የኒዩክሌር ሕክምና እንዲስፋፋ በትኩረት እንደሚሠራ ተገለጸ

0
196

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እንደገለጸዉ በፓዮኒር ዲያግኖስቲክስ ማዕከል እና ረዳት ሄልዝ ኬር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማሕበር በተባሉ ሁለት ተቋማት  የኒውክሌር ሜዲሲን ማዕከል ከሰሞኑ ተከፍቷል።

በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ እንደተናገሩት የጤና ሽፋን አገልግሎት ተደራሽነት በመንግሥት አቅም ብቻ የማይሸፈን በመሆኑ የግል ዘርፉ ተሳትፎ ወሳኝ ነው:: መንግሥት የግል የጤናው ዘርፍ ሚናን ለማጎልበት በፖሊሲ የተደገፉ ስትራቴጂክ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ከግል የጤናው ዘርፍ ባለቤቶች ጋር በቅርበት እየሠራ ነው:: በጤናው ዘርፍ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶችንም ለመጨመር የተለያዩ አማራጮችን እና የማትጊያ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት በትኩረት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል::

የኒውክሌር የሕክምና ማዕከል ከፍተኛ ወጪን በመቀነስና የውጭ ምንዛሪን በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት:: መንግሥት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አገልግሎቱ በሚፈለገዉ መልኩ እንዲስፋፋና በሌሎችም ተጨማሪ የሕክምና ማዕከል ለመገንባት ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ተግባር መግባቱን አውስተዋል።

የኑክሌር ሕክምና ልዩ ራዲዮሎጂ ሲሆን  ለጤና ምርምር ማለትም ካንሰርን ጨምሮ ለተለያዩ ሕመሞች ሕክምና በጣም አነስተኛ መጠን ያለው ራዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገር (ራዲዮኑክሊድ ወይም ራዲዮ-መከታተያ) ይጠቀማል። የኒዩክሌር ሕክምና ምስል የተለያዩ ዘርፎች ድብልቅ ነው። እነዚህም ኬሚስትሪ፣ ፊዚክስ፣ ሒሳብ፣ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ እና ሕክምናን ያካትታል።

እንደ አንጀት፣ ጡንቻዎች እና የደም ቧንቧዎች ያሉ ለስላሳ ሕብረ ሕዋሳት (ቲሹዎች) በተቃራኒ ኤጀንት (አዋሃጅ) ጥቅም ላይ ካልዋሉ በቀር በተለመደው ኤክስሬይ (ራጅ) ላይ ለማየት አስቸጋሪ ናቸው። አዋሃጁ (ኤጀንቱ) ግን ሕብረ ህዋሳቱ በደንብ እንዲታዩ ያስችላቸዋል:: የኒዩክሌር ምስል የአካል ክፍሎችን እና የሕብረ ሕዋሳትን መዋቅር እንዲሁም ተግባርን ያሳያል:: ራዲዮኑክሊድ በተወሰነ አካል ወይም ሕብረ ህዋሳት የሚወሰድበት መጠን የአካል ክፍል ወይም ሕብረ ሕዋሳት ምን ያህል እንደሚሠራ ያሳያል። ስለዚህ የምርመራ ራጅ በዋናነት የሰውነት አካልን ለማጥናት ጥቅም ላይ የሚውል ቢሆንም፣ የኒዩክሌር ምስል የአካል ክፍሎችን እና የሕብረ ሕዋሳትን ተግባር ለማጥናት ይጠቅማል።

በሂደቱ ውስጥ አነስተኛ መጠን ያለው ራዲዮኑክሊድ ጥቅም ላይ ይውላል:: ራዲዮኑክሊድ ራዲዮ ፋርማሲዩቲካል ወይም ራዲዮአክቲቭ መከታተያ በመባልም ይታወቃል።

 

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here