የኢትዮጵያ እግር ኳስ ስፖርት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ቢያስቆጥርም መሰረተ ልማቶቹ ግን የተሟሉ አይደሉም። የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ የታዳጊ ፕሮጀክት እና ማሰልጠኛ ማዕከላት አለመኖር ለአብነት በእግር ኳስ ሰፖርቱ የሚነሱ ችግሮች ናቸው:: በሀገራችን አንድም ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ሳይኖር መቆየቱ ደግሞ ለሰሚው ግራ ያጋባል። ረብጣ ሚሊዮን ብሮችን ለማውጣት የማይሰስቱት የሀገራችን የፕሪሚየር ሊጉ ከለቦች ስቴዲየም ለመገንባት ይሰስታሉ። ምንም እንኳ ብዙ ገንዘብ ቢጠይቅም ሰታዲየም ለመገንባት በዕቅዳቸው እንኳ አለማካተታቸው አግራሞትን ይፈጥራል።
አሁን ላይ በየቦታው የተጀመሩት የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችንም የሚያጠናቅቃቸው ጠፍቶ እንደ ቅርስ ባሉበት ቆመዋል። አንድም የካፍን መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም ባለመኖሩ ብሄራዊ ቡድኖች ከሀገር ውጪ ጨዋታዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። በተለይ ዋሊያዎቹ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የዓለም እና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያዎችን ለማድረግ ከሀገር ውጪ መሰደዳቸው የሚታወስ ነው። ይህ ደግሞ በተለያየ መልኩ የብሄራዊ ቡድኑ ውጤት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳደሩም ባለፈ ሀገሪቱን ለወጪ ሲዳርጋት ቆይቷል።
አሁን ግን ይህን ችግር የሚቀርፍ ዜና በቅርቡ መስማታችን ይታወሳል። የካፍ የጥራት መመዘኛን መሰረት በማድረግ ዕድሳት ላይ የነበረው ድሬድዋ ስታዲየም ተጠናቆ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። እንደ ካፍ መረጃ አንድ ስታዲየም ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ የካፍን የመጨረሻውን ትንሹን መስፈርት ማሟላት ይኖርበታል። ከእነዚህ መስፈርቶች መካከል በምሽት ጨዋታዎችን ማከናወን የሚችል ፓውዛ መብራት ያለው፣ ደረጃውን የጠበቀ የመጫዎቻ ሰው ሠራሽ የሳር ንጣፍ፣ የቪ አይ ፒ እና የቪቪ አይፒ (የክብር እንግዶች እና ባለስልጣናት) መቀመጫዎች ፣ የተጫዋቾች ፣ የዳኞች እና የታዛቢዎች የመልበሻ ቤት ክፍል እንዲሁም የሚዲያ ክፍል ሊኖረው እንደሚገባ ይጠቁማል።
በጥሩ መንገድ እንደታደሰ የሚነገርለት ስታዲየሙ የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም እስኪጠናቀቅ ዋሊያዎቹን ከስደት ይታደጋል ተብሏል። ሌሎች ጅምር ላይ ያሉት ስታዲየሞች እንዲጠናቀቁም መነቃቃት ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። በጅምር ላይ ካሉት እና ካልተጠናቀቁት ስታዲየሞች መካከል የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም አንዱ ነው። ግዙፉ ስታዲየም ከዚህ በፊት ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ጨዋታዎችን ካስተናገዱት መካከል በቀዳሚነት ይቀመጣል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የካፍን ዝቅተኛ የስታዲየም መስፈርት ባለማሟላቱ መታገዱ አይዘነጋም። የካፍን የስታዲየም የጥራት መስፈርት ለማሟላትም አሁን ላይ ተጨማሪ ግንባታዎች እየተከናወኑ ናቸው። የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በ2002 ዓ.ም የመጀመሪያው ግንባታው የተጀመረ ሲሆን በአራት ዓመታት ውስጥ ተጠናቆ የመላው የኢትዮጵያ ጨዋታዎችን አስተናግዷል። ከተጀመረ ከ13 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ስታዲየሙ ከዓመታት በኋላ አሁን ሁለተኛው ዙር ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል።
