“ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ”

0
207

ሁሉም ዘመን ጥሩ እና መጥፎ አለው። በኢትዮጵያም ጥሩ ጊዜያት አልፈዋል፤ መጥፎዎቹም አልፈዋል። ተወደደም ተጠላም ግን ሁሉም አላፊዎች መሆናቸው ይገርማል። በመጥፎው እንጸጸታለን ፣ በጥሩው እንጽናናለን። መስማማት ባልተደረሰበት የኢትዮጵያ ታሪክ ጉዞ ላይ ብዙ ውዝግቦች አሉ። ዘመን ሰዎችን ወክሎ ሲናገር፣ ሲፈርድ፣ ሲያደላ፣ ሲያስደስት፣ ሲያደርግ፣ ሲናገር፣ ሲገድል፣ ሲበድል… እና ሌሎችንም ሲያደርግ እንመለከተዋለን። ዘመን መሪውን ይመስላል፤ መሪዎችም ትልቅ ትኩረት የሚያደርጉት የስልጣን ዘመናቸው በእነሱ ስም የሚጠራ፣ የሚታወሱበት፣ እነሱን መሰል እንዲሆን ነው። ድርጅቶች፣ ተቋማት፣ ሕግ እና መመሪያዎች መሪዎች ሊያሳኩት በሚፈልጉት መስመር ይቀየሳሉ።

እርግማን ይመስል በሀገራችን አንዱ መሪ በሌላ ሲተካ፣ ሽግግሩ ጤናማ አይደለም። የብዙኀንን ደም እና ሕይወት በመንጠቅ የሚጀምር ነው። አዲሱ ሥርዓት በአሮጌ ሲተካ፣ አዲስ የተባለው በሌላ አዲስ ሲለወጥ፤ በጭብጨባ የሰቀሉት በጩኸትና ጥይት ሲወርድ ሕዝብ በአዲሱ ተስፋ ያደርጋል።

የጠብመንጃ አዙሪት አለብን እና እንደገና አሁንም አዲሱ ሥርዓት የተጣለበትን ተስፋ ዘንግቶ፣ በሕዝብ ፊት የገባውን መሐላ ትቶ ፈላጭ ቆራጭ ይሆናል። መቃወም የማይሰለቸው ሰፊ ሕዝብ እንደገና በፈላጭ ቆራጩ አገዛዝ ላይ ሰይፉን ያነሳል። ያንን ጊዜ ስነ ቃሉን መምዘዝ ይጀምራል። “ትሻልን ሰድጄ  ትብስን አመጣሁ” ብሎ ብሶቱን ይገልጻል። ይህ ቅኔያዊ ትርጉሙ እና በምስጢር ማስተላለፍ የተፈለገው ነው። ይህንን ንግግር በሌሎች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ሰዎች ይጠቀሙበታል። በፖለቲካው መስክ ከላይ ተመልክተነዋል እና በማህበራዊ ዘርፍ ደግሞ የሆነውን እንመልከት እንደ ብሂል አሉ ብለን እንቀጥል።

ድሮ፣ ገና ድሮ ነው አሉ። አንድ ባላገር ሚስቱ ሙያ ባለመቻሏ በማሕበረሰቡ ዘንድ የሚሰጠውን ክብር አላገኝ ይላል። ድግስ፣ ማህበር፣ ደስታና መከራ ቢሆን ቤት ውስጥ ሁልጊዜ ባልዬው መሳቀቅ አልለየው ይላል። ይህ ባላገር በወዳጅ በዘመድ ሚስት ፈልጉልኝ ብሎ ሌላ  አፈር አይንካኝ የምትል፣ ምጣድም እንዝርትም፣ ወጥም ጠላም የማትሠራ ቆንጆ ሴት ያገባል። ያን ጊዜ ባላገሩ “ትሻልን ሰድጄ  ትብስን አመጣሁ” ብሎ ከትናንቷ ሚስቱ የባሰ ገጠመኝ ብሎ ተናገረ ይባላል። ይባላል ነው የስነ ቃል ብሂሉ።

ከዚሁ ጋር የሚመሳሰሉ በተለያዩ አውዶች፣ በተለያዩ አካባቢዎች እና ሰዎች የተነገሩ ብዙ ምሳሌያዊ ንግግሮች አሉ። የተሻለ ተመኝቶ የባሰ መጥፎ ማግኘት እርግማን ነው። “የባሰ አለ አገርህን አትልቀቅ”፤ “እልፍ ሲሉ ጉንትር” የሚሉ መሰል አባባሎችም አሉ። ጅብ አባሮት ከዛፍ ሲወጣ ነብር የሚጠብቀውን ሰው አስቡት፤ እንዲያ ነው ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ ማለት።

ሀገሬው ለክፉም ለደጉም ብሂሎች አሉት።  እኔን ያየህ ተቀጣ እንደሚለው ሁሉ “የባሰ አለና ሚስትህን  አትፍታ ብሎ” በቀጣይ ሚስቱን ሊፈታ ያሰበውን ሰው በምክር አዘል ማስጠንቀቂያ ሸንቆጥ ያደርገዋል። “አያ እገሌን አላየህም  እንዴት ያችን የመሰለች ሸጋ ሚስት ፈትቶ ይህችን ምንም ማታውቅ ሙያ የለሽ ሲያገባ” ብሎ በማስረጃነት ያጣቅሳል።

አንዱን ካላዩ አንዱን አያመሰግኑም እንዲሉ አበው ሕይወት ወደ ኋላ ሲያዩት ይጣፍጣል መሰለኝ። ብዙዎች ነገሮቻችን ትናንት ላይ ይጣፍጣሉ። ዛሬ መራር ነው ያልነው “ዛሬ” እንኳን ሲያድር እንደ ወይን የሚጣፍጠው ለምን ይሆን? 1998 ዓ.ም ቅርብ ጊዜ ነው።  አንድ አምባሻ 20 ሳንቲም ይሸጥ ነበር።

የሠፈራችን እውቅ  አምባሻ  ጋጋሪ በትሐ  ትባላለች። አምስቱን   ይዤ ቤቴ እመጣና እናቴ ሻይ ታፈላለች። ትኩስ አምባሻዬን በልቼ እየሮጥሁ ወደ ትምህርት ቤቴ። እናቴ አምስት ልጆችን በአንድ ብር ቁርስ አበላች ማለት እኮ ነው።  ያን ጊዜም ጊዜው ክፉ ይባል ነበር። ኑሮው ተወደደ  ይባላል። 2000 ዓ.ም ላይ ነገሮች  በፍጥነት ተለወጡ። 30፣ 35፣ 50… እያለ ዋጋ ማሻቀብ ጀመረ።

ምሬትና ሕይወት እኩል መሳ ለመሳ ቀጠሉ። ተመስገን ያልተባለበት ዛሬ ትናንት ሲሆን “ይቅር በለኝ” ይባላል። ዘንድሮ ላይ በ18 ዓመታት ውስጥ 25 ሳንቲም የሚገዛ አምባሻ 25 ብር ደረሰ። እኛም ትናንት የረገምነውን ዛሬ እየመረቅን፣ ትናንት በተስፋ የጓጓንለትን ተቀብለን ረግመን፣ ሲያልፍ ደግሞ የባሰው መጣብን  እያልን አለ።

ትናንት ዛሬ እና ነገ የሚባሉ የጊዜ ምዕራፎችን  በዚህ “ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ” በሚል  ምሳሌያዊ አባባል ውስጥ እናገኛለን። “በሽታ በሽታን ያስመርጣል” ነው እና በትናንት የጠፋን እምነት፣ የቃል ኪዳን ጉድለት በዛሬ ማግኘት ባለመቻሉ ነገን ተስፋ እያደረጉ በልጅነቱ ያልተመሰገነውን ዛሬን በእርጅናው ትናንት ምዕራፍ ላይ እናመሰግነዋለን።

አባቴ በተደጋጋሚ የሚጠቀምባት አባባልን ላስታውሳችሁማ። ነገሩ እንዲህ ነው፣ የገጠር ሰው ቅዳሜ ወይም በሌሎች ከሥራ ውጪ ቀናት እህሉን በአህያ ጭኖ፤ የክት ልብሱን ለብሶ ወደ ገበያ አንዱን ሸጦ ሌላውን ሸምቶ ለመምጣት ያቀናል።

ታዲያ አቧራው፣ እሾሁና ቆንጥሩ፣ ጭቃው፣ ዳገት ቁልቁለት ሳያንሰው አህያው በጀርባዋ የተጫነችውን ታጋድልበታለች። እንደምንም አስቁሞ ጭነቷን  ያጠብቅና መንገድ ይቀጥላል። አሁንም ትንሽ እንደተጓዘች አህያዋ ጭነቷን  ታጋድላለች።

