አረንጓዴዉ ጎርፍ በጋና

0
212

እ.አ.አ በ1920ዎቹ አፍሪካውያን አንድነታቸውን እና ሕብረታቸውን ለማጠናከር አንድ የስፖርት የውድድር መድረክ ማዘጋጀት አስፈለጋቸው። ሊዘጋጅ የተፈለገው የስፖርት መድረክ ደግሞ “የመላው አፍሪካ ጨዋታ” እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል። ታዲያ ውድድሩ በአልጀሪያ እና በግብጽ ሙከራ ተደርጎ አልተሳካም። የስፖርት መድረኩ ገና ከጥንስሱ የከሸፈበት ዋነኛው ምክንያት ደግሞ የአውሮፓውያን ሴራ ነበር። አዲሱ መድረክ ለቅኝ ተገዥዎቹ የአፍሪካ ሀገራት የነፃነት በርን ይከፍታል በሚል ስጋት ቅኝ ገዥዎቹ ውድድሩ እውን እንዳይሆን አድርገዋል።

በ1965 እ.አ.ኣ ግን የመላ አፍሪካ ጨዋታ በዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እውቅና አግኝቶ ውድድሩ አንድ ተብሎ ተጀምሯል። በወቅቱም ከሰላሳ ሀገራት የተውጣጡ ከሁለት ሺህ 500 በላይ ስፖርተኞች በ10 የስፖርት ዓይነቶች መሳተፋቸውን የስፖርቱ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ። በኮንጎ ብራዛቪል በተከናወነው በመጀመሪያው የመላው አፍሪካ ጨዋታ ኢትዮጵያ የተሳተፈች ሲሆን አንድ የብር እና የነሐስ ሜዳሊያ ማስመዝገቧን ታሪክ ያወሳል።

የአፍሪካ ጨዋታዎች (የቀድሞ የመላው የአፍሪካ ጨዋታ) ከዛን ጊዜ ጀምሮ በየአራት ዓመቱ እየተካሄደ ይገኛል። ባለፉት ጊዜያት የውድድር ስርዓቱ ባይቀየርም የስያሜ ለውጥ ግን አድርጓል። ከ11ኛው የውድድሩ ምዕራፍ ጀምሮ የቀድሞ ስያሜውን በመተው ”የአፍሪካ ጨዋታዎች“ ብቻ በሚል  እየተደረገ ይገኛል። ይህ ግዙፍ የስፖርት መድረክም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እና እየተሻሻለ መሆኑን የአወዳዳሪው አካል መረጃ ያሳያል። የመወዳደሪያ ስፖርት ዓይነቶች መጨመር፣ የተሳታፊ ስፖርተኞች ቁጥር ማደግ፣ አስተናጋጅ ሀገራት ለመድረኩ ትኩረት መስጠት የውድድሩ ጥራት እና ደረጃ ከፍ እንዲል አድርጓል።

13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ዘንድሮ በጋና ዋና ከተማ አክራ ተደርጎ ተጠናቋል። ውድድሩ መካሄድ የነበረበት ባሳለፍነው ነሐሴ ወር ቢሆንም የስፖርት እና ሌሎች አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች ባለመሟላታቸው ምክንያት ውድድሩ ተገፍቷል። ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋና ለዚህ ግዙፍ የስፖርት ድግስ 145 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ማድረጓን መረጃዎች አመልክተዋል።

ለ15 ቀናት በቆየው የስፖርት ውድድር ከ53 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከአምስት ሺህ በላይ ስፖርተኞች በ29 የስፖርት ዓይነቶች ተካፍለዋል። ከእነዚህ የስፖርት ዓይነቶች መካከል ስምንቱ ለፓሪሱ ኦሎምፒክ ቅድመ ማጣሪያ ተደርጎባቸዋል። አትሌቲክስ፣ ባድሜንተን፣ ብስክሌት፣ ውሃ ዋና፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ የሜዳ ቴኒስ እና የመሳሰሉት የወራት ዕድሜ ብቻ በቀረው የፓሪሱ ኦሎምፒክ ማጣሪያ የተደረገባቸው የስፖርት ዓይነቶች ናቸው።