ለስታዲየሙ ግንባታ የክልሉ መንግስት 700 ሚሊዮን ብር፣ የሜድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ 300 ሚሊዮን ፣ ዳሽን ቢራ እና ከማህብረሰቡ በተለያየ መንገድ ከተሰበሰበ 74 ሚሊዮን ብር በአጠቃላይ በአንድ ቢሊዮን 74 ሚሊዮን ብር የሁለተኛው ዙር ግንባታ እየተከናወነ ይገኛል። በዚህ በጀትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ሥራው እየተከናወነ መሆኑን እኔም በቦታው ተገኝቼ ታዝቤያለሁ። የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የእግር ኳስ ሜዳ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም 23 የስፖርት ዓይነቶችን አንድ ጊዜ ማከናወን የሚችል ሁለገብ የማዘውተሪያ ሥፍራ ጭምር ነው።
ይሁን እንጂ እስከ 2015 ዓ.ም የመጀመሪያው ዙር ግንባታ ሳይጠናቀቅ ሲጓተት ቆይቷል። ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ግን የፊፋ መስፍርትን ለማሟላት ያልተጠናቀቁትን የመጀመሪያው ዙር ግንባታዎችን ጨምሮ የሁለተኛው ዙር ግንባታ እና ለአገልግሎት አስፈላጊ የሆኑ መሰርተ ልማቶች እየተሰሩ መሆናቸውን ከአሚኮ በኩር ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ እርዚቅ ኢሳ ተናግረዋል።
ሜዳውን ሰው ሠራሽ ሳር ማንጠፍ፣ የመቀመጫ ወንበር መግጠም፣ የቪ አይ ፒ እና የቪቪ አይ ፒ መግቢያ በሮች እና መቀመጫዎች፣ የተጫዋቾች የመልበሻ ክፍል ፣የስክሪን፣ የድምጽ ሲስተም እና ፓውዛ መብራት መግጠምም ከሚከናወኑ ሥራዎች መካከል ይገኙበታል። የልብስ መቀየሪያ ክፍሎችም ከዚህ በፊት ከነበሩት በቁጥርም በጥራትም ከፍ ባለ መንገድ ነው እየተሰሩ ያሉት። የካፍን መስፈርቶች መሰረት ተደርጎ እየተሰራ ያለው የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በተመሳሳይ ጊዜ አራት ቡድኖች ለጨዋታ መዘጋጀት የሚያስችላቸው የመልበሻ ክፍል ይኖረዋል ።
ከዚህ በፊት ለሴት ዳኞች እና ታዛቢዎች የመልበሻ ክፍል እንዳልነበረ ይታወቃል። ይሄንን ችግር ለመቅረፍም አሁን ላይ እየተሰራ ይገኛል። በተጨማሪም ለሴት እና ለወንድ ኳስ አቀባዮች ራሱን የቻለ የመልበሻ ክፍል እየተሰራም ነው ተብሏል። ቡድኖቹ ከጨዋታ በፊት እና ዕረፍት ላይ የጽንሰ ሀሳብ ልምምድ የሚያደርጉበት ክፍል ከመልበሻ ቤቱ አጠገብ እየተገነባ ነው። ይህም አሰልጣኞች አሰላለፋቸውን የሚያሳውቁበት፣ ሌሎች የቴክኒክ እና የታክቲክ ጉዳዮችን ለተጫዋቾቻቸው የሚያስረዱበት ወሳኝ ክፍል ሲሆን ግንባታውም የዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ነው እየተከናወነ ያለው።
የፕሬዝዴንሺያል (የቪ አይ ፒ እና የቪ ቪ አይ ፒ) መቀመጫዎች እና መግቢያ አሳንሰሮችም እንግዶችን በሚመጥን መልኩ በጥራት እየተሠሩ ነው። ለእነዚህ ሰዎች ለብቻ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ጭምር ነው የሚዘጋጅላቸው:: ሜዳውን በተለመከተ ደግሞ ሰው ሠራሽ ሳር የሚነጠፍለት ይሆናል።
