የፑቲን ማሸነፍ እና የዓለም ምላሽ

0
196

እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር በ1952 የተወለዱት ቭላድሚር ፑቲን እ.አአ.  ከ2000 ጀምሮ ነው ሩሲያን በፕሬዝዳንትነት እየመሩ የሚገኙት፡፡ ፑቲን በሰሜን ምዕራብ ሩሲያ በምትገኘው ሌኒንጋርድ በአሁኗ ሴንት ፒተርስበርግ በሚገኝ የጋራ መኖሪያ ቤት ነበር ያደጉት፤ የ71 ዓመቱ ቭላድሚር ፑቲን በወጣትነታቸው ዘመን የሩሲያ የስለላ ድርጅት ኬጅቢ ዋና መሥሪያ ቤትን በተደጋጋሚ ደጅ ይጠኑ ነበር፡፡ ይህ ምኞታቸው ተሳክቶላቸውም በሌኒንግራድ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርታቸውን ከተከታተሉ በኋላ እ.ኤ.አ በ1975 የሶቪየት የስለላ ተቋም (ኬጂቢ) አባል ሆነዋል፡፡

እንደ ቢቢሲ ዘገባ  በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ነሐሴ 9 ቀን 1999 የወቅቱ የሩሲያ ፕሬዚደንት ቦሪስ የልሲን ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን አባረው በቀጣይ ዓመት ከተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፊት እምብዛም የማይታወቀውን የ46 ዓመቱን ጎልማሳ ፑቲንን ተኩ። እ.ኤ.አ. በ1999 ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስልጣን የመጡት የቀድሞው የኬጂቢ አባል እና የአሁኑ የሩሲያ ፕሬዚደንት ሌተናል ኮሎኔል ፑቲን ሰሞኑን በተካሄደው ምርጫ በከፍተኛ የድምጽ ብልጫ አሸንፈዋል፤ በሀገራቸው የተካሄደው የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ለምዕራቡ ዓለም መልዕክት ሊያስተላልፍ እንደሚችል ፑቲን ተናግረዋል፡፡ ፑቲን አሁን ካሸነፉት ምርጫ ጋር ተደምሮ ከቀድሞዋ ሶቭየት አምባገነን መሪ ከጆሴፍ ስታሊን በመቀጠል ለረጅም ዓመታት ሀገራቸውን ያስተዳደሩ መሪ ያደርጋቸዋል።

ሮይተርስ እንደዘገበው ፑቲን 87 ነጥብ ስምንት በመቶ ድምጽ በማግኘት ነው ምርጫውን ያሸነፉት፤ ይህም በሩሲያ የድህረ-ሶቪየት ታሪክ ከፍተኛው ውጤት ነው ሲል የሕዝብ አስተያየት ፋውንዴሽን (FOM) አስተያየቱን አስቀምጧል።

ምርጫውን ተከትሎ ታዲያ በተለይ ከኃያላኑ በኩል የትችት አስተያየት እየተሰነዘረ ነው፤ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ እና ሌሎች ሀገራት በፖለቲካ ተቃዋሚዎች እስር እና ሳንሱር ምክንያት ምርጫው ነፃም፤ ፍትሐዊም አልነበረም ብለዋል። ከምዕራባዊያን በተቃራኒ ደግሞ ከእስያ፣ ከላቲን አሜሪካ፣ ከአፍሪካ፣ … ሀገራት የደስታ መልዕክት ተችሮታል፡፡

ፑቲን በሞስኮ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት የድል ንግግር ሩሲያ በዩክሬን ከምታካሂደው ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ ጋር ተያይዘው የሚከናወኑ ተግባራትን ለመፍታት ቅድሚያ እንደሚሰጡ እና የሩሲያ ጦርን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።

“ከፊታችን ብዙ ሥራዎች አሉን። ነገር ግን ማንም ሊያስፈራራን እና ሊያፍነን ቢፈልግ ማንም በታሪክ የተሳካለት የለም፤ አሁን አልተሳካላቸውም እና ወደፊትም አይሳካላቸውም” ብለዋል ፑቲን።

