ጠባቡ ቤት

0
261

በጣሊያን ሲሲሊ ፔትራሊያ ሶታና መንደር ከአዋሳኙ ፈቃደኝነት ወይም ይሁንታ ባለማግኘቱ በእልህ የተሠራው ባለ ሁለት ፎቅ ቤት የዓለማችን ቀጭኑ ወይም እጅግ ጠባብ ቤት የሚል ስያሜ ያሰጠው መሆኑን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል፡፡

በፓልሬም ግዛት ሁለት ሺህ ነዋሪዎች ባሏት ፔትራሊያ ሶታና መንደር የተገነባው 90 ሴንት ሜትር ስፋት ያለው ባለ ሁለት ፎቅ ቤት ለመንደሯ መስህብ ሊሆን መቻሉን ድረ ገፁ አስነብቧል፡፡

ባለሁለት ፎቅ ቤቱ ግንባታው በ1950ዎቹ ነው የተከናወነው፡፡ የፎቅ ቤቱ ባለቤት መሠረቱን ሰፋ አድርጐ ሰርቶ ፎቅ ቤቱን ሽቅብ መገንባት ሲጀምር ከአጐራባቹ ጋር ስምምነት ላይ ሳይደርስ ቀርቷል፡፡

ያኔ ማለትም ግንባታው በተከናወነበት 1950ዎቹ በነበረ ደንብ አንድ ቤት ገንቢ ፎቅ ቤት ሲሠራ ከአጐራባቹ ይሁንታ ማግኘት ግድ ይል እንደነበር ነው የተብራራው፡፡ በመሆኑም ቤት ገንቢው የአጐራባቹን ይሁንታ ባለማግኘቱ በእልህ ለመበቀል ይወስናል፡፡

የፎቅ ቤቱ ገንቢ መሠረቱን በስፋት ቢያወጣም ወደ ላይ ፎቁን መቀጠል ባለመቻሉ 90 ሴንቲ ሜትር ስፋት ጠባብ ቤት ገንብቶ የኋላኛው ፎቅ ቤት የፊት ለፊት እይታ እንዳይኖረው አድርጐ ያዳፍንበታል፤ ብቀላ መሆኑ ነው፡፡

የባለሁለት ፎቅ  የውስጥ ስፋቱ 90 ሴንቲ ሜትር ሲሆን እንኳን መኖሪያ ሁለት ሰው ጐን ለጐን ማሳለፍ አይችልም፡፡ ቀጭኑ ባለሁለት ፎቅ ቤት መውጫ መውረጃ ደረጃ መስኮት ቢኖረውም ውስጡ ባዶ ነው፡፡ ምነው ቢሉ ፎቅ ቤቱ አጐራባቹን ለማናደድ በእልህ የተሰራ እንጂ ለመኖሪያ ቤትነት ምቹ ባለመሆኑ ነው፡፡

ዛሬ ላይ ግን ጠባቡ ፎቅ ቤት ለመንደሯ ዋነኛ የቱሪስት መስህብ መሆኑ ነው በድረ ገፁ የተገለፀው፡፡

(ታምራት ሲሳይ)

በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here