ከዚህ በፊት ዝናብ ሲዘንብ ሜዳው ላይ የሚጠራቀመው ውሃ ወደ ውስጥ ይሰርግ የነበረ ሲሆን አሁን ግን ወደ ውጪ እንዲፈስ ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ አቶ እርዚቅ ተናግረዋል። ሥራው ሲጠናቀቅ በዝናብ ምክንያት ሜዳ ውስጥ የሚያርፈው ውሃ በአስር ሰከንድ ውስጥ ወደ ውጪ ይፈሳል ተብሏል። በዝናብ ምክንያትም ጨዋታዎች እንደማይቆራረጡ ነው የተነገረው። የፊፋ እና ካፍ ፍቃድ ባለው የፈረንሳዩ ግሪጎሪ ድርጅት የሳር ማንጠፉ ሥራ የሚያከናወንም ይሆናል::
እንደ ቢሮው ኃላፊ ገለጻ የልምምድ ቦታ ተብለው እየተሰሩ ያሉት ሁለቱ ሜዳዎች ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንዲያከናውኑ ተደርገው አስፈላጊው ነገር እየተሟላላቸው ጭምር ነው። እነዚህ የልምምድ ሜዳዎች ጨዋታዎችን በቀን ብቻ ሳይሆን በምሽትም ያከናውናሉ ብለዋል አቶ እርዚቅ። እንደ ቢሮው ኃላፊ መረጃ እያንዳንዳቸው የልምምድ ሜዳዎች በግራ እና በቀኝም እስከ ሁለት ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ይኖራቸዋል።
ለዋናው የእግር ኳስ ሜዳ ሃምሳ ሁለት ሺህ መቀመጫ ወንበሮች የሚገጠሙለት ሲሆን በሜድሮክ ኩባንያ ሥር ያለው አዲስ ጋዝ ሰብ ኮንትራክተር ወንበሮችን የማምረት እና የመገጣጠም ተግባሩን ያከናውናል። የድምጽ ሥርዓት እና የፓውዛ መብራት ግዥም ተጠናቋል። ወደ ባሕር ዳር ከተማ የማጓጓዝ ሥራ ብቻ እንደሚቀር የግንባታውን ሂደት በበላይነት የሚቆጣጠረው የአማራ ክልል ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
ግዙፍ ስክሪን መግጠምን የተመለከተ ሥራውም በሂደት ላይ ይገኛል። አንዱ ግዙፍ ስክሪን ብቻ 93 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን በሁለቱ የስቴዲየም ጎኖች የሚገጠም ይሆናል። በአጠቃላይ ግን የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ከካፍ የስታዲየም ጥራት መስፈርቶች በተጨማሪ ሌሎችም አገልግሎት የሚሰጡ አስፈላጊ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችንም እያከናወነ ነው።
ወደ ስታዲየሙ ግቢ የሚያስገቡ ከዚህ ቀደም የነበሩት ሁለት በሮች ወደ አምስት እንዲያድጉ ተደርጓል። ከውጪ ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ ወደ ቪ አይ ፒ፣ ቪ ቪ አይ ፒ፣ መግቢያ በሮች ሚዲያ እና የክለቦች የመኪና ማቆሚያ መግቢያዎች እየተሰራ ይገኛል:: የደጋፊዎች መኪና ማቆሚያ እና እግረኛ መግቢያም ተለይቶ ሥራ ተጀምሯል። በቴክኖሎጂ የታገዘ የትኬት መቁረጫ እና መቆጣጠርያ ለመስራትም በዝግጅት ላይ ይገኛል::
የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ሰታዲየም ሁለተኛው ዙር ግንባታ ጥቅምት 30 /2016 ዓ.ም ነበር ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል ተበሎ የነበረው:: ይሁን እንጂ በተያዘለት የጊዜ ቀጠሮ መጠናቀቅ አልቻለም። የግንባታ ሥራው እስካሁን የዘገየውም በውጪ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት መሆኑን አቶ እርዚቅ ኢሳ አብራርተዋል። በዚህ ዓመት መጨረሻ ግን ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ኃላፊው ተናግረዋል።
(ስለሺ ተሾመ)
በኲር መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም