“አርበኛዉ እጁ ተይዞ ይሰጠኝ!” – የኢጣሊያ ቅዠት

0
222

በኢትዮጵያውያን ጀግኖች አድዋ ላይ የጣሊያን ጦር የተከናነበው ሽንፈት አጅግ መራር ስለነበር በድጋሜ በሃገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ጦርነት አካሂዷል። ውጤቱ ግን በምንም ሁኔታ ኢትዮጵያዊ ጀግኖችን ማሸነፍ እንደማይችል አጣጥሞ ያለፈበት ነበር።

የወልወሉን ግጭት ሰበብ አድርጎ ጣሊያን የሃሰት ክስ በማዘጋጀት ደረሰብኝ ላለው ጉዳት ኢትዮጵያ 200 ሺህ ብር ካሳ እንድትከፍለው፤ በኢጣሊያ ወታደሮች ላይ ከባድ ጥቃት ያደረሰው አርበኛ ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ደግሞ እጁ ተይዞ ይሰጠኝ ብሎ መጠየቁን የፍስሃ ያዜን “ካልተዘመረለት እያሡ እስከ ተዘመረለት ኢህአዴግ” እንዲሁም የጳውሎስ ኞኞን “የኢጣሊያ እና የኢትዮጵያ ጦርነት” የታሪክ ድርሳናት በማጣቀስ ባለፈው ሳምንት ዕትም የመጀመሪያውን ክፍል አስነብበናል። በዚህ ቀጣይ ክፍል ደግሞ በጣሊያን ጦር ላይ ከፍተኛ ኪሳራ በማድረሳቸው እጃው ተይዞ ይሰጠኝ የተባሉት   ደጃዝማች ዑመር ሰመተር የአርበኝነት ተጋድሎ ላይ በማተኮር ይዘን ቀርበናል፤

መልካም ንባብ!

እብሪተኛዋ ኢጣሊያ የኢትዮጵያን ግዛት በጉልበት እወስዳለሁ ብላ ወልወል ላይ እሳት ጫረች፤ በሁለቱም በኩል ከፍተኛ ጉዳት ደረሰ። በኋላ እርቀ ሰላም አወርዳለሁ ብላ ቃል ስትገባ፤ ድርድርም ስታቀርብ ከኢትዮጵያ ግዛት ተቆርሶ ወደ እኔ ይካተት፤ እንዲሁም በኢጣሊያን ላይ በደል የፈጸሙት ደጃዝማች ዑመር ሰመተር እጅ ተይዞ ይሰጠኝ ስትል ጠየቀች።

ታዲያ ይህን ጥያቄ የሰሙት የኦጋዴኑ አርበኛ ደጃዝማች ዑመር ሰመተር “ከአፈር የሚደባልቅ በልጅግ እና ጎራዴ ይዤ ነው እጄን የማሳየው” ብለው መለሱ።

አርበኛ ደጃዝማች ዑመር ሰመተር በኦጋዴን አካባቢ ጋልካዩ በተባለ ሥፍራ በ1880 ዓ.ም ተወለዱ። በጎሳቸው ባህል እና ልማድ መሠረት አስፈላጊውን ሁሉ ትምህርት እያጠኑም አደጉ።

ለአካለ መጠንም በደረሱ ጊዜ ባስተዳደሩ ሥራ ላይ በማተኮር የሃገር ባላባት ሆነው አገልግለዋል። በዚህም በሶማሌ ክልል ውስጥ የሱልጣን አሊ ዮሴፍ እንደራሴ ሆነው በናኢባነት እንዲሁም የኤል-ቡር ገዥ በመሆን ለ23 ዓመታት ሃገራቸውን በፍጹም ቅንነት አገልግለዋል።

የኢጣሊያን ጦር በወልወል የጫረው እሳት በሰሜን ተያይዞ መላውን ሃገርም እንዳያዳርስ ብለው አርበኞቻችን በዱር በገደሉ ተበትነው ይጠባበቁ ጀመር። የጠላት ጦርም በቅርብ ያገኘውን ያለ ርህራሄ ሲገድል፤ አርበኞቻችን ሲገጥሙት ብርክ እየያዘው መውጫ ቀዳዳውን ይፈልግ ነበር።

በምሥራቁ የሃገራችን ክፍልም ከደጃች አፈ ወርቅ ወልደ  ሰማያት ጋር በመሆን ዑመር ሰመተር የትግሉን ጎራ ተቀላቀሉ። በዚህ ወቅት ከአቻ ወንድሞቹ ጋር በተለያዩ የጦር አውደ ግንባሮች የተሰለፈው የሶማሌ ክልል ጦር ጠላትን መውጫ መግቢያ አሳጥቶ የእግር እሳት ሲሆንበት በተለይም ደግሞ በዑመር ሰመተር የሚመራው ጦር ጎርበሌ ላይ መሽጎ የጠላት ጦርን መድረሻ አሳጣው። በመሪው በዑመር ሰመተር ኢትዮጵያውያን በድል ጎዳና ተራመዱ። ወራሪው ኢጣሊያ በዚህ ሽንፈቱ ሰበብም ነበር ካሳ እንዲከፈለው እና ጀግናው አርበኛ ደጃዝማች ዑመር ሰመተር እጃቸው ተይዞ እንዲሰጠው የጠየቀዉ።