ደጋፊዎቻቸው መድረክ ላይ ሲወጡ “ፑቲን፣ ፑቲን፣ ፑቲን” ሲሏቸው ነበር፡፡ የአቀባበል ንግግራቸውን ካደረጉ በኋላም “ሩሲያ፣ ሩሲያ፣ ሩሲያ” እያሉም ዘምረዋል።

ባለፈው የካቲት ወር 2016 ዓ.ም በአርክቲክ እስር ቤት ውስጥ ታዋቂው የተቃዋሚ መሪ አሌክሲ ናቫልኒ መሞታቸው ይታወሳል፤ በዚህም ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ሩሲያ ውስጥ እና ውጭ ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች ፑቲንን በመቃወም ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ፑቲን ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የሩሲያ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ነው፤ በእርሳቸው ላይ በናቫልኒ ምክንያት የተነሳው ተቃውሞም በምርጫው ውጤት ላይ ምንም ተጽዕኖ የለውም።

የምርጫውን ውጤት ተከትሎ ትችት ከሰነዘሩ ሀገራት መካከል አሜሪካ ትገኝበታለች፤ ምርጫውንም ዴሞክራሲያዊ አይደለም ስትል ነው የተቸችው፡፡ ፑቲን በድጋሚ መመረጣቸውን ተከትሎ በኤንቢሲ ሲጠየቁ የአሜሪካን የፖለቲካ እና የፍትሕ ስርዓትን ተችተዋል። “ዓለም ሁሉ በአሜሪካ እየሆነ ባለው ነገር እየሳቀ ነው” ብለዋል።

ቭላድሚር ፑቲን በከፍተኛ የድምጽ ብልጫ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫን ካሸነፉ በኋላ፣ የምዕራባውያን መንግሥታት ድሉን “ኢ-ፍትሐዊ እና ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነው” በማለት ምርጫውን አጣጥለውታል። የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ምርጫው በሩሲያ ያለውን “የጭቆና ጥልቀት” ያሳየ ነው ብለዋል፤ ተቃዋሚዎችን በማሰሩ የመርጫ ሂደቱ በሚገርም ሁኔታ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ነው ሲል ደግሞ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳውቋል።

በመላው አውሮፓ እና አሜሪካ ያሉ መሪዎች የሰጡት አስተያየቶች ከመላው እስያ፣ አፍሪካ እና በላቲን አሜሪካ ከሚገኙ ሀገራት ከተላለለፉት የደስታ መልዕክቶች በተለየ መልኩ የሚቃረኑ ናቸው። እነዚህ ተቃራኒ ምላሾች ሩሲያ ከሁለት ዓመት በፊት ዩክሬን ላይ ጦርነት ከከፈተችባት ጊዜ ጀምሮ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ባለው ግንኙነት ላይ ቀውስ ከተፈጠረ በኋላ የተሰነጠቀውን የጂኦፖለቲካዊ ጥፋት አጉልተው ያሳያሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዘጠኝ ወራት የቀራት አሜሪካ በጆባይደን እና በትራምፕ ስሜታዊ ንግግሮች እየታመሰች ትገኛለች፡፡ ለአብነትም የሪፐብሊካኑ ዕጩ ተወዳዳሪ ዶላንድ ትራምፕ ከሰሞኑ በኦሃዮ ተገኝተው ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር “በምርጫዉ ካላሸነፍኩ አሜሪካ የደም ባሕር ትሆናለች” ብለዋል፡፡ ይህን በማለታቸው ከፍተኛ ትችት ደርሶባቸዋል፤ ሌሎች የሪፐብሊካን አባላትም ንግግራቸውን ለማስተባበል እና ሌላ ትርጉም ለመስጠት ሲሞክሩ ተስተውለዋል፡፡ ዴሞክራሲን ከኔ በላይ የሚተገብር ሀገር የለም በማለት እና ሌሎች ሀገራትን አምባገነን ናቸው፤ ዴሞክራሲን አይተገብሩም በሚል ስትተች እና ስትኮንን የምትደመጠው አሜሪካ ከዕጩ ፕሬዝዳንቷ ይህ አሳፋሪ ንግግር በመሰማቱ በዓለም ሕዝብ ዘንድ ትዝብት ዘንድ እንድትወድቅ አድርጓታል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለፈው የካቲት ወር የሩሲያዉ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ይልቅ የባይደንን ፕሬዚዳንትነትን እንደሚመርጡ ተናግረው ነበር። በወቅቱ “ባይደን የበለጠ ልምድ ያላቸው እና ሊገመት የሚችል ባሕርይ ያላቸው ሰው ናቸው” ሲሉ መናገራቸውም በርካቶችን አስደንቋል። ዶናልድ ትራምፕ ለመጀመሪያ ጊዜ ለፕሬዚዳንትነት ከመወዳደራቸው በፊት ፑቲን “ታላቅ እና ጎበዝ” በማለት በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2016 ማሞካሸታቸው ይታወሳል።