የመድረኩ ተካፋይ የነበረችው ሀገራችንም ጥሩ ውጤት ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው። በአጠቃላይ በዘጠኝ የስፖርት ዓይነት 149 ስፖርተኞች ወደ ጋና አቅንተው በውድድሩ ተሳትፈዋል። አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ቡጢ፣ ብስክሌት፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ሜዳ ቴኒስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ውሃ ዋና እና ቅርጫት ኳስ ስፖርቶች ኢትዮጵያውያን በመድረኩ የተፎካከሩበት ነው።

ከባለፉት ዓመታት አንፃር በዘንድሮው ውድድር በርካታ ሜዳሊያዎች የተገኙበትም ነበር። ከአትሌቲክሱ በተጨማሪ በብስክሌት ስፖርትም ሜዳሊያ ተገኝቷል። በሴቶች ቡጢ ስፖርት ደግሞ ለመጀመሪያ ግዜ ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎች ተገኝቷል::

በሴቶች የ52 ኪሎ ግራም የቡጢ ስፖርት ቤተልሄም ገዛኸኝ እንዲሁም ቤተልሄም ወልዴም በ66 ኪሎ ግራም  የወርቅ ሜዳሊያ በማሸነፍ አዲስ ታሪክ ጽፈዋል። በተመሳሳይ በወንዶች 75 ኪሎ ግራም ቡጢ ስፖርት  ተመስገን ምትኩ  የነሐስ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆኑ አይዘነጋም።  በብስክሌት ስፖርት ዘንድሮ ሀገራችን ሜዳሊያ ውስጥ ገብታ ማጠናቀቅ ችላለች። የታዋቂው የቀድሞ ብስክሌተኛ የልጅ ልጅ የሆነው ኪያ ጀማል ሮጎራ የአያቱን ፈለግ በመከተል የሀገሩን ስም አስጠርቷል። ኪያ ጀማል ሁለተኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ነበር  የብር ሜዳሊያ ያገኝው።

በተለይ በአፍሪካውያን ልዩ ትኩረት በሚሰጠው እና ሀገራችን በዓለም አቀፍ መድረኮች ጎልተው በሚታዩበት የአትሌቲክስ ውድድርም አንጸባራቂ ድል መመዝገቡ የሚታወስ ነው። በመም እና በሜዳ ተግባራት የተሳተፉ 87ቱ አትሌቶቻችንም ሰባት ወርቅ ፣ሰባት ብር እና አራት የነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ 18 ሜዳሊያዎችን መሰብሰብ ችለዋል። ሀገራችን በአትሌቲክሱ ዘርፍ ብቻ በደረጃ ሰንጠረዡ ከናይጀሪያ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በሴቶች 5ሺህ ርቀት የአረንጓዴው ጎርፍ ታሪክ በአክራ ሰማይ ስር ዘንድሮ ተደግሟል። መዲና ኢሳ ፣ ብርቱካን ሞላ እና መልክናት ውዱ በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል። ከመዲና ኢሳ በተጨማሪ ጽጌ ዱጉማ በ3ሺህ ሜትር  እና ሒሩት መሸሻ በ1500 ሜትር ርቀት ወርቅ ያመጡ ሴት አትሌቶች ናቸው።

በወንዶች ደግሞ ሳሙኤል ፍሬው በ3ሺህ   ሜትር መሰናክል፣ ምስጋና ዋቁማ በ20 ኪሎ ሜትር እርምጃ፣ ሀጎስ ገብረህይወት በ5 ሺህ ሜትር እና ንብረት መላክ በ10ሺህ ሜትር ርቀት ለሀገራችን የወርቅ ሜዳሊያ አምጥተዋል።

ገመቹ ዲዳ፣ ስንታየሁ ማስሬ፣ ውዴ ከፋለ፣ ኤርሚያስ ግርማ፣ ሀዊ አበራ እና ዘውዲቱ አደራው ደግሞ የብር ሜዳሊያ ባለቤቶች ናቸው። ሎሚ ሙለታ፣ አበራ አለሙ እና ተካን በርሄም ልክ እንደ መልክናት ውዱ እና ተካ ተመስገን በጋናው መድረክ የነሐስ ሜዳሊያ ያገኙ አትሌቶች ናቸው።

