ክትትል እና ትንበያን አጋዡ

0
208

አቅጣጫ እና መገኛ ቦታ ማመላከቻ (GPS) ለማዕበል እንዲሁም ነጐድጓዳማ ውሽንፍር ለተቀላቀለበት የአየር ንብረት ክስተቶች ክትትል እና ትንበያን በማሻሻል ለቅድመ ጥንቃቄ ተግባራት አጋዥ መሆኑን ቴክኖሎጂ ዶት ኦርግ  አስነብቧል፡፡

በሲውዘርላንድ ዙሪክ በ2021 ሀምሌ ወር እ.አ.አ ሆንግገርብርግ በተሰኘ የዩኒቨርሲቲ ተቋም ጣሪያ ላይ ከሳተላይት እና /የጂፒ ኤስ/ /የጆኦግራፊክ ፓዚሽኒግ ሲስተም/ የተገኘው ሞገድ የተቆራረጠ ወጥነት የሌለው መሆኑን ተመልክተዋል- ተመራማሪዎች፡፡

ተመራማሪዎቹ ከፍተኛ የአየር ሁኔታ ክስተቶች “በጂ ፒ ኤስ” ሞገዶች ጥራት ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድሩም ለመለየት ችለዋል፡፡ “ከጂ ፒ ኤስ” የሚደርሱ ምልክቶች ነጐድጓዳማ ውሽንፍርንም ሆነ ሌሎች በረዶ ያዘለ  ኃይለኛ አውሎ ነፋስን ለማለየት እና ለመተንበይ አበርክቷቸው የጐላ ሊሆን እንደሚችል ከሁነቱ ተገንዝበዋል፡፡

መብረቅ የተቀላቀለበት ጠንከራ  ውሽንፍር ከ”ጂ ፒ ኤስ” በሚደረሱ ሞገዶች ላይ ተጽእኖ ያሳድራሉ፡፡ በመሆኑም በቀጣይ የከባቢ አየር መዛባትን እና ጠንካራ ሁነቶችን ለመቋቋም ለሚደረጉ ጥረቶች አጋዥነቱን አስፍረዋል- ተመራማሪዎቹ፡፡

በተወሰነ አካባቢ ጠንካራ ነፋስ፣ ዝናብ፣ በረዶ፣ ውሽንፈር ወዘተ በሚከሰትበት ወቅት “የጂ ፒ ኤስ” ሞገዶች ተጽእኖ ቢታይባቸውም ጥርት ብሎ ምንነቱን እንደማያመላክት በውል ድምዳሜ ላይ አለመድረሱን  ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል።

በጣሪያ ላይ ከተሰቀለ የርጥበት እና የጠንካራ የአየር ንብረት ሁነት መከታተያና መመዝገቢያ መሣሪያ ባሻገር “ጂ ፒ ኤስ” ርጥበት አዘል እና አውሎ ነፋስ የመሳሰሉትን ለመተንበይ እንደሚያስችል ዶክተር ማቲያስ አይቺንገር ሮዘንበርገር አመላክተዋል፡፡

እስካሁን በተለያዩ ቦታዎች እና ተቋማት የአየር ሁኔታን ሙቀት፣ የርጥበት መጠን በመለካት ክስተቶችን ለመተንበይ ይደረግ ከነበረው አሠራር በተሻለ “ከጂ ፒ ኤስ” መረጃ መሰብሰብ፣ መተንበይ እና ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አዋጪ ስልት ሊሆን እንደሚችል ነው ተመራማሪዎቹ አጽንኦት ሰጥተው ያሰመሩበት፡፡

በመጨረሻም ተመራማሪዎቹ በትልልቅ ከተሞች ወይም በተመረጡ ቦታዎች በየአቅጣጫው የአቅጣጫ መጠቆሚያ እና የተፈጥሯዊ ሁነቶች መረጃ መሰብሰቢያ ጣቢያዎችን ማቋቋም ለቅድመ ጥንቃቄና የሚደርሱ የከፉ አደጋዎችን መቀነስ እንደሚያስችል ነው ያደማደሙት፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here