ጄኔቫ

0
200

ባህር ማዶ ሻገር እንበል፤ ወደ አንዷ ካንቶን ምድር፤ ወደ ተወዳጇ ውብ አውሮፓዊት ሀገር ስዊዘርላንድ።  ካንቶን በኢትዮጵያ ክልል እንደምንለው ነው። በስዊዘርላንድ 26 ካንቶኖች አሉ። ከእነዚህም ውስጥ የጄኔቫ ካንቶን ይጠቀሳል። ጄኔቫ የሀገሪቱ ዋና ከተማ እና የካንቶኑ ዋና ከተማ በመሆን ታገለግላለች።  በ16 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ስፋት ላይ የተቀመጠችው ጄኔቫ ወደ 200 ሺህ ሕዝብ ይኖርባታል።

ጄኔቫ በሁለት የተራራ ሰንሰለቶች መሀል የተገነባች ናት። ጄኔቫ ሐይቅ በሚባለው ደቡብ ምእራብ በኩል ትገኛለች። ከዚህም ሐይቅ ሮህኒ ወንዝ ወጥቶ መፍሰስ ይጀምራል። ታዲያ ስለዚህች ውብ የዓለማችን  ከተማ ነው በዚህ ጽሑፍ በወፍ በረር የምንቃኘው።

ጄኔቫ ውስጥ  የሰው ልጅ ስልጣኔ ምልክቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የታዩት በለማን ሐይቅ (ጄኔቫ ሐይቅ)  ዳርቻዎች ላይ  በ3000  ቅድመ ዓለም ግድም እንደሆነ የከተማዋ ታሪክ ያስረዳል። የሐይቁን መውጫ የተቆጣጠረው  የቀድሞዋ ከተማ ኮረብታ /ተራራ (hill) እስከ 1000 ቅድመ ዓለም ድረስ ሰው አልሰፈረበትም። ወደ 500 ቅድመ ዓለም አካባቢ  ሴልቲኮች እንደ ምሽግ ይጠቀሙባት ነበር።

ሮማውያንን እና ሄልቬታውያን ጄኔቫን በ50 ቅድመ ዓለም ከፈረንሳዩ ጎውል ጋር ለነበራቸው ጦርነት እንደ መስፈንጠሪያ ስፍራ ይጠቀሙባት ነበር።

በ371 ዓ.ም ጄኔቫ የጳጳሱ መቀመጫ እና በሮማ ግዛት ስር ነበረች። በ435 ዓ.ም ከተማዋ በቡርጋንዲ ጎሳዎች ተይዛለች፡፡ በኋላም በ526 ቡረጋንዲ  በፍራንኮ ጎሳዎች ተያዙ። በ880 ዓ.ም ከተማዋ የአዲሱ የቡርጋንዲ ስርወ መንግሥት አካል ሆነች። በ1024 ዓ.ም ደግሞ ለጀርመኒክ ንጉሠ ነገሥታት እጅ ተሰጠች።

አስራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ኢንዱስትሪዎች በተለይ የሰዓት አለካክ ጥበብ፣ የቢዝነስ እና የባንክ ስርአት የፈነዳበት ወርቃማው ዘመን ነበር። በተያያዘም ባህል እና አርት ነክ ፈጠራዎች ያበበበት ነበር። ጄኔቫ የደን ጃኪዩዝ ረሱ የትውልድ ቦታ፣ የቮልቴር መኖሪያ ነበረች።   ሌሎች የአብርሆት ዘመን አንቂዎችን ቀልብ ስባ ነበር።

ጄኔቫ በ1790 ዓ.ም በፈረንሳይ ተይዛ ከቆየች በኋላ በ1813 ዓ.ም የናፖሊዮን ቦናፓርቲ ሰራዊት ከተሸነፈ በኋላ ነፃነቷ ተመለሰላት። የሪፐብሊኩ ማጅስትሬት በስዊዝ ኮንፌዴሬሽን ለመካተት ያቀረበው ጥያቄ በ1807 ዓ.ም ተቀባይነት አግኝቶ ተቀላቀለች።

ጄኔቫ የተወለደው የቢዝነስ ሰው እና የማህበራዊ አንቂ የነበረው ሄነሪ ዱናንት በ1855 ዓ.ም የዓለማቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ እንዲፈጠር አነሳስቷል። በጦርነት የማይሳተፉ ንፁሃን እና የጦር ምርኮኞች አያያዝን የተመለከተው የ1856 ዓ.ም የጄኔቫ ስምምነት፣ በዱናንት እሳቤዎች የተመሰረተ ነበር። በዚህም የተነሳ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጄኔቫ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ ዋና መቀመጫ እንድትሆን ተመርጣ እንደነበር ታሪክ ያስረዳል።

በዋናነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በርካታ ወኪሎች ዋና  መስሪያ ቤቶችን እና አለም አቀፍ ቀይ መስቀልን ጨምሮ በርካታ ዓለማቀፍ ድርጅቶች በመኖራቸው ምክንያት ጄኔቫ በስፋት እንደ አንድ የዓለም ከተማ ተደርጋ ተቆጥራለች። እንዲሁም ደግሞ የጄኔቫው ስምምነት የተፈረመባት ስፍራ መሆኗም ሰፊ ግምትን አስገኝቶላታል።።

ጄኔቫ እናት ሀገሯ ስዊዘርላንድ ዝነኛ የሆነችባቸውን አብዛኛዎቹን ነገሮች አቅፋ ይዛለች፤ ትንፋሽ የሚያሳጥሩ ውብ የቦታዎች፣ ደረጃውን የጠበቀ ወይን፣ ቼኮሌት እና አይብ እንዲሁም  የሰአት ስራ ጣሪያው ጄኔቫ ናት። በዚህ ላይ የተለያዩ ባህል በአንድ ላይ የሚኖሩባት ከተማ ስትሆን ፈረንሳይኛ፣  ጀርመንኛ፣ እና ጣሊያንኛ ቋንቋዎች የሚዘወተሩባት እና ብዙ የዓለም ድርጅቶች ዋና መስሪያ ቤታቸውን የተከሉባት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እንደ አንድ የዓለም አቀፍ ማእከል (መናኸሪያ) ሆና ታገለግላለች።

እጅግ አማላይ በሆነችው ጄኔቫ ውስጥ የጄኔቫ ሐይቅ ውብ ገፅታ፣ አልፎም ከከተማዋ ብዙም ሳይርቁ ባሉት አስደማሚ ገጠራማ መንደሮች ከብዙ በጥቂቱ ከተማዋን ደጋግመው  ቢመጡባት የማትሰለች ከሚያደርጓት ነፍስን በሀሴት የሚያረኩ ነገሮች ናቸው።

ውበት በሚያረብባት ውቧ የጄኔቫን ጎዳናዎች ይዘው ግራ ቀኟን እየቃኙ በእግርዎ ዞር ዞር ቢሉ በሚያዩት ነገር ሁሉ መደመምዎ አይቀሬ ነው። እፁብ ድንቅ ሕንፃዎቿ፣ አውራ ጎዳናዎቿ፣ ውብ ዛፎች እና አበቦች ተባብረው የሚረጩት የውበት ቃና ያለማጋነን መቼም አይረሴ ሆነው በህሊናችሁ ውስጥ ታትመው ይቀራሉ። በእግር እየተዟዟሩ ከተማዋን ሲጎበኙ መንገዱ ዳር ለከተማው ውበት ከሆኑት መካከል በክብ የሰዓት ቅርፅ የተዘጋጀ በአረንጓዴ ሳር ያማረ መሬት ሊመለከቱ ይችላሉ። በርግጥም አረንጓዴው የመሬት ላይ ሰዓት ይቆጥራል። ለከተማዋ አዲስ ያልሆነ ሰው ጥበብን አይቶ ከመደመም ያለፈ ትርጉም አለው። ሰዓት  እና ጄኔቫ የሚያወዳጃቸው ረጅም ታሪክ አለው።

ጄኔቫ ብራንድ የሰዊዝ የእጅ ሰዓቶች መፈብረኪያ ማእከል ናት። ከሦሥት ክፍለ ዘመን በላይ ለዘለቀው ጊዜ የስዊዝ ሰዓት  ሰሪዎች የዓለም የሰዓት ልኬት ጥበብ ግንባር ቀደምት መሪዎች ተደርገው ይታሰባሉ።  የጥራት ደረጃውን ለጠበቀ የጥበብ ስራ የተሰጠ  ከፍተኛ ክብር ነው፡፡ እናም ሲውዘርላንድ ውስጥ በመቶዎቹ የሚቆጠሩ ሰሪዎችን ሊጎበኙ ይችላሉ። በዓለም የታወቁ እንደ ሮሌክስ፣ ቾፓርድ እና ካርቲየር አይነት ብራንዶች  ራሳቸውን እና የገዛ ሀገራቸውን ከዓለም ቁንጮ ላይ ያስቀመጡ ናቸው። ጄኔቫ ደግሞ የስዊዝ ትልቋ የሰዓት ኢንዱስትሪ ማሳያ ናት። ጄኔቫ ውስጥ የሰዓት ስራ ትምህርት ቤቶች፣ ቱሮች፣ እንዲሁም ቡቲኮች ይገኛሉ።

ምንም እህት ከተማ የሌላት ጄኔቫ ራሷን የምታየው የመላው ዓለም ወዳጅ አድርጋ ነው። በመሆኑም ዓለም አቀፋዊ ቃና አላት ይሏታል። ቤታቸው ያደረጓት ልዩ ልዩ የዓለም ድርጅቶች ናቸው።

ጄኔቫ የዓለም ዲፕሎማቶች ከተማ ናት፡፡ ምክንያቱም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የዓለም የጤና ድርጅት፣ የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን(UNHCR)፣ የዓለም ንግድ ድርጅት እና ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማህበር፣ የዓለም የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ኮሚቴ፣ የዓለም አእምሮ ንብረት ጥበቃ ድርጅት ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ።.