በተለያዩ የጦር አውደ ውጊያዎች ላይ ድልን መጎናጸፍ የጀመረውን የጀግናውን አርበኛ ዑመር ሰመተርን ጦር ኤል-ቡር በተባለው ቦታ ጠላት በስድስት ባታሊዮን ዙሪያውን ከበበው። በዚህ ጊዜ ጀግናው አርበኛ ዑመር ሰመተር የጦራቸውን ሁኔታ አይተው ማፈግፈግን አንደኛው የጦር ስልት አድርገው ለማፈግፈግ ተገደዱ።

ከዚያም ለአምስት ወራት ጦራቸውን አጠናክረው ሶማሌውን፣ አማራውን፣ ኦሮሞውን እንዲሁም ከሌሎች የሃገሪቱ ግዛቶች የተውጣጡ አርበኞችን አስከትለው በ1930 ዓ.ም በጠላት ጦር ላይ አደጋ ጣሉ። ስድስቱንም ባታሊዮን ጦር ከጥቅም ውጭ አደረጉት። የሞተው ሞቶ፤ ቀሪውንም ምርኮኛ አደረጉት። መሳሪያም ማረኩና ተመልሰው ሽላቦ በተባለ ቦታ ላይ ሰፈሩ። አሁንም የጣሊያን ጦር ሽላቦ ድረስ እየመጣ አላስቀምጥ ቢላቸው እንደገና ገጥመው ድል አደረጉት።

ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ጦራቸውን በጦር መሳሪያ እና ስንቅ አጠናክረው እንደገና ቆራሄ ላይ ጠላትን ገጥመው ድል አደረጉት። ከጠላትም ምሽግ ገብተው የጨበጣ ውጊያ በማካሄድ የማይረሳ ጀብዱ ፈጽመዋል።

ከዚያም ወደ ደጋሃቡር በመሄድ ከጦር አለቆቻቸው ጋር ተገናኙ። በዚህም ወቅት የጦሩ የአንድ ክፍል አዛዥ የነበሩት ደጃች ገብረ ማርያም የዑመርን ጀግንነት ተመልክተው ነበርና ከኦጋዴን አውራጃ ካሉት የአካባቢው ተወላጆች ወታደር መልምለው እንዲቀጥሩ ፈቀዱላቸው። የፊታውራሪነት ማዕረግም ተሰጣቸው።

ደጃዝማች ዑመር ሰመተር  በተዋጉባቸው ጦር ሜዳዎች በሙሉ በድል ይወጡ ነበር። በዚህም በጎርሌ ጎቤ፣ በቆራሄ፣ በሃነሴ … በሚያስደንቅ ሁኔታ ጀብዱዎችን ፈጽመዋል።

ደጃች አፈ ወርቅ ወልደ ሰማያት ጦር ሜዳ ላይ ለሃገራቸው ክብር መስዋዕት ሲሆኑ አርበኛውን እያረጋጉ ጦሩን ሲመሩ የነበሩት ደጃዝማች ዑመር ሰመተር እሳቸውም በስድስት ጥይቶች ተመትተው ቆሰሉ። ወደ ጅጅጋ ተመልሰው ህክምና እንዲያገኙ ተደረገ።

ደጃዝማች ዑመር ሰመተር የደረሰባቸው ጉዳት ተመልሰው ጦር ሜዳ ላይ እንዳይሰለፉ አደረጋቸው። ቁስላቸው እጅግ እየባሰባቸው ስለሄደ ወደ ሃርጌሳ እንዲሄዱ ተደረገ። ከሃርጌሳም ተነስተው በኬኒያ በኩል ወደ ለንደን ተወሰዱ። በዚያም ጦርነቱ እስኪያበቃ ድረስ በለንደን በስደት አሳለፉ። ነፃነት ሲመለስ ወደ ሃገራቸው ተመለሱ።

ደጃዝማች ዑመር ሰመተር በሰውነታቸው ውስጥ የቀሩት ጥይቶች ቁስላቸውን እያመረቀዙ ህክምና ቢያደርጉም ሳይሻላቸው ቀረ። ደጃዝማች ዑመር ሰመተር በተወለዱ በ56 ዓመታቸው መጋቢት 10 ቀን 1936 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ቀብራቸውም በሐረር የአብደል መካነ መቃብር ተፈጸመ።

ለሃገራቸው ነፃነት ላበረከቱት ከፍተኛ ተጋድሎ እና ለአርበኝነታቸው መታሰቢያ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኝ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በስማቸው እንዲጠራ ተደርጓል።

(ጥላሁን ወንዴ)

በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here