ ተባለ፣ ነበር፣ አሉ፣ ድሮ፣ተብሎ እና መሰል የገለጻ ስልቶችን በመጠቀም ማህበረሰባዊ ሀብትነታቸውን እንደያዙ፣ የእገሌ ናቸው ሳይባል ከዘመን ወደ ሌላ ዘመን፤  ከአባት ወደ ልጅ ይተላለፋሉ። አሉ ብለን እኛም ታሪክን እናስታውስ።

በቀድሞ ዘመን እንዲህ ሆነ አሉ። አንድ ወንድ ሴቷን ይፈልጋትና መልእክቱን ለቄስ ይልክባታል። ሴቷ ደግሞ ቄሱ እንዴት ለዚህ ጉዳይ አሸማጋይ ሆነው መጡ በማለት ትገረማለች። ቀጥላም በግጥም ሐሳቧን እንዲህ ተናገረች።

“ ቢሆንም ይሆናል፤ ባይሆንም አይሆንም

ሰው ቢማር ቄስ እንጂ፤ ሰው መላክ አይሆንም

ከእንግዲህ በኋላ አትመላለስብኝ

ሦስት ራብዕ ፊደል ቆጥረህ ድረስብኝ”

ሦስት ራዕብ ፊደል ቆጥረህ ድረስብኝ ያለችው፤ ራዕብ ማለት አራት ማለት ነው። ፊደላቱም ‘ማ’፣ ‘ታ’፣ እና ‘ና’ ናቸው። ይህ ምሳሌያዊ ንግግር የዘመኑን አኗኗር፣ ባህል፣ የቋንቋ ደረጃ፣ እና መልክ ያሳያል።

ማታና ማታ በጨለማ መጥተህ  የምትፈልገውን ታገኛለህ የሚል ውስጠ ወይራ ንግግር ነው። አፍቃሪ ሆዬ በተሰጠው አቅጣጫ መሰረት መሄድ የእሱ ድርሻ ነው።

በነካ እጃችን ሌሎችንም ምሳሌያዊ ንግግሮች እንመልከት። አዲስ ባልና ሚስት ተጋብተው ኑሯቸውን ሞቅ ደመቅ አድርገው መኖር ይጀምራሉ። በኢትዮጵያ ባሕል መሰረት ደግሞ ቤተሰባዊ ቁርኝት ጠንካራ ስለሆነ የሚስትም የባልም ዘመዶች አዲሱን ትዳር ለማሟሟቅ ሙሽሮች ቤት በብዛት መኖራቸው የተለመደ ነው። በዚህ ስነ ቃል የምንጠቅሰው ባልም የሚስት ዘመዶች ቤታቸውን ትተው ከእሱ ቤት (ልጃችንን እንያት) እያሉ ማዘውተራቸው ምቾት አልሰጠውም። በተለይ የሙሽሪት እናት ቤት የሌላቸው ይመስል ሁልጊዜ ከቤት አልጠፋ ማለታቸው፣ የሚደረግላቸው እንክብካቤ ባልዬውን ያበሳጨዋል። ምን ብሎ እናትሽ ቤታችን አይምጡ ይበል፣ ግራ ይጋባል።  አንድ ቀን:-

”ተለመደና ዶሮ መከችከች

እኝህ እናትንሽ ሀሙስ ከች”

ብሎ ሐሳቡን፣ ትዝብትና ብሶቱን በጥበብ ተናገረ ይባላል። ምሳሌያዊ ንግግሮቻችን  አስመሳይነትን ይነቅፋሉ፤ ለራስ ጉዳይ ቅድሚያ መስጠትን ደግፈው፣ ይህ ካልሆነ ግን ውሸታምነት ነው ይላሉ። በማህበረሰቡ አኗኗር ከራስ በላይ ነፋስ ይባላል። ይህም ቅድሚያ አንተ ሰላም ሁን ለራስህ ካልሆንህ ለማንም አትሆንም፤ የራስህን ችግር ካልፈታህ የማንንም አትፈታም ከሚል መነሻ ነው። “ራስ ሳይጠና ጉተና፣ የራሷ ሲያርባት የሰው ታማስላለች፣ ለቅሶ ሳለ ከቤት፣ለቅሶ ይሄዳል ከጎረቤት”  የሚሉ ሐሳቦች ትችት አዘል ምክሮች ናቸው። በቅድሚያ የራስህን፣የቤትህን ጉዳይ ተመልከት፣ ችግርህን ፍታ የሚሉ ናቸው።

ሌላም ምሳሌ እናስከትል። በኢትዮጵያ ማህበረሰብ ቤተሰብ መመስረትና ልጆች መውለድ ትልቅ ክብር የሚያሰጥና ደረጃን የሚያሳድግ ነው። የሀይማኖት አስተምህሮዎችም የሰው ልጅ ከኃጢዓት እንዲሰበሰብ ትዳር ቢይዝ፣በአንድ ሚስት ቢወሰን፣ ልጆች ወልዶ ኅላፊነትን ወስዶ ተረጋግርቶ እንዲኖር ይመክራሉ። ኑሮ ከመቼውም ጊዜ  በላይ ተወደደ በሚባልበት  በዚህ ዘመን አንድ ወጣት ቤተሰቦቹ እና የሚያውቁት ሁሉ “ሚስት አግባ፣ ልጅ ውለድ” የሚል ምክር ሲያበዙበት “ወየው ጉድ በቅሎ ግዙ ግዙ አሞሌ ላያግዙ” የሚል ብሂልን ጠቅሶ ትዝብቱን  አሰማ አሉ ይባላል።

ምሳሌያዊ ንግግሮች ምክርም ይሠጥባቸዋል። ብዙ ሰው ከተናገረ በኋላ የሚመጣበትን ውጤት እና ቅጣት ለመቀበል ሲቸገር እናያለን። ብዙው ባልናገር ኖሮ “ሚያው ባልሁ ፍየል ከፈልሁ ሲል በጸጸት ውስጥ እንታዘባለን። ለዚህም አበው “ተናግሮ ከማሰብ ከንፈርን መሰብሰብ” ጥሩ ነው ብለው ይመክራሉ። “በለፈለፉ አፍ ይጠፉ” ብለው መናገር (መለፍለፍ) አላግባብ ሲሆን የሚያስከትለውን እዳም  ይጠቁማሉ።

እንዲሁም “ሁለት ጊዜ ተናግረህ ከፋህ፤ ሁለት ጊዜ በልተህ ተፋህ” በዚህ ብሂል ንግግርህ ልክና መጠን ቢኖረው ምን ነበር? ብዙ በልቶ ጤና እንደሚያጣ ሰው፣ ብዙ ተናግረህ አጠፋህ ነው መልእክቱ። ንግግር አውድና ሁኔታውን በመረዳት እንዲሆን አበው ይመክራሉ። “ዳኛ አይተህ ተናገር፣ ወቅት አይተህ ተሻገር” እንደሚሉት እንዲሁ “ቀድሞ ያሸተውን ወፍይበላዋል፣ ቀድሞ የሚናገረውን ሰው ይጠላዋል” በማለት ንግግር በጥበብ እና በማስተዋል እንዲሆን፣ ከመናገርህ በፊት ሁኔታዎችን ምን እንደሚመስሉ አስተውል፣ዕድሉን አገኘሁ ብለህ አትናገር  ይላሉ። ምሳሌያዊ ንግግሮች  እንደ ሁኔታው፣ እንደ ወቅቱ፣  እንደ አረዳዱ የተለያዬ ትርጉም አለው። “ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባም” ይሉ እና በተቃራኒው ደግሞ “ካለመናገር ደጅ አዝማችነት ይቀራል” ሲሉ እንሰማቸዋለን። ሁለቱንም በየ አውዱ እንደ አስፈላጊነታቸው መርጠህ ተጠቀም፤ መናገር ባለብህ ወቅት ተናገር፣ ዝምታ አስፈላጊ ሲሆንም መዝነህ ዝም በል ነው ምክራቸው።

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here