ሕገ መንግሥታዊ ሕግ እና የሕገ መንግሥት መርሆች

0
238

በዚህ ሳምንት የፍትሕ አምድ ጽሑፋችን  ሕገ መንግሥታዊ ሕግ እና የሕገ መንግሥት  መርሆዎች ምንድን ናቸው? ስንል በአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ የፍትሃብሔር ጉዳዮች  ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  አቶ መንበሩ ማናዬን ጠይቀን  እንደሚከተለው አብራርተውልናል:: ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ሕገ መንገሥታዊ ሕግ የሚባለው ሥልጣን ባለው አካል የወጣ ማንኛውም ሕግ  ነው:: ሕገ መንግሥት  የመሰረታዊ ሕጎች፣  መርሆዎች እና ደንቦች ስብስብ እና የሕጎች የበላይ ሕግ ሆኖ አንድ ሀገረ መንግሥት የሚመራበት ስርዓት ነው::

ሕገ መንግሥት የሁሉም ሕጎች ምንጭ እና የበላይ ነው:: ማንኛውም ዜጋ እና የመንግሥት አካል ሕገ መንግሥቱን በአስገዳጅነት ባህሪው ሊያከብረው እና ሊያስከብረው የሚገባ፣ መብት እና ግዴታን የሚያስቀምጥ፣ ሰላም እና ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚያገለግል ሥርዓት ነው::                                                                            ሕገ መንግሥት ከሌሎች ሕጎች የሚለየው መሰረታዊ ጉዳዮችን (ሕገ ነክ እና ሕገ ነክ ያልሆኑ) የያዘ  እና መንግሥትን ለማቋቋም ሥልጣን የሚሰጥ  መሆኑ ነው::

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ስምንት እና ዘጠኝ እንደሰፈረው  ሕገ መንግሥቱ የሕግ አካል ሲሆን የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነ፤ በረገሪቱ ለሚወጡ ሕጎች ሁሉ መነሻ ምንጭ ሆኖ የተቀረጸ፤ መሠረታዊ የሕገ መንግሥት መርሆችን፣ ሌሎች መብቶችን እና ግዴታዎችን አካቶ የያዘ፤ ሁሉም ለሕግ መንግሥቱ ተገዢ መሆን እንዳለበት ኃላፊነትን የጣለ፤ በሕገ ወጥ መንገድ የመንግሥትን ሥልጣን መያዝ የተከለከለ መሆኑን በግልጽ የደነገገ፤ በአቀራረጹ እና በይዘቱ በግልጽ የተቀመጠ እና ሕዝብ ተስማምቶ ያጸደቀው የሉዓላዊነት መገለጫ ሰነድ እንደሆነ ዳይሬክተሩ አብራርተዋል::

ሕገ መንግሥት የተለያዩ ፋይዳዎች እንዳሉት የጠቆሙት አቶ መንበሩ ከእነዚህም መንግሥትን ማቋቋም፣ ሥልጣንን መወሰን እና  መገደብ፣ ሥርዓት መዘርጋት፣ የሕዝብ እሴቶች እና ግቦችን ማመላከት፣ ለሰብዓዊ መብቶች እውቅና እና ጥበቃ መስጠት እንዲሁም  የዜጎችን አንድነት ማጠናከር የሚሉት ይገኙበታል::

በሕገ መንግሥት መሠረታዊ መርሆች

ላይ እንደተገለፀው ሕገ መንግሥት የመሰረታዊ ሕገ መንግሥት መርሆች ስብስብ ነው:: የሕገ መንግሥት መርሆች ሀገረ መንግሥቱ የሚመራበት እና የሀገሪቱ ዜጎች የሚመሩበትን ድንጋጌዎች ማለት ነው:: በተጨማሪም የሕገ መንግሥት መርሆች ወሳኝ እሴቶችን፣ የሕዝብን /የሀገር / ራዕይ እና ፍላጎት                        የሚገልፅበት ነው::

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ የሕገ መንግሥት መርሆች በሕገ መንግሥት ረቂቅ ሂደት መተማመንን ለመፍጠር፣ የመንግሥት እና ሕዝብ እሴቶች እውቅና እና ጥበቃ ለመስጠት፣ በሕገ መንግሥቱ በተካተቱ ጉዳዮች ላይ ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ያገለግላሉ:: እነዚህ የሕገ መንግሥት መርሆች የሕግ የበላይነትን፣  ሉዓላዊነትን፣ የሰብዓዊ መብቶች ማክበርን፣ ግልጸኝነትን፣ ተጠያቂነትን…  ያካትታል::

የሕግ ምንጮች በሀገራችን በፌዴራል እና በክልል ደረጃ ወጥተው ሥራ ላይ ውለዋል::  ሕጎችም በፌዴራል እና በክልሎች የተለያዩ ምንጮች እንዳሏቸው ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል::

ከእነዚህ ውስጥ   የፌደራል የሕግ ምንጮች  አንደኛው ነው:: የኢ.ፌ.ድ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ ዘጠኝ ንኡስ ቁጥር  አንድ ላይ ሕገ መንግሥት የሀገሪቱ የበላይ ሕግ እንደሆነ አስቀምጧል::

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ማንኛውም ሕግ ለአብነት አዋጅ፣ ልማዳዊ አሠራር፣  የመንግሥት አካል ወይም የባለሥልጣን ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት አይኖረውም:: ይህ ማለት ሕገ መንግሥት የማንኛውም ሕጎች መነሻ እና ምንጭ እንዲሁም ሕጋዊነታቸውን የሚያገኙበት መሰረት ነው::

ሁለተኛው ዓምንጭ ለም አቀፍ ስምምነቶች ናቸው። ሀገራት ዓለም አቀፍ ስምምነት ሲፈርሙ ስምምነቱን እንደ አንድ ዓለም አቀፍ ሕግ እንደተቀበሉት ማስረጃ ነው:: የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ዘጠኝ ንኡስ ቁጥር አራት እንደሚደነግገው ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ ሕግ አካል ናቸው::  ስምምነቶች ሥራ ላይ ለመዋል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቅ እና በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትመው መውጣት አለባቸው:: በመሆኑም ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ ሕግ አካል ሆነው ተግባራዊ ይሆናሉ ማለት ነው::

ሦስተኛው የሕግ ምንጮች ደግሞ  ኮዶች ኮዶች እንደሆኑ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል:: እንደ እርሳቸው  ማብራሪያ በሀገራችን በ1960ዎቹ አምስት ኮዶች ተዘጋጅተው ወደ ሥራ ገብተዋል:: እነዚህም የፍትሃብሄር፣ የንግድ፣ የባሕር፣ የወንጀል ሥነ ሥርዓት እና የፍትሃብሄር ሥነ ሥርዓት ሕጎች  ናቸው:: እነዚህ ሕጎችም በነጋሪት ጋዜጣ በአዋጅ መልክ ታውጀው ሥራ ላይ ውለዋል:: ከዚህም በኃላ የተሻሻለው የቤተሰብ፣ የወንጀል እና አዲሱ የንግድ ሕግ በኮድ መልክ ሥራ ላይ የዋሉ የሀገራችን የሕግ ምንጮች ናቸው::

ደንብ እና መመሪያዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ በሚኒስትሮች ምክር ቤት እና  በፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ወይም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ይወጣሉ:: በተጨማሪም የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅ ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ ተሰጥቶታል:: እነዚህ የሕግ ክፍሎች ወይም ዓይነቶች የሀገሪቱ የሕግ ምንጭ በመሆን ያገለግላሉ:: በሥራ ላይ የሚውሉበትን ሁኔታ በተመለከተም አቶ መንበሩ ሲያብራሩ  በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም በሚነስትሮች ምክር ቤት ከታወጁበት ወይም በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ ነው::

አራተኛው የሕግ ምንጭ አስገዳጅ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ናቸው:: ይህም  ፍርድ ቤቶች የሚሰጡት ውሳኔ በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ አስገዳጅ የሚሆኑበት ሥርዓት ማለት ነው:: በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 10 ንኡስ ቁጥር ሁለት ስር እንደተደነገገው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ችሎት የሚሰጠው የሕግ ትርጉም በየትኛውም ደረጃ ላይ ባለ የፌዴራል እና የክልል ፍርድ ቤት ላይ አስገዳጅነት ይኖረዋል ይላል:: ይህ ማለት እነዚህ ውሳኔዎች የሕግ ምንጭ ሆነው ሥራ ላይ ይውላሉ ማለት ነው::

አምስተኛው የሕግ ምንጭ  ልማዳዊ የተሠኘው ነው::  ልማዳዊ ሕጎች በኢትዮጵያ ሕጎች ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት  እንደ ምንጭ ሲያገለግሉ ቆይተዋል:: ለምሳሌ የፍትሃብሄር ሕጉን ያረቀቁት ፕሮፌሰር ሬኒ ዳቪድ በረቂቁ ውስጥ የኦርቶዶክስን ልማዳዊ ሕግ ፍትሐ ነገሥትን እንደምንጭ እንደተጠቀሙበት ገልፀዋል::

በተጨማሪም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 34 ንኡስ ቁጥር አምስት  ስር እንደተደነገገው የግል እና የቤተሰብ ሕግን በተመለከተ በተከራካሪዎች ፈቃድ በሃይማኖቶች ወይም በባሕላዊ ሕጎች መሰረት መዳኘት እንደሚችሉ አስቀምጧል:: በመሆኑም ባህላዊ ወይም ልማዳዊ ሕጎች እንደ አንድ የሕግ ምንጭ ያገለግላሉ ማለት ነው::

ስድስተኛው የክልል ሕግ ምንጮች (የክልል ሕገ መንግሥት ) ነው:: በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 52 ንኡስ አንቀፅ ሁለት ስር እንደተደነገገው ክልሎች የራሳቸውን ሕጎች ማውጣት ይችላሉ:: ስለሆነም ክልሎች የራሳቸው ሕገ መንግሥት ከፌዴራል ሕገ መንግሥት ጋር በሚጣጣም መልኩ አውጥተው እየተገለገሉበት ይገኛሉ:: የክልል ሕገ መንግሥት በክልሎቹ ውስጥ የበላይ ሕግ እንደሆነም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል::

የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት ክልሎች ለአስተዳደር በሚያመች መልኩ የክልሎቹን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት አዋጅ ማውጣት እንደሚችሉ ያስቀምጣል:: ለአብነት ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ሌሎች ክልሎች የራሳቸው የቤተሰብ ሕግ አውጀዋል::

የፌደራል ሕገ መንግሥት የክልል አስፈፃሚ ምክር ቤቶች በክልል ወሰን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ እንዲሁም ደንብ እና መመሪያዎችን ማውጣት እንደሚችሉ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል:: የሕጎች ተዋረድ  የሕጎች የበላይነት ደረጃን ወይም የትኛው ሕግ ከየትኛው ሕግ የበላይ ሕግ እንደሆነ የሚያሳይ ነው:: በሀገሪቱ  በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ ዘጠኝ ንኡስ ቁጥር አንድ  ስር እንደተደነገገው ማንኛውም ሕግ ልማዳዊ ድርጊት እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት እንደማይኖረው ደንግጓል:: ይህ ማለት በሀገሪቱ ውስጥ የሕጎች ሁሉ የበላይ  ሕገ መንግሥቱ እንደሆነ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል::  የፌዴራል ሕገ መንግሥቱ ደግሞ  በፌዴራልም ይሁን በክልል ደረጃ የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ ነው::

የሀገሪቱ የበላይ ሕግ አውጪ አካል ማለትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያወጧቸውን አዋጆች ይከተላሉ:: የዓለም አቀፍ ስምምነቶችን የሕግ ተዋረድ በተመለከተ ወጥ የሆነ መግባባት ባይኖርም በሕገ መንግሥቱ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገረቱ ሕግ አካል ይሆናሉ ስለሚል ከአዋጁ ጋር ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ይቀመጣሉ የሚል ሀሳብ አለ:: በሕግ ተዋረድ በመቀጠል የሚመጡት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚወጡት ደንቦች እና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የሚወጡት መመሪያዎች በቅደም ተከተል ናቸው::

በሌላ በኩል በተመሳሳይ ተዋረድ ላይ ባሉ ሕጎች መካከል መቃረን ሲኖር ተፈፃሚ የሚሆነው በጊዜ ዘግይቶ የወጣው ሕግ  እንደሆነ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል::  ይህ ማለትም ዘግይቶ የወጣው ቀድሞ ከወጣው ይልቅ ተፈፃሚ ይሆናል ማለት ነው:: እንዲሁም ከጠቅላላ ሕግ ይልቅ ልዩ ሕግ ቅድሚያ ተቀባይነት  እንደሚኖረው አረጋግጠዋል::

(ማራኪ ሰውነት)

በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here