ባላገሩ ሰው ክላሹን፣ ጃንጥላውን፣ ጋቢውን ያስቀምጥና በደንብ አህያዋን ደረቷ ጥግ ድረስ አጥብቆ መጓዝ ይጀምራሉ። አህያዋ ደረቷን  መጫኛው ስለያዛት ቁና ቁና መተንፈስ ትቀጥላለች። ወዲያ ደግሞ ድንገት የመንገድ ቋጥኝ ይገፋትና ጭነቷን ይዛ ትጋደማለች ። ባላገሩ ስትወድቅ እያነሳ፣ ስታጋድል እያቃና፣ ስታላላ እያጠበቀ በብዙ አልፎ ነው ገበያ የሚደርሰው። የእህል ገበያ ከረከሰበትስ? ድጋሜ ጭኖት ወደ ቤቱ ይመለሳል።

ከአህያዋ ጋር  እንዲህ እየታገለ ገበያ ይደርሳል። ይህ ባላገር ደግሞ ሌላ ጣጣ አለበት። የወንዶች ዓይን ማረፊያ ሚስቱን ከኋላው አስከትሏል። ጥላዋን ይዛ ሽቶዋን ተቀብታ፣ ነጠላዋን አጣፍታ በደንቡ መሰረት ከበሏ ኋላ ኋላ ትከተለዋለች። ሽፍታ ሚስቴን ቢቀማኝስ?፣ አህያዋ ጭነቱን ገልብጣ ብትጥለውስ?፣ የእህል ዋጋ  ረክሶ ቢሆንስ፣ ልብሴን አህያዋ ጭቃ አለበሰችኝ… እና ሌሎችን ሐሳቦች እያውጠነጠነ ይጓዛል።

በገጠር አኗኗር ኀይል  ትልቅ ዋጋ አለው። ኀይል ካለህ የሰው ክምር ሲበላ የዋለ በሬህን ሰው አይነካብህም። ደካማ ከሆንህ ደግሞ ገና በማሳው ጥግ ሲያልፍ እግሩን ይሰብሩታል። ለዚህም  ቆንጆ ሚስትን ከሚመኛት ባለጌ ማስከበር  በሚወዳት ሚስቱ በኩል የሚመጣን ጥቃት መመከት ትልቅ ፈተና ነው። ለዚህ ነው አባቴ  “ሴት ያስከተለ እና አህያ የጫነ፣ እንደልቡ አይጓዝም” የሚለው።

ከጥንቃቄ እና ፈጣሪ እርዳታ ጋር  በተገናኘ አንዲት  ሐሳብ ላስከትል። “አላህንም አምናለሁ፣ አህያዬንም አስራለሁ” ያሉት አንድ ሙስሊም ሕብረተሰቡ የግል ጥረቱን ሳያደርግ ፈጣሪ አለ በሚል መስነፍን  በመመልከታቸው ይመስላል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የተከሰተ ሰሞን ሕዝቡ የጥንቃቄ መልእክቶችን ሰምቶ ተግባራዊ ለማድረግ ተቸግሮ ነበር። ሕዝቡ “ፈጣሪ ያድነናል፣ኢትዮጵያ የሀይማኖት ሀገር ናት፣ ምንም አንሆንም” እያለ ተዘናግቶ ነበር። የሀይማኖት አባቶች ደግሞ እምነት ብቻውን አያድንም፣ሥራም ያስፈልገዋል፣ ፈጣሪ እንዲረዳን እኛ ምክንያት እንሁን የሚሉ ሐሳቦችን በተደጋጋሚ በብዙኀን መገናኛ አስተጋቡ። አንድ ቀን አንድ ሼህ “አላህንም አምናለሁ፣ ግመሌንም አስራለሁ” በሚል ሲመክሩ ሰምቻቸዋለሁ።

“በቅሎ እንደገሪው፣ሕዝብ እንደመሪው” የሚሉት የአበው ብሂል ሕዝብ መሪው ያደረገውን ይመስላል፣ ይቀረጻል ይላሉ። ሰነፍ፣ ተንኮለኛ ሰው የገራው በቅሎ እየደነበረ፣ እንዳለመጠ የገራውን ሰው ይመስላል። በተመሳሳይ መሪው ሙሰኛ፣ ሌባ፣ ጦረኛ ከሆነ ሕዝቡም ያንኑ ይሆናል። ሕግን ማስከበር የነበረበት የሀገር  ራስ መሪ  ያጠፋውን የጥፋት መንገድ ሕዝቡ ፈራ ተባ እያለ ይቀላቀለዋል።

ያን ጊዜ ውሻ በቀደደው ጅብ  ይገባል ይባላል  እንዳጠፋሽ አጥፍቻለሁ በሚል ይሻገራል። እንዲህ ዓይነት የመሪዎች አጥፊነት ሲፈጠር ደግሞ የተቋማት መሪዎች “ምን በእግሩ  እየመጣ፣ በእጁ እንዳይመጣ” የሚሉ ይሆናሉ።

የሰው ልጅ እኖር ባይ ነፍሱ ጥበብ መሳይ ማምለጫ ስልትን እንዲያይ  ታስገድደዋለች። እውነቱን ፊት ለፊት የሚናገር ቢኖርም እንኳን፣ ብዙኀኑ እውነትን በአፍላ ዕድሜዋ ስትዳፈን ዝም ይሉና በአሮጌነት ዘመኗ ከተዳፈነችበት አቧራ አራግፈው ያወጧታል። ፕላቶ እንደሚለውም “እውነቱን እንደሚናገር ሰው የሚጠላ የለም” እና እውነት መናገር የሚያስከፍለው ዋጋ ሕይወትን የሚፈታተን በመሆኑ ዘመኑን አልፎ ፤አንድ ቀን ይወጣል።

በኢሕአዴግ ዘመን ኢሕአዴግ ቅዱስ ነው፤ ይህን የሚክድ ይቀጣል። ርኩስ ቢሆንም ርኩስ አይባልም። በወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል እንዲሉ ስልጣኑን አጥቶ ያረጀ አንበሳ ሲሆን ቀድሞ ያደረጋቸው ገመናዎቹ ይዘከዘካሉ። ይህንን አነሳሁ እንጂ በሌሎች አኗኗራችንም ዛሬን ዛሬ አንናገርም። አርፍደን ዛሬን ነገ ነው ምንኮንነው። ለዚህም   የአዕምሮ ጤና መታወክ  ችግር  ያለባቸው  ሰዎችን  በ አሉ ተባሉ ብሂል በመጠቀም  ዛሬ ስለ ዛሬ እንናገራለን። ይህን ጊዜ ነበር አበው “እብድ እና ዘመናይ የልቡን ይናገራል” ያሉት።

ብልህ ዝነኞች የሚያደርጉት አንድ ነገር አለ። ሆን ብሎ መሰወር። በስውር አድገው፣ ሀብትና ኑሯቸውን አሳድገው፣ በሕዝብ ልብ ውስጥ በእጥረት እሳቤ ገናና ሆነው ያልፋሉ። በሌላ በኩል ደግሞ እውቀቱ፣ ችሎታው እና ዝናው እያላቸው ዝናቸውን ማስተዳደር ከብዷቸው እዚህም እዚያም ሚዲያ ላይ በመታየት ከሕዝብ ልብ ውስጥ ያላቸውን ተፈላጊነት የሚያጡ ብዙ ናቸው።

ያገኘ ሁሉ ሲጎትታቸው፣ አድናቂ ነኝ ባይ ሲንቃቸው፣ በቀላል በመገኘታቸው ፊታቸው አዲስነቱ፣ ክብራቸው እንግድነት ቀርቶ ይሰለቻሉ። ሴት ልጇን ልትጠይቅ በእንግድነት የመጣች እናት በመጀመሪያው ቀን የንግሥትነት አቀባበል ይደረግላታል።

ባልየው ከአልጋ ወርዶ ያስተኛታል፣ እግሯን ያጥባታል፣ ስትገባ ስትወጣ ቁጭ ብድግ ይላል። ይህች ሴትዮ አንድ ሳምንት ብትቀመጥ “የበሬ እና የሴት እንግዳ የለውም” ትባል እና የቤት ውስጥ ሥራዎችን ከሚስት እኩል መሥራት ትጀምራለች።