ባይደን በበኩላቸው የሩሲያውን ፕሬዚዳንት ፑቲንን ለዓመታት በሰላ ሁኔታ በመተቸት  ይታወቃሉ፤ ከሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት በፊትም በአንድ ወቅት “ነፍሰ ገዳይ” ሲሉ ወርፈዋቸው ነበር ሲል ቢቢሲ ላይ ያገኘነው መረጃ ያትታል፡፡

የሩስያ ምርጫ ውጤት በምዕራቡ ዓለም የተወገዘ ቢሆንም፣ በመላው እስያ፣ አፍሪካ እና ላቲን አሜሪካ ያለው ምላሽ አዲስ ዓለም አቀፋዊ ለውጥ እየመጣ መሆኑን ያሳያል ሲል የዘገበው ዘጋርዲያን ነው፡፡

የፑቲንን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማሸነፍን ተከትሎ በርካታ ሀገራት አስተያየቶችን የሰጡ ሲሆን የቻይናዉ ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ፑቲን ምርጫውን በማሸነፋቸው “እንኳን ደስ ያላችሁ” ለማለት የቀደማቸው አልነበረም፤ “ቤጂንግ ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ከሞስኮ ጋር የመሠረተችውን ወሰን የለሽ አጋርነት ማራመዷን ትቀጥላለች” ብለዋል።

ፑቲን በበኩላቸው ድላቸውን ካወጁ በኋላ ለደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር “ታይዋን የቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ አካል ናት” ሲሉ ቤጂንግ በሚገኘው መንግሥት ላይ ያነጣጠሩ አስተያየቶችን ሰጥተዋል። ቻይና ፣ ሩሲያ፣ ብራዚል፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሕንድን ጨምሮ ታዳጊ ምጣኔ ሀብትን በማዋሃድ የአሜሪካን የዓለም ምጣኔ ሀብት የበላይነት ለመገዳደር ዓላማ ያለው የብሪክስ ቡድን አባል ሀገራት ለፑቲን ድጋፋቸውን አሳይተዋል፡፡

በተጨማሪም የታዳጊ ሀገሮች ስብስብ እና ቀደም ሲል በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ ሀገሮች ብዙዎቹ ሩሲያን መደገፋቸውን ቀጥለዋል፡፡

በአብዛኛው የፑቲን ድል የተከበረው በላቲን አሜሪካ መሪዎች በታሪክ ከአሜሪካ ጋር ጠብ ውስጥ በነበሩ መሪዎች ነው። ለአብነትም የቬንዙዌላው ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ለተገኘዉ ውጤት “ታላቅ ወንድማችን ቭላድሚር ፑቲን አሸንፏል፤ ይህም ለዓለም ፖለቲካ ሚዛን ጥሩ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። የኩባዉ ፕሬዝዳንት ሚጌል ዲያዝ-ካኔል ውጤቱን “የሩሲያ ሕዝብ የሀገሪቱን (የፑቲን) አስተዳደርን እንደሚደግፍ ተአማኒ ማሳያ” ብለውታል፡፡

እ.ኤ.አ. ከ2020 ጀምሮ ከበርካታ መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ማሊ እና ኒጀርን ጨምሮ በታጣቂ ቡድኖች በሚመሩት በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ ውስጥ ባሉ በርካታ ሀገራት የፑቲን ድል ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎለታል።

(ሳባ ሙሉጌታ)

በኲር መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዕትም

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here