ኢትዮጵያ በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ዘጠኝ ወርቅ ስምንት ብር እና አምስት ነሐስ በድምሩ 22 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዡ ስምንተኛ ሆና ጨርሳለች።  ግብጽ በ187 ሜዳሊያዎች የደረጃ ሰንጠረዡ አናት ላይ ሆና ስታጠናቅቅ፣ ናይጄሪያ በ121 ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ደረጃን ይዛ መጨረሷ ይታወሳል። ደቡብ አፍሪካ ደግሞ በ106 ሜዳሊያዎች ሦስተኛ ሆና ማጠናቀቋ አይዘነጋም።

በዚህ ውድድር በአጠቃላይ 23 ሀገራት ሜዳሊያ ዝርዝር ውስጥ ገብተው አጠናቀዋል። ከእነዚህ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ ዘንድሮ ከባለፉት ዓመታት የተሻለ ሜዳሊያ መሰብሰብ ችላለች። ለአብነት ከአራት ዓመታት በፊት በሞሮኮ ራባት በተደረገው 12ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች ስድስት ብቻ የወርቅ ሜዳሊያ ማስመዝገቧ አይዘነጋም። ዘንድሮ ግን ተጨማሪ ሦስት ሜዳሊያዎችን ማግኘቷ የሚታወስ ነው።

ሀገራችን ከአትሌቲክሱ ዘርፍ ውጪ በቡጢ እና በብስክሌት ስፖርት የወርቅ እና የነሐስ ሜዳሊያን ማግኘቷ ተስፋ ሰጪ ሆኗል። የስፖርቱ አቅም ባለባቸው ሁሉም ቦታዎች  ትኩረት ተሰጥቶ ቢሰራ ደግሞ ከዚህ በላይ ውጤት ሊመዘገብ እንደሚችል የአክራው መድረክ አመላክቷል። በአማራ ክልል እንኳ በባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴ እና ወልዲያን የመሳሰሉ ከተሞች በርካታ ባለተሰጥኦ የቡጢ ስፖርተኞችን ማግኝት የሚቻልባቸው ቦታዎች እንደሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በተመሳሳይ በብስክሌት ስፖርትም ባሕር ዳር ከተማ ሰፊ አቅም ስለመኖሩ የቀደሙት ዓመታት ውጤቶች ምስክሮች ናቸው። በ13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች በሜዳ ተግባራት አበራ ዓለሙ በምርኩዝ ዝላይ ያስገኘው ሜዳሊያ ለዘርፉ ትኩረት ቢሰጥ ሀገራችን ተፎካካሪ በመሆን ተጨማሪ ሜዳሊያዎች ሊመዘገቡበት የሚችል ዘርፍ መሆኑን ዐይተናል።

በእግር ኳስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስ፣ ሜዳ ቴኒስ እና ውሃ ዋና ስፖርቶች ግን ከሌሎቹ ጠንካራ ከሆኑ ሀገራት ብዙ መማር እና መሻሻል እንደሚኖርብን የተመዘገቡ ውጤቶች ያመለክታሉ።  የአፍሪካ ጨዋታዎች መድርክ አዳዲስ ፊቶች የሚታዩበት፣ ወጣቶቹ ራሳቸውን የሚያሳዩበት መድረክ እንደሆነ ቢታወቅም በዘንድሮው የአክራ መድረክ ግን ከወጣቶቹ ይልቅ በርካታ አንጋፋ ኢትዮጵያውያን ሰፖርተኞችን የተመለከትንበት ሆኖ አልፏል::

ባለፉት 13 የመድረኩ ምዕራፎች 50 ሀገራት ሜዳሊያ ዝርዝር ውስጥ መግባት ችለዋል። የዓለም አቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል ከሆኑ 54 ሀገራት ውስጥ እስካሁን በመድረኩ ታሪክ አራት ሀገራት ብቻ ሜዳሊያ አለማሳካታቸውን የአፍሪካ ጨዋታዎች ድረገጽ መረጃ ያስነብባል።

ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ግብጽ በአጠቃላይ በመድረኩ አንድ ሺህ 826 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ቀዳሚ ሀገር ናት። ናይጄሪያ አንድ ሺህ 448 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ሁለተኛ እና ደቡብ አፍሪካ በአንድ ሺህ 159 ሜዳሊያዎች ሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ  ደግሞ 196 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ከአራት ዓመታት በኋላ የሚደረገውን 14ኛውን የአፍሪካ ጨዋታዎች ግብጽ  ለሁለተኛ ጊዜ የምታስተናግድው ይሆናል።

 

(ስለሺ ተሾመ)

በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here