ቀናት በነጎዱ ቁጥር አማትነት ቀርቶ፣ እግር ማጠቡ ቀርቶ፣ ከአልጋ ማስተኛቱ ተረስቶ አማት እንደ ማንኛውም ሰው ወለል ልትተኛ ትችላለች። አንቱታ ወደ አንቺ ሊቀየር ይችላል።

እንዲህ አይነት ሴት ሳትሆን ትቀራለች “ዘመድ በሩቁ” የሚልን በመቀራረብ የሚመጣን የክብር መሳሳት፤ በመራቅ የሚገኝን ክብርና ተወዳጅነት የተናገረችው! ነብይ በአገሩ አይከበርም፤ የጓሮ ጠበል የልጥ መንከሪያ ይሆናል፤ በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል የሚሉ አባባሎች አሉ።

የርቀት ነገር ከተነሳ አይቀር አንድ ሐሳብን ደግሞ እንመልከት። “ሩቅ ሀገር ለውሸት ይመቻል” ይባላል። “ጅብ ከማያውቁት ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ አለ” የሚል አቻ አባባልም አለ። አለመታወቅ እንደልብ ያናግራል፤ ንግግርን ኀላፊነት ወስዶ፤ ምን ያስከትልብኛል ብሎ መናገር ደግሞ ከመታወቅ የሚመጣ ነው። ውስጥን  የመናገር  ምኞት እየናጠው አንዳንዴ ዝምታ ተመራጭ የሚሆነውም ምን ያመጣብኝ ይሆን ከሚል ነው። ማሕበራዊ ሚዲያ ላይ በየገጹ እየገቡ የሚሳደቡ ሰዎች ማንም አያውቀኝም ከሚል መነሻ ነው። አለመታወቅ የበለጠ ነጻነትን ይሰጣል።

በሰውኛ ዘይቤ ጠቅሰን ስለ ዱር አደሩ ጅብ ቁርበት ላይ የመተኛት ምኞት ስናወራ ማንም አያውቀኝም በሚል ስሌት ባዕድ አካባቢ ሄደው ከማንነታቸው በላይ የውሸት ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎችን ነው ምናነሳው።

“መካር የሌለው ንጉሥ ያላንድ ዓመት አይነግሥ” የሚለው እንዲሁ መንግሥታት ከሕዝባቸው ጋር ያላቸውን መስተጋብር እንዲያጤኑት፤ ርትዕ እና ፍትሕን እንዲያሰፍኑ የሚያነቃ ነው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሕዝቡን ችላ ብለው በራሳቸው ምቾትና መስመር የተጓዙ ቀን የዙፋናቸው ዕድሜ ያጥራል። ምክር ሳይሰሙ ቢቀሩ ንጉሡም መንግሥቱም በአጭር መቀጨት እጣቸው ይሆናል። “ሰው አይወድም በደል፣ በሬ አይወድም ገደል” እንዲሉ ሕዝብ የተነሳበት መንግሥት ቢያድር ያረፍዳል፣ቢያረፍድ  ያመሻሻል እንጂ አያድርም።

ለፍቅር ብተኛት ለጸብ አረገዘች እንዲሉ፣ አንዳንድ ጊዜ በሰፈሩት ቁና መሰፈሩ ቀርቶ፤ ወርቅ ላበደረ ጠጠር መስጠት  የምድር አሳዛኝ ገጠመኝ ነው። ሰማያዊው ርስት በበዛ ደግነት የሚገኝ ቢሆንም እንኳን ሕዝብ በምድራዊ  ኑሮው፤ በደግ መዋል  በደል ሲደርስበት ይታያል። ለዚህ ነው  “እምብዛም ደግነት ለበግም አልበጃት፣ ዘጠኝ ሆና ሄዳ አንድ ነብር ፈጃት” ሲሉ ደግነት የሚያስከትለውን ምድራዊ  ጣጣ  የሚገልጹት። በዚህ ምክር አልሰማ ያለ ሰው ቢኖር  “በደግነቱ ፣ ተቆረጠ አንገቱ” ብለው አስፈራርተው ለማስጠንቀቅ ይሞክራሉ። በመጨረሻም  “ሊወጋ የመጣ፣ ጌታዬ ቢሉት አይመለስም”  በሚል የአባቶች ብሂል ጽሑፌን እቋጫለሁ።

 

(አቢብ ዓለሜ)

በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here