በከተማዋ ውስጥ ከዓለም ዙሪያ የሆኑ የተለያዩ ቋንቋዎችን እና ሰዎችን ማግኘት የተለመደ ነው። ከተለያዩ አህጉራት የመጡ ሁሉ እንደ ባህሪታቸው እና እንደ ባህላቸው የሚያስተናግዱ ሰፊ የሬስቶራንት አማራጮች አሉ። ማንም በቋንቋው አዝዞ የሚመገብባት ምርጥ ከተማ ናት።

የዓለማችን ቢልየነሮች መንፈላሰሻ ተመራጭ ከተማም ናት። ታዲያ በዓለም ውድ ከተሞች አንዷ ናት። የጄኔቫ ዋጋ ዉድ ሊሆን ስለሚችል ታዲያ ከተማዋ ከፈረንሳይ ጋር ቅርብ እና ወሰን ስለምትጋራ ሰዎች 10 ደቂቃ ተጉዘው በፈረንሳይ ከተሞች ጥሩ፣ እርካሽ ሬስቶራንቶች ተመግበው ለመመለስ አመቺ ናት።

ጄኔቫ በሁሉም ወቅቶች ድንቅ ናት። በዝናብ፣ በበረዶ ወይም በፀሐይ ወቅት ብዙ ደስታን ትለግሳለች። ከታህሳስ እስከ የካቲት ጄኔቫ በበረዶ የምትሸፈንበት ጊዜ ነው። ታዲያ ጄኔቫ በአንዳንድ ክፍሏ እና በሀይቁ ዳርቻው የበረዶ ሸርተቴ ስፖርት መዘውተር ይጀምራል። ከመጋቢት እስከ ጥቅምት ደረቃማ አየር ይኖራል። በዚህ ወቅት የጄኔቫ ሐይቅ የተለያዩ የውሃ ስፖርት ማእከል ይሆናል።

በሌላ በኩል ጄኔቫ የሳይንሳዊ ምርምር እና እድገት ማእከል ናት። እግዚአብሔር ዩንቨርስቲን የፈጠረበትን ሚስጢር ለማግኘት የዓለማችን የፊዚክስ ተመራማሪዎች የሚታሰሩበት ሰርን የተሰኘው የምርምር ማእከል የሚገኝባት ከተማ ናት ጄኔቫ። ስዊዘርላንድ በተሻለ ከምትታወቅባቸው አንዱ የእጅ ሰዓት  ስራ ነው። ሌላው ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ነው። ጄኔቫ በዓለም እውቅና የተሰጠው ሰርን የተባለው የፓርቲክል ፊዚክስ ተቋም ነው። ተቋሙ በፈረንሳይ ሲውዘርላንድ ድንበር ላይ 27 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ከምድር ስር 175 ሜትር ከመሬት በታች ውስጥ ለውስጥ የተቦረቦረ ረጅም ቱቦ ወይም ዋሻ ነው። የአውሮፓ ትልቁ የኒውክሌር ማብላያ ተደርጎም ይታወቃል። ግዙፉ ማሽን ስራ በማያከናውንበት ጊዜ በአስጎብኝ እየተመሩ የዩንሸርስን መነሻ ለማግኘት ስለሚደረገው ታላቁ የምድራችን ግንዛቤ ለማግኘት የጉብኝት እድል ዝግ አይደለም። ጄኔቫ የመሄድ እድሉን ሲያገኙ ሰርንን ከጎበኙ መልካም ነው።

ጄኔቫ የስነጥበብ እና የታሪክ ማሳያ ናት። በርካታ ጋላሪዎች እና ሙዚየሞች በደንብ አሰናድታ ይዛለች። የስዊዝ የሰዓት ስራ ታሪክ ህይወት የተላበሰው በጄኔቫው ፓቴከ ፊሊፔ ሙዚየም ነው። የቀይ መስቀል እና የቀይ ጨረቃ የዓለማቀፍ ሙዚየም የቀይ መስቀልን እና ቀይ ጨረቃን የሰብአዊ ስራን በአጭሩ የሚያስረዳ ቋሚ ማሳያ የተደራጀበት ነው። በጄኔቫ የኢትኖግራፊክ ሙዚየም ውስጥ  የተለያዩ የዓለም አካባቢ ባህሎችን በተመለከተ ሙዚየሙ ከያዛቸው በመቶዎቹ ከሚቆጠሩ ቅርሶች መማር ትችላላችሁ።

ምንጭ፡-geneacity.org, Ungeneva.org,Geneva.info

 

 

(መሰረት ቸኮል)

በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here