በ26 ዓመታት የትዳር ቆይታ በቤት እመቤትነት ላገለገለችበት የቀድሞ ባለቤቷን 96 ሺህ ዶላር ካሳ እንዲከፍላት በፍርድ ቤት ማስወሰኗን ኦዲቲ ሴንትራል ድረ ገጽ አስነብቧል::
በስፔን የፖንቴቬድራ ግዛት ለ26 ዓመታት በትዳር ስትኖር በቤት እመቤትነት ለሠራችበት ለቀድሞ ሚስቱ ባል 96 ሺህ ዶላር እንዲከፍል ተወስኖበታል።
በድረ ገፁ ስማቸው ያልተጠቀሰው ጥንዶች የትዳር ህይወታቸው አብቅቶ ከተለያዩ በኋላ ባልየው ከቤተሰቡ በተካፈለው መኖሪያ ቤት ህይወቱን ሲቀጥል፤ ሚስት መኖሪያ ቤቱን ለቃለት ተከራይታ ትኖር ነበር:: ለኑሮዋ መደጉሚያ በጣም አነስተኛ የሚባል ጡረታ ይሰጣታል::
በፍቺ መኖሪያ ቤቱን ለቃ የወጣችው ባለቤቱ ብዙም ሳትቆይ ካሳ እንደሚያስፈልጋት አምና ፍርድ ቤት ትከሳለች::
ፍርድ ቤቱ በመጀመሪያ 130 ሺህ ዶላር ካሳ ለባለቤቱ እንዲሰጥ ቢበይንም በሁለቱም ወገን ይግባኝ ቀርቦበታል::
ባልየው ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ብይን ወደ 65 ሺህ ዶላር እንዲቀንስለት ጠይቋል:: የቤት እመቤቲቱ ወይም የቀደሞ ሚስት በበኩሏ ካሳው ወደ 200 ሺህ ዶላር እንዲጨምርላት መረጃና ማስረጃዎችን አቅርባ ተከራክራለች::
የቀድሞ ባል ከፈታት ሚስቱ ያገኟት አንድ ልጅ ራሷን ችላ የምትኖር በመሆኗ ልጇን የመንከባከብ ኃላፊነት የሌለባት በመሆኑ ራሷን ችላ መኖር እንደሚኖርባት ተከራክሯል:: ሰርታ በምታገኘው ህይወቷን መግፋት እንዳለባትም ለችሎቱ አስረግጦ አቋሙን አሰምቷል::
ግራ ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ በሁለቱም ወገን የተነሱ መከራከሪያ ነጥቦችን መዝኖ የመጨረሻ ፍትሐዊ ብያኔውን አሳልፏል:: በመጨረሻው ብያኔ የቀድሞ ባል ለቀድሞ ሚስቱ 88 ሺህ 25 ዩሮ ወይም 96 ሺህ ዶላር እንዲከፍል የተወሰነበት መሆኑን የድረ ገጹ ጽሑፍ አስነብቧል::
(ታምራት ሲሳይ)
በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም